Get Mystery Box with random crypto!

የመስሩር እና የመቅሩር ታሪክ ~ ክፍል አስራ ሰባት የሙታን ከየመቃብሮቻቸው መነሳት ምድር በ | ወርቃማ ንግግሮች

የመስሩር እና የመቅሩር ታሪክ

~ ክፍል አስራ ሰባት

የሙታን ከየመቃብሮቻቸው መነሳት


ምድር በልቧና በሆዷ ያስቀመጠቻቸውን ሁሉ ከየማዕዘናቱ የምድር ከርስ የወጡ ሙታን ሁሉ ዳግም ህያው ሆነው ተቀሰቀሱ ከዚህ በኋላ ነፍሶች ከአካሎቻቸው ጋር በፍጹም አይለያዩም። ለብዙ ዘመናት ተቋርጦና የተረሳሳ መስሎ የነበረው የአካልና የህሊና ግንኙነት ድሮ እንደነበረው ያለምንም እንከን እንዲቀጥል ተደርጓል። ይህ ማለት ሰውየው ሲሞት አብሮት የነበረው ህሊናው የማስታወስ ችሎታው፣ ትዝታው ሁሉም ነገሩ እነደገና ተመልሶለታል ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ እርቃኑን በባዶ እግሩና
አቧራ እንደለበሰ ከተኛበት ቦታ ተነሣ።


በዚህ ሁኔታ መስሩር ከሞተበት የመቃብር ስፍራ ሲቀሰቀስ መቅሩርን ከጐኑ ቆሞ ተመለከተው፡፡ መስሩርም በማመናጨቅ መልክ አንተ ማን ነህ? እዚህስ ምን ታደርጋለህ? በማለት ጠየቀው። መቅሩርም የፈጣሪ ያለህ ሞተን አልነበረም እንዴ? አለ የመቅሩር ቃላት መስሩርን ድንገተኛ በሆነ ፍርሃት ናጠው፡፡


ከዚያም መስሩር ፍርሃቱን መደበቅ እያቃተው ፊትህን ሳስተውለው ከዚህ በፊት የማውቅህና አዲስ አልመስልህ አለኝ። አንድ ጊዜ በክህደት ወንጀል ከሰንህ ነበር ልበል? አለ።


መቅሩርም ሲመልስ ልክ ነው በአንድ ወቅት በክህደት ወንጅላችሁኝ ነበር። ያ የተመሰረተብኝ ክስ ምክንያት ይኸው አሁን የምናየውን ከሞት በኋላ ስለመቀስቀስ ማመኔ ነበር” አለው፡፡


መስሩር በድንገት ሁኔታው ተለወጠ ከዚያም ኩራት በተላበሰ መንፈስ አንተ ሞኝ እንከፍ! አንተ እንደምትለው ሳይሆን እስካሁን የሚያስጠላ ህልም ውስጥ ነበርን። አሁን ገና መንቃታችን ነው የታለ የሌሊት ዘበኞቹ አለቃ? የደኅንነት ኃላፊውስ የት ነው? ይልጀመር።


መስሩር ይህን ከተናገረ በኋላ አቅሉን ሰብሰብ አድርጐ ስለ መቅሩር ሁኔታ ማሰብ ጀመረ። መቅሩር አሁን እየተናገረው ያለው ነገር ምናልባትም እውነት ሊሆን ይችላል። እውነትም ሞተው የነበረ መሆኑ ሀቅ ይሆናል እርሱ እንደሚያስበው የሚያስጠላ። ህልም ላይሆን ይችላልኮ ደግሞም ባይሞቱ ኖሮ ራቁታቸውን አይቆሙም ነበር።


አሁን ሁኔታውን ሲያስበው ያ እንግዳ የሆነ ፍጡር ለሁለም የሰው ዘር የማይቀር ነው እያለ እንዲጐነጭ የሰጠውን የሞት ጽዋ ቅዥት ወይም የሚያስጠላ ህልም ነበር ለማለት እንዳማይቻል ተገነዘበ። ከሁሉም በላይ በመቃብር ውስጥ ያጋጠመው በቃላት የማይገለጽ ስቃይ ህልም እንዳልሆነ እርግጥ ነው፣ ሁኔታውን አሁን እያገጣጠመ በአእምሮው ሲመረምረው እንደተባለው ሞቶ እንደነበርና አሁን ደግሞ ከመቃብሩ መቀስቀሱን ማመን ጀምሯል።


ይህ ሃሳብ እውነት መሆኑ ከፍተኛ የፍርሃት ዝንቅ ውስጥ ከተተው መስሩር ስለመቅሩር ጉዳይ ሲያስብ በቅጽበት የመፀፀት ስሜት ወረረው አሁን ሲያስታውሰው ይህን መሣይ ምስኪን ሰው አደጋና ሴራ ደቅኖብኛል ብሎ ማመኑ ምንኛ የማይመስል ነገር ነበር! እንዴትስ የሞት ቅጣት እንዲወሰንበት ተደረገ? በመቅሩር ላይ የተወሰነው የሞት ቅጣት በችኰላ የተፈፀመ መሆኑን ቢያምንም በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የደኅንነት ኃላፊው ያቀረቡትን ሪፖርት በመፃረር የሰውየው ንፁህነት መቀበል ደግሞ በጊዜው ከባድ እንደነበር አስታወሰ


አሁን መስሩር በደመነፍስ ወደ አንድ አቅጣጫ እየተጓዘ መሆኑን ልብ አለ። ዙሪያውን ሲያማትር በሺዎች የሚቆጠሩ ሙታን እንደርሱ ራቁታቸውን እየተግተለተሉ ወደ መሰብሰቢያው ምድር እያመሩ ነው። መስሩር ራሱን እንዲህ እያለ ይጠይቅ ነበር “እንዲህ እየተጣደፍኩ ወዴት ነው የምጓዘው? ማንስ ነው የቀሰቀሰኝ? ልብሶቼ የታሉ ቤተ መንግስቴስ የት አለ? አገልጋዮቹና ወታዶሮቼስ? ለመሆኑ ከሞት እንድነሳ ትእዛዝ የሰጠው ማን ነው? እግሮቼ እንዲንቀሳቀሱ ያደረገው ማን ነው? ጠቅላላ ስልጣኔና ክብሬን ማን ወሰደብኝ?


መስሩር አሁን መላ ቅጡን ባልለየው ምስጢራዊ ሁኔታ እንደተወጠረ ባለበት ሁኔታ ሁለት እንግዳ የሆኑ ፍጥረታት አብረውት እየተጓዙ እንደሆነ አስተዋለ
ከሁለቱ አንደኛው ከፊት ለፊቱ ሆኖ ያለምንም ድምፅ እየመራ ወደ አንድ አቅጣጫ እየወሰደው ሲሆን ሌላው ደግሞ ከኋላው ሆኖ እየተጠባበቀው ይጓዛል። ሁኔታቸውን ሲያጤነው ልክ እንደ በከባድ ወንጀል ተከሶ የተፈረደበት ሰው በሚጠበቅበት አኳኋን ነው በጥብቅ አጅበውት የሚሄዱት። መስሩር አሁን ያረጋገጠው ሀቅ እንደፈለገና በመረጠው ሁኔታ መጓዝ እንደማይችል ብቻ ሳይሆን ማምጫ በሌለው ሁኔታ በቁጥጥር ስር የወደቀ መሆኑንም ጭምር ነው……

ይቀጥላል