Get Mystery Box with random crypto!

ረስቶ የሚበላን ወይም የሚጠጣን ፆመኛ ማስታወስ ~ ፆመኛ ሰው ረስቶ ቢበላ ወይም ቢጠጣ ፆሙ አይበላ | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

ረስቶ የሚበላን ወይም የሚጠጣን ፆመኛ ማስታወስ
~
ፆመኛ ሰው ረስቶ ቢበላ ወይም ቢጠጣ ፆሙ አይበላሽም። ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦
من نسي وهو صائم فأكل أو شرب فليتم صومه فإنما أطعمه الله وسقاه
"ፆመኛ ሆኖ ረስቶ የበላ ወይም የጠጣ ፆሙን ባለበት ይቀጥል። ያበላውና ያጠጣው አላህ ነው።" [አልቡኻሪይ፡ 1933] [ሙስሊም፡ 1155]

ይህንን መነሻ በማድረግ ረስቶ የሚበላና የሚጠጣን ሰው ማስታወስ አይገባም የሚሉ አሉ። እንደማጠናከሪያም የኢብኑ ዑመርን 'አሠር' ያጣቅሳሉ።
ኢብኑ ዑመር አስታወኩና [ሊበሉ ሲሉ] "ፆመኛ አይደለህ?" አሏቸው ዐብዱላህ ብኑ ዲናር። በዚህን ጊዜ "አላህ ሊያበላኝ ሸቶ ነበር ከለከልከኝ" አሉ። [አልሙሐላ፣ ኢብኑ ሐዝም 6/221]

ይህንን አሠር' ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ያለ አለ፡
"ሶሒሕ ነው። ከሶሐባም፣ ከታቢዒይም ከተከታዮቻቸውም የተቃረነው አላውቅም። አንዳንድ ዓሊም ግን 'ማስታወስ ይገባል። ይሄ በበጎ ነገርና አላህን በመፍራት ላይ መተባበር ርእስ ውስጥ ይገባል' ይላል። በዚህ ላይ ትክክለኛው ሊያስታውሱት አይገባም የሚለው ነው። ምክንያቱም እሱ ጥፋት አልፈፀመምና። ጥፋት ቢሆን ኖሮ ከነብዩ ﷺ በተላለፈው ረስቶ ከበላና ከጠጣ ፆሙን ባለበት ይቀጥል' በሚለው ሐዲሥ ላይ 'ያበላውና ያጠጣው አላህ ነው' የሚል ቃል ባልኖረ ነበር" [አተሕጂል፡ 154]

ይሄ ንግግር ሙሉ ለሙሉ ስህተት ነው።

1ኛ:- ከሰነድ አንፃር፦

1.1. ሰነዱ ከመነሻው የተቆረጠ እንደሆነ ሙሐላ ላይ በግልፅ ይታያል። ኢብኑ ሐዝም ዘግይተው ነው የመጡት። የዘገቡት ግን ከወኪዕ፣ ከሹዕባ ፣ ... ብለው ነው። ከወኪዕ ጋር ዘመናቸው በጣም የተራራቀ እንደሆነ ይታወቃል፡። ይሄ እየታወቀ ጫፉን ብቻ በመመልከት ሶሒሕ ነው ማለት ተገቢ አይደለም።
1.2. ይሄ ዘገባ ከኢብኑ ሐዝም ውጭ በኢባዲያና መሰል ሀሰተኛ ስራዎች ላይ እንጂ አይታወቅም ይላሉ አጥኚዎች።
1.3. "አላህ ሊያበላኝ ሸቶ ነበር ከለከልከኝ" የሚለው ቃልም ጤነኛ አይደለም። የአላህ መሻት በፍጡር መሻት የሚሰናከል አይደለምና።

2ኛ፦ ከሌሎች ሰለፎች 'ኣሣሮች' አንፃር፦

ይህንን ደካማ ዘገባ የሚቃረኑ ሌሎች መረጃዎች ከሰለፎች በተጨባጭ ተገኝተዋል። ምሳሌ ልጥቀስ:-
2.1. ዐብዱላህ ብኑ ሸቂቅ ረሒመሁላህ ለአቡ ዘር ረዲየላሁ ዐንሁ "ፆመኛ ነህ ወይ?" ብዬ ጠየቅኳቸው ይላሉ። እሳቸውም "አዎ" አሉ። ቤት ስንገባ ግን አብረው መብላት ያዙ። ከዚያ ግን በእጄ እየነቀነቅኩ #አስታወስኳቸው ይላሉ። [አሱነኑል ኩብራ፣ በይሀቂይ፡ 4/293]
2.2. አቡ ጦልሐ በፆም በረዶ ሲበሉ አነስ "ፆመኛ አይደለህንዴ?" ብለው #አስታውሰዋቸዋል። ሸይኹል አልባኒይ "በቡኻሪይና ሙስሊም መስፈርት መሰረት የተዘገበ ትክክለኛ ነው" ብለውታል። [አዶዒፋህ: 1/154]
ማስታወስ እንደሚገባ ከሶስት ሶሐባ አገኘን ማለት ነው። አቡ ዘር፣ አቡ ጦልሐ እና አነስ። እንዲሁም ከዐብዱላህ ብኑ ሸቂቅ። ከኢብራሂም አነኸዒይ፣ ከዐብዱላህ ኢብኑል ሙባረክ፣ ከአሕመድና ከሌሎችም ሰለፎች ማስታወስ እንደሚገባ እንደተገኘ አጥኚዎች ገልፀዋል።
ማስታወስ አይገባም የሚለው ግን ቀደምቶች ዘንድ አይታወቅም። ኋላ ላይ የመጡት ዘንድ ነው የተስተዋለው።

3ኛ፦ ከጭብጥ አንፃር

ረስቶ የበላና የጠጣን ሰው አላህ ነው ያበላውና ያጠጣው የሚለው በድርጊቱ ውስጥ ስህተት የለም ለማለት አይደለም። ኢብኑ ዑሠይሚን ረሒመሁላህ በዚህ መልኩ ተርጉሞ ማስታወስ አይገባም የሚል አለ ተብለው ሲጠየቁ እንዲህ ሲሉ ነበር የመለሱት፦
الذي يقول هذا الكلام جاهل؛ لأنَّ الله تعالى أطعمه وسقاه باعتبار نفسه هو؛ لأنه ناسٍ، أما أنت فأنت عالم، فلا بد أن تنبهه، هذا مثل الذي يقول: إذا رأيت القط يأخذ حمامة شخص فلا تنقذها منه؛ لأنَّ هذا رزق القط، هل هذا صحيح؟ لا.
"ይህንን ንግግር የሚናገር ሰው መሀይም ነው። ምክንያቱም 'የላቀው አላህ አበላው አጠጣው' የሚባለው ከራሱ አንፃር ነው። የረሳ ነውና። አንተ ግን ፆመኛ መሆኑን ታውቃለህ። ስለሆነም የግድ ልታስታውሰው ይገባል። ይሄ 'ድመት የአንድን ሰው እርግብ ስትበለ እንዳታስጥላት። ምክንያቱም ይሄ የድመቷ ሲሳይ ነውና' እንደሚል ሰው ነው። ይሄ ትክክል ነው? በጭራሽ!" [ሊቃኡል ባቢል መፍቱሕ፡ 18]

ስለዚህ የሐዲሡ ጭብጥ ዒባዳ የሚያበላሽን ነገር ረስቶ እየፈፀመ ያለን አካል ማስታወስ አይገባም ማለት አይደለም። በረመዷን ቀን ላይ መመገቡ ስህተት ነው። "አላህ ነው ያበላውና ያጠጣው" ማለት የረሳ ስለሆነ ተጠያቂ አይደለም ለማለት እንጂ በመርሳት የሚፈፀም ስህተት ኢንካር አይደረግም ለማለት አይደለም። ረስቶ ስህተት የሚሰራን ሰው ማስታወስ ይገባል። ሶላት ላይ የሚጋጥምን ስህተት አስመልክቶ ነብዩ ﷺ እንዲህ ይላሉ:-
إِنَّمَا أَنَا بَشَرٌ أَنْسَى كَمَا تَنْسَوْنَ، فَإِذَا نَسِيتُ فَذَكِّرُونِي
"እኔ ሰው ነኝ። እንደምትረሱ እረሳለሁ። ስረሳ ጊዜ አስታውሱኝ።" [አልቡኻሪይ፡ 401] [ሙስሊም፡ 572]
ልብ በሉ! ይሄ አካሄድ ሶላት ላይ ብቻ የሚገደብ አይደለም። ሁሉንም ዒባዳ ይመለከታል። ይህንን ቃዒዳ እናስታውስ፦
العبرة بعموم اللفظ، لا بخصوص السبب
በዒባዳ ላይ የረሳን ማስታወስ ጠንካራ መሰረት ያለው ኢስላማዊ መርህ ነው። ረስቶ ወይም ተኝቶ ሶላት ያለፈው ሰው ወንጀለኛ አይደለም። ይሄ ማለት ግን "አላህ ነው ያስተኛው" ብለን ወቅት እያለፈ ዝም እንለዋለን ማለት አይደለም።
ከዚህ በተቃራኒ ዒባዳን የሚያበላሽ ስህተት በመርሳት ሲፈፀም አታስታውሱ የሚል አንድም መረጃ የለም።

ሳጠቃልል ከዘመናችን ታላላቅ ዑለማኦች ውስጥ ሸይኹል አልባኒይ፣ ኢብኑ ባዝ፣ ኢብኑ ዑሠይሚን፣ ፈውዛን ፆመኛ ረስቶ ሲመገብ ማስታወስ ይገባል ይላሉ። ወላሁ አዕለም።
(ኢብኑ ሙነወር: ረመዷን 25/1445)
=
* ቴሌግራም ቻናል፡- https://t.me/IbnuMunewor
* ፌስቡክ፦ https://www.facebook.com/Ibnu.Munewor?mibextid=ZbWKwL
* ዋትሳፕ፦ https://whatsapp.com/channel/0029VaA3X1e5kg7BlsJboa2M