Get Mystery Box with random crypto!

የቤቶቹ ጨረታ ላይ የተነሳው ጥያቄ ምንድነው ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የ1997 ዓ. | Housing in Addis Ababa የአዲስ አበባ ቤቶች

የቤቶቹ ጨረታ ላይ የተነሳው ጥያቄ ምንድነው ?

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የ1997 ዓ.ም. የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ዕጣ ያልወጣላቸው ቆጣቢዎች ያቀረቡለትን አቤቱታ መሠረት በማድረግ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ከ3 ሺህ ቤቶች በላይ በሽያጭ ለማስተላለፍ ያወጣው ጨረታ ላይ የሕጋዊነትና የፍትሐዊነት ጥያቄ አንስቷል።

የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አጋጠመኝ ያለውን የፋይናንስ አቅም ችግር ለመፍታትና ተጨማሪ ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ለመገንባት፣ ከከተማው የዲዛይንና ግንባታ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን 3,146 የመኖሪያ ቤቶችንና 306 የንግድ ሱቆችን በጨረታ ለመሸጥ ማቀዱን መግለጹ ይታወሳል።

በ1997 ዓ.ም. ተመዝግበው ከስቱዲዮ እስከ ባለ3 መኝታ ቤት ድረስ ቤቶች ለማግኘት እየቆጠቡ ያሉ 959 ነዋሪዎች፣ እያንዳንዳቸው ምን ያህል እንደቆጠቡ የሚገልጽ ሙሉ ስማቸው ከፊርማቸው ጋር ያረፈበትና በድምሩ 144,820,085.43 ብር መቆጠባቸውን ከሚያሳይ ሰነድ በማያያዝ፣ ኮርፖሬሽኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ለመሸጥ የጀመረውን ሒደት #እንዲያሳግድላቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ለዕንባ ጠባቂ ተቋም ጨረታው ይፋ በተደረገበት ዕለት አስገብተው ነበር።

አቤቱታቸውን የተቀበለው ዕንባ ጠባቂ ተቋም የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም በዋና ዕንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) ተፈርሞ በወጣ ደብዳቤ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በ7 የሥራ ቀናት ውስጥ ምላሹን እንዲያሳውቀኝ ሲል 4 ጥያቄዎችን አቅርቧል። 

1ኛ. ኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ በሽያጭ የማስተላለፍ ሕጋዊ መሠረት ያለው ስለመሆኑ በማስረጃ ተደግፎ እንዲቀርብ ብሏል። 

2ኛ. መኖሪያ ቤቶቹ በጨረታ ለሽያጭ ሲቀርቡ የ1997 ዓ.ም. እና የ2005 ዓ.ም. የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎችን ቅድሚያ በመስጠት፣ በልዩ ሁኔታ ተሳታፊ ያልተደረገበት ምክንያት እንዲገለጽ ጠይቋል። 

3ኛ. ኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ ቤቶችን ከዕጣና ከምደባ ውጪ በጨረታ ሽያጭ ለማስተላለፍ ሲወስን፣ በ1997 ዓ.ም. እና 2005 ዓ.ም. ተመዝግበው ቤት እየተጠባበቁ ያሉ ነዋሪዎች ጉዳይ ላይ ግልጽና የመጨረሻ ውሳኔ ያልተሰጠበትን ምክንያት እንዲገለጽ የሚል ጥያቄ አቅርቧል። 

4ኛ. ኮርፖሬሽኑ ቤቶችን በጨረታ ለመሸጥ ሲወስን ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የከተማው ነዋሪዎችን አቅም ባገናዘበ መንገድ የጨረታ መነሻ ዋጋና የአከፋፈል ሥርዓት ሊታይ ያልቻለበትን ምክንያት በመግለጽ፣ ኮርፖሬሽኑ ምላሹን በሰባት የሥራ ቀናት ውስጥ እንዲሰጥ ሲል በደብዳቤ ጠይቋል።