Get Mystery Box with random crypto!

የገላትያ መልዕክት ማብራሪያ/ ክፍል 6/ የአይሁድ ሕግ ብቁ አለመሆኑ/ ገላ 2:15-21/ 15 | ሕያው ቃል

የገላትያ መልዕክት ማብራሪያ/ ክፍል 6/

የአይሁድ ሕግ ብቁ አለመሆኑ/ ገላ 2:15-21/

15-16 ጳውሎስ ንግግሩን በመቀጠል ለጴጥሮስና በገላቲያ ለነበሩ አይሁድ ክርስቲያኖች «እኛ አይሁዳዊ ነን ኃጢአተኞች የሆኑ አረማውያን አይደለንም »ይላል በአይሁድ አመለካከት ከሕዛብ ሁሉ የአይሁድን ሕግ ሰለማይከተሉ ኃጢአተኞች እንደሆኑ ይቆጠራል ። ጳውሎስ የሚናገረው በአይሁድ አመለካከት ነው ። ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች የሆንን አይሁድ እንኳ ሰው ሕግን በመጠበቅ እንደማይጸድቅ እናውቃለን ይላል። አይሁድ እና አሕዛብ ጻድቅ ተብለው ሊጠሩ የሚችሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ካመኑ ብቻ ነው ። /ሐዋ 15:11/ ።ጳውሎስ ከመጀመሪውኑ ለገላቲያ ሰዎች ያስተማረው እውነተኛ ወንጌል ይህ ነው ። ካዲያ የገላትያ ክርስቲያኖች በኢየሱስ በማመን ከጸደቁ በኃላ አሁንም ለመጽደቅ የአይሁድን ሕግ መፈጸም ያስፈልጋል ወደሚለው እንዴት ዞር አሉ ? ይህ ሊሆን ይገባል ።

አንድ ሰው ለድህነት የሚያስፈልገው ምን እንደሆነ ሁላችንም ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል ። በመጀመሪያ መልካም የሆኑ ነገረ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጸጋ የሚመጣ እንደሆነ ማወቅ ። ከእግዚአብሔር ጸጋ ማለትም ከፍቅሩ የተነሳ ክርስቶስ ሰዎችን ለማዳን ወደ ምድር እንደመጣ ። አይሁድ ይሁን አረማዊ ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ነው ። /ሮሜ 3:23-23/ ። ስለዚህ ሁሉም ሰው የኃጢአት ቅጣት ከሆነው ከዘላለም ሞት የሚያድነው አዳኝ ያስፈልገዋል ።/ ሮሜ 6:23/ ። ምህረት የማይገባን ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለኛ ሞተ ። ክርስቶስ የእኛን ቅጣት ስለ ተቀበለልን በእርሱ ያመንን እኛ በእግዚአብሔር ዓይን ጻድቅ ሆነን እንጂ እንደ ተፈረደብን ሰው አንቆምም ። ይህም ሁሉ የእግዚአብሔር ጸጋ ውጢት ነው ።

ታዲያ ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት ? በክርስቶስ ማመን አለበት ። የእግዚአብሔር ጸጋ ጸጋ መቀበል ይኖርበታል ። እግዚአብሔር ይህንን ስጦታ ለምስጠት እጁን ዘርግቷል እኛ ስጦታውን መቀበል ይኖርብናል ። እምነት እጅን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ስጦታ የመቀበል ሁኔታ ነው ። ለዚህም ነው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች ሲጽፍ «ጸጋ በእምነት አድኖአችኋል ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ እንጂ ከእናተ አይደለም ያለው ። የእኛ እምነት የእግዚአብሔር ጸጋ ለድህነታችን አስፈላጊ ነው ። በክርስቶስ ስናምን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንቀበላለን ። ምንም ጥፋት እንደሌለበት ጻድቅ ተብለነሰ እንጠራለን ። /ሮሜ 5:1-2/ ። ስለዚ እግዚአብሔር ባለፈው ኃጢአታችን አይቆጣም ። ይልቁኑ ይቅርታውን ሰጥቶን ልጆቹ ያደርገናል ። በክርስቶስ ባመንን ቅጽበት ጻድቅ ሁነን ድኅነታችንን እናገኛልን ። ድህነትን በማግኘታችን የዘላለም ሕይወት እናገኛልን

ስለዚህ ለመዳን በመጀመሪ ጻድቃን መባል አለብን ። ለመጽደቅ በክርስቶስ ማመንን ይኖርብናል ። በክርስቶስ ለማመን ደግሞ በመጀመሪያ የእግዚአብሔር ስጦታ መቀበል አለብን ። እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ጠርቶናል ።/ኤፌ 1:4/ ።ድህነታችን ፣ ጽድቃችን ፣ እምነታችንና መጠራታችን ሁሉ እጅግ ጥልቅ ከሆነ ከእግዚአብሔር ጸጋ የሚመነጩ ናቸው ። ሕግጋቶች ወይም ሰው ሰራሽ ወጎች በመፈጸም ድህነታችንን ለማግኘት አንሞክር ። በሰራነው ስራ ጻድቅ መባል አንችልም እንዲውም በስራችን ጽድቅን ለማግኘት መጣር የክርስቶስ ጸጋን መቃወም ነው ።

በቁ.ር.16 መጨረሻ ላይ ሕግን በመጠበቅ ማንም አይጸድቅም ሲል ተናግሯል ። ይህ ለምን ሆነ ? ምክንያቱም ማንም ሕግን እፈጽማለው የሚል አንዲቷን ግን ባይጠብቅ ሁሉን እንደተላለፈ ይቆጠራል ። /ያዕ 2:10/ ። ከትዕዛዛት ሁሉ ልንጠብቀው የማንችለው አትመኝ የሚለውን ነው ።/ዘጸ 20:17/ ። ከአስርቱ ትዕዛዛት ምናልባት ዘጠኙን እንጠብቅ ይሆነል ። አስረኛውን ግን ሁል ጊዜ መጠበቅ አንችልም ። አትመኝ ማለት ክፉ ምኞት አይኑርህ ማለት ነው ።

ቁ .ር 17. በዚህ ስፍራ ጳውሎስ ለአይሁድ አማኞች ይናገራል ። የአይሁድ ክርስቲያኖች ስጋት ውስጥ የከተታቸው የአይሁድ ሃይማኖትን ወግ ባይከተሉ ኃጢአታቸው የከፋ እንደሆነ በማሰባቸው ነው ። ይህ እውነት ከሆነ በክርስቶስ ማመን ወደ ባሰ ኃጢተኝነት ይመራል ማለት ነው ። በሌላ አነጋገር ክርስቶስ ኃጢአትን ይጨምራል ማለት ነው ። በጳውሎስ አባባል ግን ተቃራኒ እውነት ነው ። በክርስቶስ በማመን ብቻ አለመፈለጋቸው በእግዚአብሔር ፊት ይልቁን ኃጢአተኞች ያደርጋችኋል ቅዱስና ንጹሕ የመሆናቸው ብቸኛ መንገድ እምነትን በክርስቶስ ማድረግ የእርሱን ጽድቅ መቀበል ነወ ።

18. በሕግ መመካት እጅግ ኃጢአተኛ ያደርጋል ። ጳውሎስ የፈረሰውን መልሶ የመገንባት ሐሳብ የለውም ። አያስፈልግም ብሎ የተወዉን ሕግና ወግ እንድ ገና አያነሳም ። እንዲ ካደረገ ግን «የጸጋ ሕግን »ዋጋ ማሳጣቱ ነወ ። ይህም ሰዎች ሁሉ የሚጸድቁበትን የክርስቶስ ስራና መስዕዋት መቃወም ነው ። የክርስቶስን ጽድቅ ትቶ በቃት በሌለው ሕግ ለመጽደቅ መጣር በእግዚአብሔር ፊት እንድ ሕግ ተላላፊ ያስቆጥራል ። ምክንያቱም ሕግን በመጠበቅ ማንም ሊጸድቅ አይችልም ።

19.ሕግ በሰው ላይ ከመፍረድ በቀር ለኃጢአተኛ አዱስ ሕይወትን መስጠት አይችልም ። ሕጉ በጳውሎስ ላይ የሞት ፍርድ ፈርዶበት ነበር ። ጳውሎስ በሕጉ በኩል ለሕግ ሙቼ ነበር ይላል ። ነገር ግን ሲሞት ነጻ ይወጣል ። ዳኛ ፍርድ ከሰጠ በኋላ በጉዳዩ ላይ ስራ አይኖረውም ።በወንጀለኛው ላይ ያለው ስልጣን ያከትማል ። ወንጀለኛው ቅጣቱን በመፈጸም ከዳኛ ነጻ ይሆናል በተመሳሳይ መንገድ ጳውሎስ ለሕግ ስለ ሞተ ከሕግ ነጻ ሆኗል ። ሕግ ጳውሎስ ላይ የሞት ፍርድ ከፈረደበት በኋላ ምንም ሊያደርገው አይችልም ። ጳውሎስ በሞቱ ከጌታው ነጻ እንደወጣ አንደ ባሪያ ነው ።ስለዚህ አሁን ከቀድሞ ጌታው ከሕግ ነጻ በመሆኑ ክርስቶስን ለማገልገል ለእግዚአብሔር ለመኖር ነጻነት አለው ። /ሮሜ 6:7 , 7:4/ ። ክርስቶስ በውስጡ ስለሚኖር ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ኃይል አለው ።

(ቁ.ር 20) ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለው እዚህ ስፍራ ጳውሎስ የሚሰጠው መስክርነት ምንኛ ጥልቅና አስደናቂ ነው። አንድ ሰው አዲስ መንፈሳዊ ሕይወት ከመቀበሉ በፊት መሞት አለበት (ሮሜ 6:6) ከክርስቶስ ጋር መሰቀል የኃጢአተኛው ማንነታችን መሞት ማለት ነው ። የዚህ ጊዜ የክርስቶስ ሕይወትና ባሕርይ በውስጣችን ይሞላል የእርሱ መንፈስ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ውስጣችን ይገባል ። በመንፈስ ቅዱስም ቅድስናና የጽድቅ ሕይወት ለመኖር ኃይልን እናገኛለን በሕይወት የሚኖረው የቀድሞው ኦእኛነታችን ሳይሆን ክርስቶስ ነው ። የቀድሞው ኃጢአተኛ ማንነታችን ሞቷል ።

እስኪ ራሳችንን ይህን ጥያቄ እንጠይቅ ። በእኔ ውስጥ የሚኖረው ማነው ? የድሮ ማንነቴ ውይስ ክርስቶስ ?

የክርስትና ሕይወት እውነተኛው ትርጉም ክርስቶስ በአማኙ ሕይወት ውስጥ መኖሩ ነው ። በገዛ ፍቃዳችን ሕይወታችንን መኖር የለብንም ። በእምነት ክርስቶስ በውስጣችን እንዲኖር እንፈቅዳለን "ኢየሱስ በኔ ኑሩ እኔም በእናተ እኖራለውና ብሏል " ።/ዮሐንስ 15:4/ ሰለዚህ ኢየሱስ በእኛ ውስጥ ስለሚኖር እንደ ኢየሱስ መኖር እንጀምራለን ። የዚያን ጊዜ ሌሎች ሰዎች ክርስቶስን በእኛ ውስጥ አይተው እነርሱም ክርስቲያኖች ለመሆን ይፈልጋሉ ።

(21) ጳውሎስ " የእግዚአብሔር ጸጋ አልጥልም " ይላል ። ይህም ማለት እንደ ገና ድኅነትን ሕግ በመፈጸም ለማግኘት አልሞክርም ማለት ነው ። ሰው በክርስቶስ በማመን ሳይሆን ሕግን በመፈጸም የሚያድን ከሆነ በእርግጥ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው ።