2023-05-08 13:57:28
ታላቁ የበድር ዘመቻ #9የእብሊስን ወደ ኋላ መፈርጠጥ የተመለከቱ ሙሽሪኮች
"ሱራቃ ሆይ! ወዴት ነው የምትሸሸው? ወዴት ነው የምትሄደው? ከለላ እንደ ምትሰጠንና መቼም እንደ ማትለየን ቃል ገብተህልን አልነበረምን??" ብለው መጣራት ጀመሩ።እብሊስም
{وَقَالَ إِنِّي بَرِيءٌ مِّنكُمْ إِنِّي أَرَىٰ مَا لَا تَرَوْنَ إِنِّي أَخَافُ اللَّهَ ۚ وَاللَّهُ شَدِيدُ الْعِقَابِ}
{እኔ ከእናንተ የጠራሁኝ ነኝ፤ እኔ እናንተ የማታዩትን አያለሁ፤ እኔ አላህን እፈራለሁ፤ አላህም ቅጣተ ብርቱ ነው። አላቸው።} [አል_አንፋል:48]
እብሊስ በዚህ መልኩ ሲያፈገፍግ አቡ ጀህል ወደ ህዝቦቹ በመቀጣጨት ምንም ነገር ሳይፈሩና ሳይሸበሩ በድፍረት እንዲጋደሉ ያነሳሳቸው ቀጠለ። የሙስሊም ወታደሮችንም ያሳንስና ይዝትባቸው ጀመረ። እሱ ግን የሙስሊሞች ጀግኖች አግኝተው እንዳይገሉት ህዝቦቹ ዙሪያውን ከበው ይጠብቁታል። ነገር ግን አስር ጊዜ ቢከበብና ቢጠበቅም በሙስሊሞች ፊት ተዋርዶ ዱንያውም አኼራው ያከሰረበት የሞት ፅዎ ከመጎንጨት አልዳነም።
የዚህ የጀሀነም ውሻ አሟሟት ታላቁ ሰሀብይ ዐብዱረሕማን ቢን ዓውፍ አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና እንደ ሚከተለው ይገልፅልናል……
"የበድር ቀን በሰፍ ላይ ሳለሁኝ ወደ ቀኜና ግራዬ ስመለከት ሁለት ከአንሷር የሆኑ ታዳጊ ልጆች መሃል አርገውኝ ቆመዋል። አንደኛው ነካ አደረገኝና
“አጎቴ ሆይ! አቡ ጀህል ታቀዋለህ እንዴ?” አለኝ።
“አዎን! ግን የወንድሜ ልጅ ሆይ! ከእሱጋ ምን ጉዳይ አለህ?” አልኩት።
“እኔ የአላህ መልእክተኛﷺ እንደ ሚሳደብ ተነግሮኛል። ነፍሴ በእጁ በሆነችው አላህ ይሁንብኝ; ያገኘሁት እንደ ሆነ ከሁለታችን አጀሉ የደረሰው ሳይሞት ሰውነቴ ከሰውነቱ አይላቀቅም!!” አለኝ። በጣም ተገረምኩኝ። ሌላኛውም ነካ አደረገኝና ተመሳሳይ የሆነ ነገር ጠየቀኝ። ቲንሽም ሳልቆይ አቡ ጀህል በሰዎች መሃል ሲንጎራደድ አየሁት። ጠራኋቸውና ይኸው የምትፈልጉት ሰውዬ ያንን ነው። አልኳቸው። ሁለቱም ተሽቀዳድመው በሰይፋቸው መቱት። አቡ ጀህልም ወድቆ መንፈራገጥ ጀመረ። ከዝያም እየሮጡ ወደ ነብዩﷺ መጥተው ነገሯቸው።
«ማንኛችሁ ነው የገደለው?» ሲሏቸው ሁለቱም
“እኔ ነኝ የገደልኩት፤ እኔ ነኝ የገደልኩት” አሉ ነብዩﷺ »ሰይፋችሁ ጠርጋችሁታል?» ሲሏቸው “አልጠረግነውም።” አሉ። «አሳዩኝ» አሏቸውና አሳዯቸው። ነብዩﷺ «ሁለታችሁም ገድላችሁታል።» አሏቸው።"
ሙሽሪኮችም ሽንፈታቸው በተረጋገጠላቸው ጊዜ ጓዛቸውንና መጓጓዣቸውን ጥለው ማፈግፈግና መሸሽ ጀመሩ። ጀግኖቹ የኢስላም ወታደሮች ከኋላ እየተከተሉ ከሙሽሪኮች የፈለጉትን እየገደሉ፤ የፈለጉትን እየገረፉ፤ የፈለጉትን አስረው ምርኮኛ አደረጉ።
ውጊያው ከተጠናቀቀ በኋላ ከፊል ሰዎች ወደ ነብዩﷺ በመምጣት “የንግድ ቅፍለቱን አሁን እንከተለው ምንም ተከላካይ የላቸውም" ሲሏቸው የነብዩﷺ አጎት የነበረውና ከመስለሙ በፊት ከሙሽሪኮች ጎራ የነበረው ዓባስ "ንግዱን መከተል የለብህም ለአንተ አይበጅም" አላቸው። ነብዩﷺ «ለምን?» ሲሉት; "አላህ ቃል የገባልህ ከሁለቱ ጭፍሮች አንዱን ነበር በቃ አንዱን አግኝተሃል" አላቸው። ነብዩምﷺ «በእርግጥም እውነት ብለሃል» ብለውት ቅፍለቱን ከመከተል ተቆጠቡ።
ከሙስሊሞች በኩል በበድር ዘመቻ ሸሂድ የሆኑት በአጠቃላይ [14] ነበሩ። ስድስቶቹ ከሙሃጂሮች ሲሆኑ ስምንቶቹ ከአንሷር ነበሩ። ……በአላህ ፍቃድ ክፍል 10 ይቀጥላል……
ሐምዱ ቋንጤ
ከፉርቃን ሰማይ ስር!!t.me/joinchat/Q0mf35Z6QEmajDQB
680 views10:57