Get Mystery Box with random crypto!

ባገሬ ሰማይ ስር . . የሚሆነው ቀርቶ የማይሆነው ሆነ፣ ሰው ለራሱ ቀርቶ ለንዋይ ታመነ። እልፍ አ | ግጥም እና ጥቅሶች

ባገሬ ሰማይ ስር
.
.
የሚሆነው ቀርቶ የማይሆነው ሆነ፣
ሰው ለራሱ ቀርቶ ለንዋይ ታመነ።
እልፍ አዕላፍ ጩኸት፣
እልፍ አዕላፍ ብሶት፣
ክፋት የወለደው የህሊና ዝቅጠት።
.
ባገሬ ሰማይ ስር
.
ተስፋን የቆረጠ የባከነ ወጣት፣
ስክነት የተለየው ዉል አልባ ማንነት፣
በአሉባልታ ወሬ ልቡ ተመርዞ፣
ማሞቅ የሚቀናው የነገር ጫፍ ይዞ፣
ስሜቱ የሚነዳው በሱሱ ደንዝዞ።
.
ባገሬ ሰማይ ስር
.
ሳቅን የናፈቁ የሚያነቡ እናቶች፣
የሚያቅፉት ያጡ ጨቅላ ህፃናቶች፣
በየሰርጡ ያሉ የጊዜ ቀማኞች፣
ዘርፈው የሚያድሩ የከበሩ ሌቦች።
.
ባገሬ ሰማይ ስር
.
ደሞ በዚኛዉ ፅንፍ፣
ደሞ በሌላው ጫፍ፣
.
ራሱን አዋርዶ ሀገሩን ያልጣለ፣
ክብሯን ያስከበረ አንዳንድ ሰው አለ።
.
ተሰቅላ ሲያያት ዉቢቷን ባንዲራ፣
እንባው የሚቀድመው ጸዳሏ ሲበራ፣
ደምስሶ የሚጥል የሙስናን ደባ፣
ጀግንነት በዉስጡ በደሙ የተጣባ።
.
ይህ ሁሉ ባገሬ ሲሆን እየታየ፣
እንክርዳድ ከስንዴ ፍፁም አልተለየ።
.
ራሱን ክዶ ለንዋይ የታመነዉም፣
ራሱን ጥሎ ክብሯን ያስከበረዉም፣
አብበዉ የተወለዱ የማህፀኗ ፍሬዎች።
የኢትዮጵያ ምድር ሁለት ገፅታዎች።
.
እናም ሀገሬ ሆይ!
.
የወላድ መካን እንዳትሆኚ ብርቱ ብርቱዉን ወለጂ፣፣
በልጆችሽ ክንድ ብርታት መቃረንን አስወግጂ፣
የብርሃን ቀንዲል ሆነሽ ለዘለዓለም አብሪ፣
በፍቅርሽ መሬት ላይ መፋቀርን ዝሪ።

10/03/15
በኤደን ታደሰ እንደተፃፈ(@ediwub)
@topazionnn
@gtem_na_tks
@gtem_na_tks
@gtem_na_tks