Get Mystery Box with random crypto!

ፎሮፎር |Seborrheic dermatitis ፎሮፎር ምንድነው? ፎሮፎር እየተመላለሰ ለረዥም ጊ | ሄሎ ዶክተር 👂👂👂🏥

ፎሮፎር |Seborrheic dermatitis

ፎሮፎር ምንድነው?

ፎሮፎር እየተመላለሰ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ከሰው ወደ ሰው የማይተላለፍ የቆዳ ህመም አይነት ነው። ፎሮፎር በባህሪው ጠንካራ ያልሆነ ብዙም ምልክት የሌለው እና ትንንሽ ብናኞች ያሉት ሊሆን ይችላል፤ይህ የተለመደው አይነት ፎሮፎር ሲሆን ዳንድረፍ (dandruff) በመባል ይታወቃል።

በተቃራኒው ደግሞ ጠንካራ የሚባለው የፎረፎር አይነት አብዛኛውን የራስ ቆዳችንን እንዲሁም ሌሎች የአካል ክፍሎቻችን ላይ ጭምር ሊከሰት ይችላል፤ ቅርፊቶቹም ወፍራም እና ከራስ ቆዳችን ጋር የተጣበቁ ሊሆኑ ይችላሉ

ፎሮፎር ምን አይነት ሰዎች ላይ ይከሰታል?

- ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ አመት ባሉ ህጻናት እና ከጉርምስና እድሜ በላይ በሆኑ ግለሰቦች ላይ ይከሰታል
- አብዛኞቹ ፎሮፎር የሚኖርባቸው ግለሰቦች ሌላ ተጓዳኝ ህመም አይኖራቸውም አንዳንድ ጊዜ ግን ከHIV ፣ Parkinson ፣ የሚጥል ህመም (Epilepsy) ፣ ጭንቀት ገር ተያይዞ ሊከሰት ይችላል

ፎሮፎር መንስኤው ምንድነው?

-የፎሮፎር መንስኤ በትክክል ይሄ ነው ተብሎ መናገር ባይቻልም ከቆዳችን ጋር ተስማምተው በሚኖሩ (normal flora) የፈንገስ አይነት (Malassezia) ምክንያት ይከሰታል ተብሎ ይታሰባል

-ፎሮፎር ወዝ አመንጪ እጢዎች (Sebaceous glands) ተከማችተው በሚገኙበት የአካል ክፍሎቻችን (የራስ ቆዳ ፣ ፊት፣ ደረት አካባቢ፣ የላይኛው የጀርባችን ክፍል ፣ የውጭኛው የጆሮ ክፍል ፣ ብብት ፣ ጡት ስር ፣ በላይኛው የጭን ክፍል እና ብልት መሀከል በሚገኘው ቦታ) ላይ ይከሰታል

ፎሮፎር እንዴት ይታከማል ?

- መድሀኒትነት ያላቸው መታጠቢያ ሻምፖዎችን (ketoconazole 2%, Selenium sulfied, Ciclopirox , Zinc pyrithione) በመጠቀም ፎሮፎርን መቆጣጠር ይቻላል።
- ሻምፖውን ተቀብተን ከ5-10 ደቂቃ አቆይተን መታጠብ ይህንንም በሳምንት ከ 2-3 ጊዜ መደጋገም ያስፈልጋል
- ከዚህ በተጨማሪ የማሳከክ ስሜት ካለው፣ጠንካራ የሚባለው የፎሮፎር አይነት ከሆነ፣ከራስ ቆዳችን ውጪ ከተከሰተ፣ተጓዳኝ ህመሞች ካሉ እንዲሁም ህጻናት ላይ ከተከሰተ የቆዳ ሐኪም በሚያዘው መሰረት ተጨማሪ መድሀኒቶች ያስፈልጋሉ።

ፎሮፎር ለምን ይመላለሳል?

መንስኤው በትክክል ስለማይታወቅ እና ምክንያት ነው ተብሎ የሚታሰበው የፈንገስ አይነት ከቆዳችን ጋር ተስማምቶ የሚኖር በመሆኑ ፎሮፎርን በህክምና ማዳን አይቻልም(not curable) ለዚህም ነው የሚመላለሰው ፤ ነገር ግን ምልክቶቹን መቆጣጠር እና የሚመላለስበትን የጊዜ ፍጥነት መቀነስ ይቻላል

ፎሮፎር እንዳይመላለስብን ምን እናድርግ?

ከላይ በተጠቀሰው መሠረት ምልክቶቹ እስኪጠፉ በሻምፖ መታጠብ ያስፈልጋል(የቆዳ ሐኪሙ ተጨማሪ መድሀኒቶችን ሊያዝ ይችላል)፤ ምልክቶቹ ከጠፉ በኋላ ሻምፖውን በሳምንት አንድ ጊዜ ወይም በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ መጠቀም ፎሮፎር እንዳይመላለስ ይረዳል

ፎሮፎር ፀጉር እንዲነቃቀል ያደርጋል?

በፎሮፎር ምክንያት የፀጉር መነቃቀል የተለመደ አይደለም ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ የማሳከክ ስሜት ካለ ጊዜያዊ የሆነና ተመልሶ የሚተካ የፀጉር መነቃቀል ሊያስከትል ይችላል

በመጨረሻም የቆዳ ሐኪም ሳያማክሩ መድሀኒቶችን ባለመጠቀም ቆዳዎን ከተጨማሪ ጉዳት ይጠብቁ