2022-07-03 10:21:52
#የፀጋዬ ወንድወሰን (ጋዜጠኛ) የጉዞ ማስታወሻ
ዛሬ ሰኔ 26 የክረምት ወቅት በይፋ ገብቷል ፤ ወቅቱ እስከመስከረም 25 ይቆያል ። በኢትዮጵያ የቀን ቀመር መሰረት ።
ክረምት ሲገባ ደርሶ የሚታየኝ መስቀል ነዉ፤ የመስቀል በዓል በጉራጌ ።
ፈጣሪ ይመስገን ኑሮም ከመናሩ ዘይትም ከመወደዱ በፊት ነዉ ባለፈዉ አመት በጉራጌ ዞን የመገኘቱ እድል የገጠመኝ እናም በዚያ የአመት በጀቴን የዘጋሁት ።
እንደአሁኑ የኑሮ ግለት የአመት ያልኩት በጀት ብዙ አመታታን ያሻግረኛል ፤ ያስቀረሁትን ቪዲዮ ስንቅ ማድረጌም አይቀርም።
እኔና ጓደኞቼ አዲስ አበባ ስንበላ የቆየነዉ ስጋ የቀመስነዉም ቅቤ High Copy መሆኑን ያረጋገጥነዉ ጉራጌ እንደደረስን ነዉ ።
ስጋን በአይነቱ በላነዉ ፣ ቅቤም ጠጣነዉ ብል ማጋነን አይሆንም ።
ልክ እግራችን እዚያ ዉብ ጎጆ በደረሰ ጊዜ የአዲስ አበባን የምግብ High copy በአታካና ነዉ መበቀል የጀመርነዉ ።
ጣዕሙ ዛሬም ድረስ ከምላሴ ስላልጠፋ ፆም እንዳያስፈታኝ ደጋግሜ እሰጋለሁ
አታካና - አይብ እና ቅቤ ጋብቻ ፈፅመዉ ጎጇቸዉን በአፍና ምላስና ጥርሳችሁ ቀልሰዉ ማደሪያን ጨጓራችሁ ላይ አድርገዉ ፈልሰስ ለማለት ከጣባዉ ላይ በጉጉት የሚጠብቋችሁ የምግብ አይነት ነዉ።
አሰራሩ'ን ትንሽ ለማስረዳት ያህል :- //ከኑሮ ዉድነቱ አንፃር ስለማይቻል ትቼዋለሁ //
ከአታካናዉ በኋላ ግን - እርጎዉ ይመጣል ...ሳ....አብ ታደርጉታላችሁ አቤት ቅዝቃዜ ፣ ጨጓራችሁን ይበርደዋል እንደእኛ በአዲስአበባ በስጨት ብላችሁ ከሄዳችሁ '' ችስስ '' ሲል ይሰማችኋል
/ ኡፏ ጠገብኩ ስትሉ ደሞ መሸት ሲል ጥብሱ ይመጣል ከዚያ ክትፎዉ ከነቆጮዉ በኮባ ቅጠል ተዉቦ / ...
ከዛ መነጫነጭ ትጀምራላችሁ " እንዴ ይሄ መጀመሪያ ፣ ኧረ ይሄ ይቅደም እያላችሁ ግራ እጃችሁ ከቀኝ እጃችሁ ጋር ጠብ ይገጥማል / ማን ይገላግል?
ወደቀልባችሁ ትመለሱና .... ድጋሚ ስለማይገኝ ሆድን እያሹ መብላት ነዉ ።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ደሞ ነገን ስለምንፈራ አጋጣሚዎችን ደህና አደርገን መጠቀም እናዉቅበታለን።
አንዱ ይነሳና '' የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም ፣ ትምህርቱን ተምረሀል ምግቡ ይቀርሀል ያዝ ብሎ የወኔ ወኔ ይሰጣችኋል ''
ያኔ አገጫችንን ወለም ካላለን መብላት አናቆምም ።
ከዚያ ደግሞ አለ ጨዋታዉ ሳቁ ፣ ምርቃቱ ....ብዙ ብዙ ነገሮቹ አካባቢዉ መብራት ያልገባለት ቢሆንም የገባንበት ቤተሰብ ፍቅር ዳተኛዉን መብራት ሀይል ያስረሳናል ።
ግን ለአዲስ አበባ ቅርብ የሆነችዉን ዞን መብራት እንዴት እስካሁን ሳይገባ ቀረ ? የተወሰኑ ቦታዎች ላይ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም ደካማ መሆኑን ግን ታዝቤያለሁ ። ብቻ እኛ ሶስት ቀናትን እንደዚህ ቆይተናል ።
በርካታ ገጠራማ አካባቢዎችን ስመለከት ልጅ ሳለን በየመንደሩ የነበሩ ትልልቅ እናቶችን ያስታዉሱኛል ።
ህፃን ፣ ወጣት ፣ አዛዉንቱ ሁሉ እንደነዚያ ለልጅነቴ ድምቀት እንደሆኑት እናቶች ያሉ ናቸዉ ፤ ፍቅር ናቸዉ ። ፍቅር መግለጫዉ ብዙም አይደል እነርሱም እንደዚያዉ ።
ወደአለም ቀረብኩ ያለችዉ አዲስአበባ ግን እነዚያን እናቶች ደብቃብናለች ወይም ጠልተዋት በየገጠሩ የሄዱ አይነት ስሜት ይሰማኛል።
አሁን ክረምት ገብቷልና ፣ መስቀል በጉራጌ መናፈቅ ይዣለሁ ። ዘንድሮ ወደጉራጌ ምድር ብሄድም ባልሄድም በዓሉ ግን ድቅን ይልብኛል ። በሌላ ምልከታዬ እስክመለስ ኬር እንዲሉ የጉራጌ እናትና አባቶች ለሁሉም ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን ።
-----------------
#የበለጠ መረጃ ለማግኘት
Telegram;- https://t.me/gurageZ
YouTube;- https://youtube.com/channelUCspMeuO6nhHHOHZpVA1ZSSQ
Facebook;- www.facebook.com/Zebidar-Tube-100279201799689/
tiktok;- tiktok.com/@zebedir
642 viewsZebidar Tube (ዘቢዳር), 07:21