Get Mystery Box with random crypto!

አክሱም ላይ አንቀላፍቶ ማይጨው ላይ መንቃት የቀጠለ ነገርግን አክሱምን፣ ላሊበላን፣ ፋሲልና ጀጎ | የስብዕና ልህቀት

አክሱም ላይ አንቀላፍቶ
ማይጨው ላይ መንቃት
የቀጠለ

ነገርግን አክሱምን፣ ላሊበላን፣ ፋሲልና ጀጎልን የጠረቡ እጆች ስለምን ለሺህ ዘመናት በደሳሳ ጎጆዎች ውስጥ እንደተቸነከሩ ማሰብ ሕመምን ይፈጥራል፡፡ ፊደል ነበረን፤ እንደ ሕዝብ ከመጻፍ ይልቅ መስማትን እንመርጣለን፡፡ ይበልጡኑ መሀይማን ነበርን፡፡ በኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አማካኝነት ሙዚቃን በኖታ በመጻፍ የመጀመሪያዎቹ ብንሆንም እዚሁ አበርክቶ ላይ ጥቂት ሀሳብ ለመጨመር የተክሌ አቋቋም, እስኪቀመር አንድ ሺህ ሦስት መቶ ዓመታት መጠበቅ ነበረብን፡፡

በ1237 ዓ.ም አካባቢ ከሦስት መቶ ዘመናት የዛግዌያን አገዛዝ በኋላ ሥልጣን በቤተክርስቲያን ጠንካራ ተጽዕኖ ከዛግዌ ነገሥታት ወደ የዘር ሀረጋቸውን ከሰሎሞን ዘር እንመዛለን ለሚሉ ሰሎሞናዊ ነገሥታት ተዛወረ፡፡ የዛግዌ ነገሥታትን ሥልጣኑን ለሰሎሞናዊው ገዥ ይኩኖአምላክ እንዲያስተላልፉ በመወትወት፣ በመገሰጽ አቡነ ተክለኃይማኖት ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ይነገራል፡፡
በሂደቱም ቤተክርስቲያን እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ድረስ የዘለቀ የክፍለዘመናት የሢሶ መንግሥትነት ፈላጭ ቆራጭነቷን አጸናች፡፡

ጥቂት ቆይቶ በ330 ዓ.ም አካባቢ የሰሎሞናዊ ስርወመንግሥቱን በትርክት እና በሕግ ለማጽናት ሲባል ‹ክብረነገሥት› የተሰኘው መጽሐፍ የመጻፉ አስፈላጊነት ታመነበት፡፡

መጽሐፉ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ ሥልጣን ባለቤቶች የዘር ሀረጋቸውን ከንጉሥ ሶሎሞን እና ከቀዳማዊ ምኒሊክ ዘር የሚመዙ ብቻ መሆናቸውን በማያሻማ ኹኔታ ይደነግጋል፡፡ በዚህም መጽሐፍ የተነሳ ኢትዮጵያን ሀገራቸውን እንደዳግማዊት ኢየሩሳሌም እንዲመለከቷት ተበረታተዋል፡፡ ለዘመናት በክርስትና እምነት መነሻነት በተገነባው በዚህ ትርክት እና በክርስትው ኃይማኖት ምክንያት ከኢትዮጵያ ውጭ በኢትዮጵያዊያን (በሰሜነኛው ክርስቲያን) አዕምሮ የታተመች ሌላ ከተማ (ሀገር) ብትኖር ኢየሩሳሌም ብቻ ናት፡፡ በዚህ ሰበብ ይመስላል ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ከውጭው ዓለም የመጣውን ሰው በተለይ ክርስቲያኑን ሁሉ የኢየሩሳሌም ሰው እንደሆነ ይቆጥሩ እንደነበር በልዩ ልዩ ተጓዦች ማስታዎች ላይ ተዘግቧል፡፡

በዚህ መልኩ በአስራ አራተኛው መቶ ክፍለዘመን መጀመሪያ የተጻፈው ክብረነገሥት ከፊውዳል ሥርዓቱና ከቤተክህነቱ ጋር ተቀይጦ በኢትዮጵያ የሥነ መንግሥት ታሪክ ሰባት መቶ ዘመናት ድረስ የዘለቀ ገዥ ትርክትን ፈጠረ፡፡ ይህ ትርክት በተለይ ከሞላ ጎደል በአንድ አገዛዝ ሥር የሚያድር፣ ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን የሚናገር በአብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታይ የሆነውን ሰሜነኛ ሕዝብ ለሰባት ክፍለዘመናት ያስተዳደረ መሪ ትርክት ሆኖ አሳለፈ፡፡ ዳግማዊ ምንይልክ የተበታተነውን የዳር ሀገር ሕዝብ ሁሉ በአንድ አጠቃለው በዘውዳዊ ሥርዓቱ ሥር ካስገቡትም በኋላ በዚህ ትርክት ሥር እንዲመላለስ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ የሰመረ ነበር ባያስብልም ቢያንስ በእሳቸው ዘመን ትርክቱ የአንድነት ስሜት በመፍጠሩ የአድዋ ጦርነትን የመሰለ በተባበረ ከንድ የተገኘ እጅግ አንጻባራቂ ገድል ለመከወን መሣሪያ ሆኗል፡፡

ኢጣሊያኖች ኢትዮጵያን ዳግም የወረሩ ሰሞን በቅኝ ገዥ ሴራ ሕዝቡን ለመከፋፈል አማርኛ ተናጋሪውን ሕዝብ በጅምላ የፊውዳል ሥርዓቱ ተጠቃሚ እና ጨቋኝ ገዥ መደብ እንደሆነ ፈርጀው ትርክታቸውን ማጠንጠን ጀመሩ፡፡ ይህ ትርክት በተለይ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ድፍን ሃያ ሰባት ዓመታት በሕገመንግሥት፣ በመንግሥት በጀት፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙሃናት በይፋ እና በስውር እንደ አስፈላጊነቱ ይቀነቀን ነበር፡፡ በበኩሌ ሰሜነኛው ሕዝብ ለፊውዳል ሥርዓቱና ለአገዛዙ በነበረው ጂኦግራፊያዊ ቅርበት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ሕዝብ በተለዬ ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ ከሁሉም በላይ በሥርዓቱ ይበደል እንደነበር አስባለሁ፡፡

ከ2010 ዓ.ም በኋላ የመጣው አስተዳደር በመደመር ግራ የገባው ቅኝት እዚያ እና እዚህ እየረገጠ ምንም የትርክት ለውጥ ሳያስፈልገው የጨቋኝ ተጨቋኝ የትርክት ንጥቂያ እና ቁማርን ማስቀጠሉን ለመረዳት ብዙ የፖለቲካ ብስለት የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡

እኛ ግን ለመላው ጥቁር ሕዝብ ትርክት ቀማሪነት የታጨን ሆነን ሳለን የራሳችን የቤት ሥራ እንኳን ሰርተን ያልጨረስን መሳቂያ የመሆናችን ነገር ያሳዝናል፡፡ ታላቁ ጥቁር የተሰኘ በንጉሴ አየለ ተካ የተጻፈ መጽሐፍ ያነበበ ሰው ሁሉ ንጉሠ ነገሥቱ አጼ ኃይለሥላሴ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ስር ለነበሩ ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ እንደምን ይታገሉ እንደነበር መታዘብ ይችላል፡፡

ታሪካችንን አላወቅነውም፡፡ መናናቂያ አድርግነዋል፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ያገኘነውን በሰው ዘርን ሁሉ ፊት በግርማ ሊያስጠራን የሚችል ዕድል እንደዘበት አምልጦናል፡፡ እናስ ያቆሙን መሰረቶች ምን ያህል ጽኑዓን ነበሩ? እንደ ኅብረተሰብ የአቋራጩ፣ ልክፍተኞች ሆነን ለመገኘታችን ምክንያቱ ምንድን ነው? የምንዋቀሰው፣ የምንናናቀው በድንቁርናችን ልክ አይደለምን? ለፍጥረት ሁሉ ከሚተርፍ በረከት፣ ኅሊና እና ርህራሄ ጋር ተፈጥረን ሳለን ዘመኑን ስላለመዋጀታችን በሰንደቅ ዓላማ ለሚያስለምን ችጋር ራሳችንን አላጨንምን?

ይቀጥላል
ደራሲ-ያዕቆብ ብርሀኑ
መፅሀፍ-በፍም እሳት መቃመስ