Get Mystery Box with random crypto!

ዘካተል ፊጥርን የሚመለከቱ ነጥቦች ~ 1- ምንነቱ፦ ሙስሊሞች ከዒደል ፊጥር በፊት ለችግረኞች የሚሰ | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

ዘካተል ፊጥርን የሚመለከቱ ነጥቦች
~
1- ምንነቱ፦ ሙስሊሞች ከዒደል ፊጥር በፊት ለችግረኞች የሚሰጥ የእህል / የምግብ ሶደቃ ነው።
2- ሑክሙ፦ በሚችል ሰው ላይ ግዴታ ነው። [አልቡኻሪይ፡ 1503] [ሙስሊም፡ 984]
3- በማን ላይ ነው ግዴታው?
3.1. በትንሽ በትልቁ፣ በሴት በወንዱ፣ በሁሉም ሙስሊም በሆኑ የቤተሰብ አባላት ቁጥር የሚወጣ ሶደቃ ነው።
3.2. ገና ያልተወለደ ፅንስ እዚህ ግዴታ ውስጥ አይገባም።
3.3. አንድ ሰው የሌሎችን ዘካተል ፊጥር (ለምሳሌ ከሱ ጋር ያልሆኑ ቤተሰቦቹን ወይም የአገልጋዮችን) ማውጣት ይችላል። ግን እንደሚያወጣላቸው ማሳወቅ ይገባል።

4- ምን ያህል አቅም ባለው ላይ ነው ግዴታ የሚሆነው? ለራሱም ለቤተሰቡም ለዒድ ሌሊትና ቀን የሚበቃ ቀለብ ባለው ላይ ግዴታ ነው።
5- ለማን ነው የሚሰጠው? የእለት ጉርስ ለሌለው ድሃ።
5.1. ዘካ እና ዘካተል ፊጥር የሚሰጠው ለሙስሊም ብቻ ነው። ሌሎች ሶደቃዎችን ሙስሊም ላልሆኑ አካላት መስጠት ይቻላል።
5.2. ሑክሙን ባለማወቅ ወይም የሚግገባው አካል ስለማያገኙ ለሰራተኞቻቸው ዘካተል ፊጥር የሚሰጡ ሰዎች አሉ። ሰራተኞቻቸው የማይገባቸው ከሆኑ የተሰጣቸውን ለሚግገባቸው አሳልፈው መስጠት ይኖርባቸዋል።

6- የሚሰጡ የእህል / የምግብ አይነቶች፦ ተምር፣ ዘቢብ፣ አይቤ እንዲሁም በሃገር በአካባቢው ለቀለብነት የሚውሉ፣ ረዘም ላለ ጊዜ ሳይበላሹ መቆየት የሚችሉ የእህል / የምግብ አይነቶች ሁሉ ይገባሉ። ምክንያቱም "ከምግብ አንድ ቁና" የሚል ሐዲሥ አለና። [አልቡኻሪይ፡ 1508] [ሙስሊም፡ 985] በዒዱ እለት መመገብ የሚችሉት አይነት ቢሆን ተመራጭ ነው።
7- መጠኑ፦ አንድ ቁና (ሷዕ) ነው። በአራቱ ኸሊፋዎች ዘመን በዚህ መልኩ ነው ሲፈፀም የኖረው።
7.1. በራስ ፈቃደኝነት ጨምሮ ቢሰጥ ይቻላል።
7.2. የሚሰጠው መጠን በኪሎ ግራም:- በሐዲሥ የመጣው በስፍር ስለሆነ የክብደት መለኪያ ስንጠቀም እንደ እህሉ አይነት መጠኑ ይለያያል። ወደ ኪሎ ሲቀየር ዱቄት ላይ 2.5 ኪሎ አቅራቢያ ይመጣል። ይሄ የአንድ ሰው መጠን ነው። 10 ቤተሰብ ያለው ሰው 25 ኪሎ ማለት ነው።

8- ጊዜው፦ ግዴታ የሚሆነው የረመዷን ወር የመጨረሻ እለት ተጠናቆ የዒዱ ሌሊት ሲገባ ነው። ልብ በሉ! በኢስላማዊው አቆጣጠር የአንድ እለት ቀዳሚው ክፍል ቀኑ ሳይሆን ሌሊቱ ነው።
8.1. ከዒድ ሶላት ማሳለፍ አይፈቀድም። ረስቶ በጊዜው ያላወጣ ሰው ሲያስታውስ ቢሰጥ ወንጀል አይኖርበትም። አውቆ ወይም ችላ ብሎ ወቅት ካሳለፈ ግን ወንጀል ላይ ወድቋል። ቢሆንም ግን የድሃ ሐቅ ስለሆነ ወቅቱ ቢያልፍም ሊያወጣ ይገባል።
8.2. ተቀባዩ በመራቁ የተነሳ በእለቱ ለማድረስ የሚቸገር ሰው "የት ላድርግልህ?" ብሎ ይጠይቅና ከወከለበት ቦታ ያደርግለታል። በዚህን ጊዜ በእለቱ ባይወስድም ችግር የለውም።
8.3. አስቀድሞ መስጠት ይቻላል? ለሚሰበስቡ አካላት አንድ ቀን ሁለት ቀን ቀድሞ መስጠት ይቻላል። ከዚህ ውጭ በጊዜው መስጠት እየተቻለ ቀደም ብሎ መስጠት አይገባም። ነገር ግን በእለቱ ለመስጠት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲኖሩ ትንሽ ቀደም ብሎ መስጠት ይቻላል። እንዲሁም በውጭ ሃገራት ያሉ ሰዎች ለሚሰጥላቸው አካል ቀደም ብለው መላክ ይችላሉ። ወኪሉ ግን በተቻለ መጠን ወቅቱን መጠበቅ አለበት።
9. ከቤተሰብ ርቃችሁ ለምትገኙ ተማሪዎች ወላጆቻችሁ ዘካተል ፊጥር የማያወጡላችሁ ከሆነና የማውጣት አቅሙ ካላችሁ ዘካተል ፊጥር ማውጣት እንዳትረሱ።
10. አስገዳጅ ወይም አንገብጋቢ ሁኔታ ካልገጠመ በስተቀር በገንዘብ ማውጣት አይቻልም። ዝርዝሩ በቀጣይ የሚታይ ይሆናል ኢንሻአላህ።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor