Get Mystery Box with random crypto!

እኛ እኛ እኮ መሬት ሊያበቅል....አሳርሶን ዝናብ ከላይ....አረስርሶን ለ.ም.ነ.ት.ን....ሰ | አብርሃም ፍቅሬ (የቅዳስ ልጅ)

እኛ

እኛ እኮ

መሬት ሊያበቅል....አሳርሶን
ዝናብ ከላይ....አረስርሶን
ለ.ም.ነ.ት.ን....ሰጥቶ አውርሶን
የተፈጥሮ....ካባ አልብሶን
የምንፋጅ....ጥጋብ ወርሶን

አይ እኛ

እኛ እኮ


ሰበዝ መዘን....መሶብ ሰፍተን
በምጣዱ....እንጀራ አስፍተን
እየበላን....ላንቋደስ
በሞት ማልደን....ላንጓረስ
የቀለለን....ደም መፋሰስ

አይ እኛ

እኛ እኮ


በአዲስ ዓመት....በአዲስ መንፈስ
ጊዜ ሰጥቶን....ለመታደስ
አበባ አየሁ....ለምለም ሳንል
እንቁጣጣሽ....ሳንዘምር
ጥቅምት እሸት....ሳንከምር

ተዘንግቶን
በክፉ ዐይን የሎስ ዓይቶን

ከአዲስ ዘመን....ላደረሰን
አዲስ ጀንበር....ላወረሰን
ብርሃን ፀጋ....ላለበሰን
ምስጋናችን....ሰማይ ሳይደርስ
የምንፋጅ....በእብሪት ደንደስ

እይ እኛ

እኛ እኮ


በደብሩ....በመቅደሱ
ምስጢራትን....የዳሰሱ
የሼህ ዱአ....በመስጊዱ
ከአምላካቸው....የማለዱ
ከአባቶች....እምነት ወርሰን
በፀበሉ....ተፈውሰን
በዘምዘሙ....ሽረት ይዘን
መቆም ስንችል....አድረን አንሰን
አንሰን...
አንሰን...
አንሰን...
አንሰን...
ድህነት...ማቅ...ያለበሰን
የአረር...ጥይት...የጠበሰን

አይ እኛ

እኛ እኮ


በአበባ....ምድር ቀልማ
በቢጫ አደይ....ተሸልማ
እዩኝ. እዩኝ. እዩኝ....ስትል
ቂም በቀልን....የምንፈትል
በልብ ይዘን....የክፋት ትል
ስንባዝን....ስንባትል

አይ እኛ

እኛ እኮ


ቄጠማችን....ከመስክ በቅሎ
የምናጭድ....ሙጃ ሰርዶ
ቅዠታችን....ባህር ማዶ
ሽንቁር ጋኖች....ሁሌም ባዶ
''ለምን?''....ብለን 'ማይሰማን
"እንዴት?" ማለት....የማይቀናን
የንፋስ ውል....ያበጃጀን
የአመል እሳት.....የሚፈጀን

አይ እኛ

እኛ


በመሳቂያ....ከንፈር ነክሰን
በማያችን....ዕንባ አፍስሰን
ላንራመድ....ሁሌ አንክሰን
በእጃችን....ተተኳኩሰን
ላናሸንፍ....ላንሸነፍ
መገፋፋት....መኮራረፍ
መጠላላት....መጠላለፍ
በሞት ተራ....ልንሰለፍ

አይ እኛ

ኖርናት መቼም
...

ክፉ አንቀልባ....እየሰፋን
ማሪያምዬን....እንዳስከፋን
ለሞታችን....ጦርን ቀርፀን
አላህዬን....ሳንማፀን
እየሱሴን....ሳንለምንም
አፈር ገባን....እንደ ምንም

አ........ይ እ..........ኛ

አብርሃም ፍቅሬ
(የቅዳስ ልጅ)

ለዚህ ግጥም ፅሁፍ መነሳሻ እንዲሁም በፅሁፉ መጨረሻ ያሉ ለአንዳንድ ሀረጋት ጭማሪ የሆነኝ የ አስታወሰኝ ረጋሳ "እኛ እኮ" የሚል አንድ የመድረክ ስራ ነው።እናም ምስጋናውን ባለበት

@HAKiKA1
@HAKiKA1