Get Mystery Box with random crypto!

በመውሊድ ላይ ስለሚፈፀመው ጭፈራ ዑለማዎች ምን እንዳሉ ታውቃለህ? ~ በመውሊድ በዓላት የተነሳ የተ | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

በመውሊድ ላይ ስለሚፈፀመው ጭፈራ ዑለማዎች ምን እንዳሉ ታውቃለህ?
~
በመውሊድ በዓላት የተነሳ የተከበሩ የአላህ ቤቶች በጭብጨባ፣ በውዝዋዜና በጭፈራ ክብራቸው ይረከሳል፡፡ ይሄ ደግሞ አላህ እንዲህ ሲል ከሃዲዎችን ከወቀሰባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው፡-
(وَمَا كَانَ صَلَاتُهُمۡ عِندَ ٱلۡبَیۡتِ إِلَّا مُكَاۤءࣰ وَتَصۡدِیَةࣰۚ)
"በቤቱ (በከዕባ) ዘንድም ስግደታቸው ማፏጨትና ማጨብጨብ እንጂ ሌላ አልነበረም፡፡" [አልአንፋል፡ 35]

የአራቱም መዝሀብ ተከታዮች ይህንን ድርጊት ያወግዛሉ፡፡ በጭብጨባ፣ በውዝዋዜና በጭፈራ “ወደ አላህ እቃረባለሁ፣ ዒባዳ ነው” የሚል እምነት አደገኛ ብልግና ነው፡፡ እንዲያውም ይሄ ከክርስቲያኖች የተኮረጀ ጥመት ነው፡፡ ዛሬም ዝላይና ጭፈራን አምልኮት ያደረጉት እነሱ ናቸው፡፡ ሃያሉ ጌታ እንዲከበሩና ስሙ እንዲወሳባቸው ባዘዘባቸው መስጂዶች ውስጥ ድቤ መደብደብ፣ ማጨብጨብና መጨፈር እጅግ አስነዋሪ ተግባር ነው፡፡ ይህን ቆሻሻ ተግባር መቃረቢያ አድርጎ ማሰብ ደግሞ የለየለት ጥመት ነው፡፡ እንዲያውም ኢብኑል ጀውዚይ እንዲህ ብለዋል፡-
وقد نفر جماعة من المتصوفة خلقًا من الخلق عن الكسب، وأوحشوا بينهم وبينه، وهو دأب الأنبياء والصالحين، وإنما طلبوا طريق الراحة، وجلسوا على الفتوح، فإذا شبعوا، رقصوا، فإذا انهضم الطعام، أكلوا، فإذا لاحت لهم حيلة على غنيٍّ، أوجبوا عليه دعوةً، إما بسبب شكر، أو بسبب استغفار. وأَطَمُّ الطامات ادعاؤهم أن هذا قربةٌ! وقد انعقد إجماع العلماء أن من ادعى الرقص قربة إلى الله تعالى، كفر،
“በርግጥም ብዙ ሱፍዮች በርካታ ህዝቦችን ስራ ከመስራት አርቀዋል፡፡ በሱ (በስራ) እና በነሱ መካከል ባይተዋርነትን አንግሰዋል፡፡ ግና ስራ የነብያትና የደጋጎች ፈለግ ነው፡፡ እነዚህ የፈለጉት ግን የእረፍትን መንገድ ነው፡፡ በየምግቡ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ሲጠግቡ ጊዜ ይደንሳሉ፡፡ ምግቡ ሲፈጭ ይበላሉ፡፡ በሃብታም ላይ የሆነ ብልጠት ሲገለጥላቸው በምስጋና ወይም በንስሃ ስም ግብዣ እንዲያዘጋጅ ግድ ያደርጉበታል፡፡ ከመዐቶቻቸው ሁሉ የከፋው መዐት ግን ይህንን (ጭፈራ) መቃረቢያ (ዒባዳ) አድርገው መሞገታቸው ነው፡፡ ዳንስን ወደ ላቀው አላህ መቃረቢያ ነው ብሎ የሞገተ ሰው እንደሚከፍር በርግጥም የዑለማዎች ኢጅማዕ ተቋጥሯል፡፡” [ሶይዱል ኻጢር፡ 168]

ኢማሙ ማሊክ፡- “እኛ ዘንድ ሱፍያ የሚባሉ ሰዎች አሉ፡፡ በብዛት ይበሉና ከዚያ ያንጎራጉራሉ፡፡ ከዚያም ተነስተው ይጨፍራሉ” ሲሏቸው
“ህፃናት ናቸው?” ብለው ጠየቁ፡፡
“አይደሉም” አሏቸው፡፡
“እብዶች ናቸው?” ሲሉ
“አይደሉም፡፡ ሸይኾች ናቸው” አሏቸው፡፡
“እኔ ከኢስላም ሰዎች ይህን የሚሰራ አንድም አልሰማሁም” አሉ፡፡ [ተርቲቡል መዳሪክ: 2/53]

አቡበክር አጦርጡሺም ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “የሱፍያ አካሄድ ቦዘኔነት፣ መሀይምነትና ጥመት ነው፡፡ ኢስላም ማለት የአላህ ቁርኣንና የመልእክተኛው ሱና እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ዳንስና ውዝዋዜ የመጀመሪያ የፈጠሩት የሳሚሪ ባልደረቦች ናቸው (በነብዩ ሙሳ ዘመን)፡፡ ያኔ ድምፅ ያለው የወይፈን አካልን አምላክ ሲያደርግላቸው ጊዜ መጥተው ዙሪያውን ይጨፍሩና ይወዛወዙ ነበር፡፡ ማለትም ጭፈራ የከሃዲዎችና የወይፈን አምላኪዎች ሃይማኖት ነው፡፡ የነብዩ ﷺ እና የሶሐቦቻቸው ጉባኤ ልክ ከራሳቸው ላይ ወፍ ያረፈ እስከሚመስል መረጋጋት ነበራቸው፡፡ እነዚህን (ጨፋሪ) ሰዎች አሚሩ መስጂድ ውስጥም ይሁን ሌላ ቦታ (ጭፈራቸውን) ከመፈፀም ሊከለክላቸው ይገባል፡፡ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን የሆነ ሰው ከነሱ ጋር ሊካፈል፣ በጥፋትም ላይ ሊያግዛቸው አይፈቀድለትም፡፡ የማሊክም፣ የአቡ ሐኒፋም፣ የሻፊዒይም፣ የአሕመድም፣ የሌሎችም ሙስሊም ምሁራን መዝሀብ ይህን ነው የሚያዘው፡፡” [ተፍሲሩል ቁርጡቢይ፡ 11/238]

አልዒዝ ኢብኑ ዐብዲሰላምም፡- “ጭፈራ ቢድዐ ነው፡፡ አእምሮው ጎደሎ የሆነ እንጂ አይፈፅመውም” ይላሉ፡፡ [ፈታዋ አልዒዝ ብኒ ዐብዲ ሰላም፡ 318-319]

ይህንን ይዘን በየመውሊዱ መስጂድ ውስጥ አግድም ተሰልፈው፣ ድቤ እየደለቁ፣ ለፉጨት የቀረበ ድምፅ እያወጡ፣ ቀረርቶ በመሰለ ድምፅ እያላዘኑ የሚወዛወዙ የጠመጠሙ መሃይማንን አስቡ፡፡ ከአላህ ቤት ጭፈራ ዲን ሆኖ ሲቀርብ ተመልከቱ፡፡ አላሁል ሙስተዓን!
~
የቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/IbnuMunewor