Get Mystery Box with random crypto!

#ፒያሳ በአዲስ አበባ ፤ ፒያሳ አካባቢ በተለምዶ ' ዶሮ ማነቂያ ' ተብሎ በሚጠራው ቦታ የሚገኙ | Housing in Addis Ababa የአዲስ አበባ ቤቶች

#ፒያሳ

በአዲስ አበባ ፤ ፒያሳ አካባቢ በተለምዶ " ዶሮ ማነቂያ " ተብሎ በሚጠራው ቦታ የሚገኙ ነዋሪዎች፤ በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ ከስፍራው እንዲነሱ ቀነ ገደብ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ምትክ የመኖሪያ እና የንግድ ቦታ ሳያዘጋጅላቸው፤ ከስፍራው " በአጭር ጊዜ ውስጥ " ተነሱ ማለቱ በነዋሪዎቹ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ አስነስቷል።

የፒያሳና 4 ኪሎ አካባቢ መልሶ የማልማት ፕሮጀክትን በተመለከተ ትላንት በወረዳ ደረጃ የተደረጉ ውይይቶች " በአለመግባባት " እና " በረብሻ " መበተናቸውን ተከትሎ ዛሬ ከአዲስ አበባ አስተዳደር እና ከአራዳ ክ/ከተማ የስራ ኃላፊዎች ጋር ነዋሪዎች ውይይት አድርገው ነበር።

ነዋሪዎች ምን አሉ ?

° በፒያሳ አካባቢ በአክሲዮን የተደራጁ ነዋሪዎች ማህበርን በሰብሳቢነት የሚመሩ ግለሰብ ፦

" ቤት ለመቀባት እንኳ 3 ቀናት ይበቃል ወይ? ትላንት በነበሩ ውይይቶች ይህንን ውሳኔ የሰሙ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ለሊቱን ሙሉ ሳይተኙ አድረዋል።አሁንም በስጋት ላይ ናቸው። "

° 5 አባላት ያሉት ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን የገለጹ እናት ፦

" አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደ እኔ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ናቸው። በስፍራው የታቀደው የመልሶ ማልማት ነዋሪዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ እና ምትክ የመኖሪያ ስፍራ ያዘጋጀ ሊሆን ይገባዋል። "

° ሌላኛዋ የአካባቢው ነዋሪ ፦

" ለልማት ተነሺዎች የሚያዘጋጀው አማራጭ የስፍራውን ማህበራዊ ትስስር በማይበጥስ መልኩ ሊደርግ ይገባል። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለን የአካባቢው ነዋሪዎች እርስ በእርስ ተደጋግፈን የምንኖር በመሆናችን ምትክ የኮንዶሚኒየም ቤት የሚሰጠን ከሆነ በአንድ ቦታ ላይ የምንሰፍርበት ሁኔታ ይመቻች ። "

ከባለስልጣናት ምን ምላሽ ተሰጠ ?

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጥላሁን ፤ ነዋሪዎቹን ከቦታው ለማንሳት ያቀደው በዘጠና ቀናት ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል።

አስተዳደሩ ለነዋሪዎች  ምትክ የኮንዶሚኒየም፣ የቀበሌ እና የኪራይ ቤቶች እንደሚያዘጋጅ ቃል ገብተዋል። 

የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ተቀባ ፤ አስተዳደሩ " ቅደመ ሁኔታ ሳያሟላ አንድም ሰው አይነቃነቅም " ብለዋል።

የከተማው አስተዳደር " ቅደመ ሁኔታውን ካሟላ " ነዋሪዎች በ3 ቀን ቢነሱ ችግር እንደማይፈጥርም ጠቁመዋል።

" ይህ ፕሮጀክት እንዳያልቅ የሚያንጓትት ካለ ኃላፊነቱን ራሱ ነው የሚወስደው " ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በዛሬው ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ በመልሶ ማልማቱ የልማት ተነሺዎቹን ሂደት የሚከታተል ኮሚቴ አባላት ምርጫ ተከናውኗል።

በመልሶ ማልማት እቅዱ የተካተተውን የፒያሳ አካባቢን በ6 በመክፈል፤ ከእያንዳንዱ ስፍራ 6 ሰዎች በህዝብ ተመርጠዋል። 

(ከላይ በፒያሳ ስለሚካሄደው መልሶ ማልማት ስራ ማብራሪያ ተያይዟል)

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ይህ መረጃ የ " ኢትዮጵያ ኢንሳይደር " መሆኑን ይገልጻል።

@tikvahethiopia