Get Mystery Box with random crypto!

Shaday

የቴሌግራም ቻናል አርማ godshaday — Shaday S
የቴሌግራም ቻናል አርማ godshaday — Shaday
የሰርጥ አድራሻ: @godshaday
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 3.56K
የሰርጥ መግለጫ

https://youtube.com/channel/UCrUVrlQb09LzTVYU05rnaSA
የተወደዳችሁ በዚህ ቻናል ዝማሬዎቻችሁን፣ ስብከታችሁን፣ግጥሞችና ጹሁፍ በዚህ አድርሱን አብረን እናገልግል

@Chere2013
@Abrham2013
ይህ በውስጣቸው የመዘመር የመስበክ እንዲሁም የተለያዩ የፀጋ ስጦታ ያላቸው ግን እድሉን ና ቦታ ላላገኙ ማገልገል ለሚፈልጉ ሁሉ ክፍት ነው
የጌታን ስራ አብርን እንስራ

Ratings & Reviews

4.50

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

1

4 stars

1

3 stars

0

2 stars

0

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች

2022-09-01 06:40:07 . Shaday DEVOTION
ⒺⓅⒽⒾⓈⒾⒶⓃⓈ

(ቀን #20)
ለዲያብሎስ ስፍራ አትስጡት!
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ኤፌሶን 4:25-27
"ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ ሁላችንም የአንድ አካል ብልቶች ነንና። ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ፤ በቍጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት።"
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

ሐዋርያው ጳውሎስ በቁ.25 ላይ "ስለዚህ" ሲል አሮጌውን ሰው አውልቃችሁ አዲሱን ሰው ከለበሳችሁ ወይም ስለለበሳችሁ የሚለውን ሀሳብ ለማመልከት ሲሆን፤ በመቀጠልም አዲሱን ሰው የለበሰ ሰው እንዴት መመላለስ እንዳለበት ያስተምራል።

በመጀመሪያ ግን "በክርስቶስ ትምህርት" የተለወጠ ሰው፤ ከሌሎች ባልንጀሮቹ ጋር የአንዱ አካል ብልት እንደሆነ ይገልጻል። ይህን ማስታወስ ያስፈለገበት ዓላማ፤ የአንድ አካል ብልት እንደመሆናችን መጠን አንደኛችን የምናደርገው ነገር ወደድንም ጠላንም በሌላኛችንን ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ነው።

በዚህ ክፍል አውድ መሠረት አዲሱን ሰው የለበሰ ሰው ሁለት ተግባራዊ ልምምድ ተገልጿል። እነርሱም፦

1. ውሸትን ያስወግዳል!

ውሸት ማለት ሆነ ብለን ከእውነታው ጋር ተቃራኒ የሆነን መረጃ ሌሎች ሰዎች እንደ እውነት እንዲቀበሉት መናገር ማለት ነው። ስለዚህ አዲሱን ሰው የለበሰ ሰው ውሸትን አስወግዶ፣ እውነትን በመነጋገር አካሉን ይገነባል እንጂ ውሸትን አይለማመድም። ልብ እናድርግ በመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር የቀጣው የመጀመሪያው ሀጢያት - የውሸትን ሀጢያት ነበር (ሐዋ 5:1-11)

ስለዚህ "ውሸት ትንሽ ሀጢያት ነው" የሚለውን የተለምዶ አባባል ተከትሎ እራስን ለውሸት ማመቻመች መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም። የጌታ ትዕዛዝ በአጭሩ ውሸትን አስወግዱ፤ እውነትን ተነጋገሩ ነው!

2. በቁጣው ላይ ፀሀይ አይገባም!

ቁጣ ትክክል ባልሆነና ደስታችንን በሚነጥቅ ነገር የሚቀሰቀስ ተፈጥሮአዊ ስሜት ነው። መቆጣት ተፈጥሮአዊ ስሜት ስለሆነ በራሱ ሀጢያት አይደለም። እንኳን እኛ ሀጢያተኞቹ፤ ፍጹም ጻድቁ እና ቅዱሱ እግዚአብሔር እንኳን ይቆጣል። ነገር ግን እኛ ሰዎች ስሜታችን በሀጢያት የተበከለ፤ እውቀታችንም ውስን ስለሆነ ልክ እንደ እግዚአብሔር ፍጹም ትክክል /ቅዱስ/ የሆነን ቁጣ (Justified/Holy Anger) መቆጣት አንችልም። ስለዚህ የቁጣ ስሜታችን በተሳሳተ ግንዛቤ ወይም መረጃ ላይ ሊመሰረት ስለሚችል እና ቁጣችንም ወደ ቂም፣ በቀል፣ ክፋት እና መራርነት ሊቀየር ስለሚችል መግራት የግድ ነው። ካልሆነ ግን በቁጣችን ሀጢያትን እንሠራለን!

መቼስ በቁጣችን ፀሀይ የማይገባው ላስቆጣን ነገር ወዲያው መፍትሔ ስናበጅለት ስለሆነ፤ ማሰላሰሉን በመተው፣ ፊት ለፊት እውነትን በመነጋገር፣ ስለጉዳዩ በመፀለይ ወይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ካልፈታነው ሰይጣን ቁጣችንን ወደ ቂም፣ በቀል፣ ክፋት፣ መራርነት እንዲለውጠው እድል ፈንታ እንሰጠዋለን።

በአጠቃላይ "አዲሱን ሰው" የለበሰ ሰው፤ ውሸትን አስወግዶ እውነትን በመነጋገር እና ቁጣውን ገርቶ ሀጢያትን ባለማድረግ፤ ሰይጣን አካሉን (ቤተክርስቲያንን) የሚያጠቃበት ስፍራ (foothold) ያሳጣዋል።

ዛሬ የማሰላስለው የቃሉ እውነት፦ ውሸት እና ያልተገራ ቁጣ ከእኔ አይጠበቅም!

የዛሬው ፀሎት፦ እግዚአብሔር ሆይ ውሸትን ባለማስወገድ እና ቁጣዬን ባለመግራት ለዲያብሎስ ስፍራ እንዳልሰጥ እርዳኝ!

ነገ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ!!

ፈይሳ መገርሣ
@Godshaday
168 views03:40
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-31 08:15:44 . Shaday DEVOTION
ⒺⓅⒽⒾⓈⒾⒶⓃⓈ

(ቀን #19)
የክርስቶስ ትምህርት
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ኤፌሶን 4:20-24
"እናንተ ግን ክርስቶስን ያወቃችሁት እንደዚህ ባለ መንገድ አይደለም፤ በርግጥ ስለ እርሱ ሰምታችኋል፤ በኢየሱስም እንዳለው እውነት በእርሱ ተምራችኋል። ቀድሞ ስለ ነበራችሁበት ሕይወትም፣ በሚያታልል ምኞቱ የጎደፈውን አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤ ደግሞም በአእምሮአችሁ መንፈስ እንድትታደሱ፣ እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው።"
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

ሐዋርያው ጳውሎስ "እናንተ ግን ክርስቶስን ያወቃችሁት እንደዚህ ባለ መንገድ አይደለም" ሲል፤ ልቦናቸው (Understanding) የጨለመ፣ ህሊናቸው ደንዝዞ እንዳሻቸው የሚኖሩ እና የዘላለም ሕይወት የሌላቸው አህዛብ ባላቸው አስተሳሰብ እና በሚለማመዱት የኑሮ ዘይቤ አይደለም ማለቱ ነው።

በዚህ ክፍል፤ "ማወቅ" የሚለው ሀሳብ አዕምሮአዊ እውቀት (Intellectual knowledge) ሳይሆን ተሞክሮአዊ እውቀትን (Experiential Knowledge) ነው። ታዲያ ክርስቶስን በዚህ መልክ እንዴት ነው ያወቅነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ፦ ኢየሱስን ሰምተን፤ በእርሱም ተምረን ነው!

ኢየሱስ ያስተማረን፣ እኛም የሰማነው፣ እርሱንም ወደማወቅ ያደረሰን እውነት (ወይም የክርስቶስ ትምህርት ጭብጥ) ምን ነበር? የሚል ጥያቄ ሊኖረን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ የትምህርቱ ጭብጥ ሁለት ነው ይለናል። ይህም፦

1. አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ ጣሉት!

አሮጌው ሰውነት በሚያታልል ምኞት የጎደፈ (corrupted) እና ከመዳን በፊት በነበረ የሕይወት ልምምድ ወይም አካሔድ የተሞላ ነው። ዓላማውም ለባሹን በማታለል የምኞቱ ባርያ ማድረግ ነው። ታዲያ የጌታችን ትምህርት አንድ - እርሱን ተዉት! አውልቁት ነው!

2. አዲሱን ሰው ልበሱት!

አዲሱ ሰውነት እውነተኛ በሆነ ጽድቅ እና ቅድስና የተሰራ ሲሆን ከመዳን በኋላ ያለ ሕይወት ነው። ዓላማውም ለባሹ በአእምሮው መንፈስ እየታደሰ እግዚአብሔርን እንዲመስል ማድረግ ነው። ታዲያ የጌታችን ትምህርት ሁለት  - እርሱን ልበሱት ነው!

ምናልባት አንዳንድ ሰው አውልቁ የተባለውን እየለበሰ፤ ልበሱ የተባለውን እያወለቀ፤ ሕይወቱም በተቃርኖ ተሞልቶ ክርስቶስን ማወቅ እችላለሁ ብሎ ያስብ ይሆናል። ከላይ ለማየት እንደሞከርነው፤ እንደ አህዛብ ማሰብ እና መኖር ክርስቶስን የማወቅያ መንገድ ስላልሆነ፤ እንኳን ቀያይረን፤ ሁለቱንም በአንድ ላይ ብንለብስ እንኳን ጌታን የማወቅ ዋስትና የለንም!

እንደ እግዚአብሔር ቃል ክርስቶስን የማወቅያ ብቸኛ መንገዱ ትምህርቱን እንደወረደ መከተል ነው። የእርሱ ትምህርት ባጭሩ "አሮጌውን ሰው አውልቁት እና አዲሱን ሰው ልበሱት" ነው። ጌታ ይርዳን፤ አሜን!

ጌታ ቢፈቅድ እና ብንኖር ደግሞ በሚቀጥሉት ሦስት ጥናቶች ውስጥ "አሮጌውን ሰው አውልቆ አዲሱን ሰው" የለበሰ ሰው ተግባራዊ የሕይወት ልምምድ ወይም አኗኗር ዘይቤ ምን እንደሚመስል እንመለከታለን።


ዛሬ የማሰላስለው የቃሉ እውነት፦ የክርስቶስ ትምህርት (አሮጌውን ሰው ማውለቅ እና አዲሱን ሰው መልበስ)

የዛሬ ፀሎት፦ ጌታ ሆይ ዕለት ዕለት አሮጌውን ሰው እያወለቅሁ፤ አዱሱን ሰው እንድለብስ ጸጋ ይብዛልኝ!

ነገ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ!!

ፈይሳ መገርሣ
@Godshaday
210 views05:15
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-30 08:25:48 . Shaday DEVOTION
ⒺⓅⒽⒾⓈⒾⒶⓃⓈ

(ቀን #18)
እንደ አህዛብ አትመላለሱ!
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ኤፌሶን 4:17-19
"ስለዚህ ይህን እነግራችኋለሁ፤ በጌታም ዐደራ እላለሁ፤ በአስተሳሰባቸው ከንቱነት እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ልትመላለሱ አይገባም። እነርሱ ከልባቸው መደንደን የተነሣ ስለማያስተውሉ ልቦናቸው ጨልሞአል፤ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ተለይተዋል። ኅሊናቸው ስለ ደነዘዘ በማይረካ ምኞት፣ በርኵሰት ሁሉ እንዳሻቸው ለመኖር ቅጥ ለሌለው ብልግና ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል።"
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

በቀደሙት ሁለት ጥናቶች የአንድነታችን መሠረት የሆኑትን ሰባቱን መንፈሳዊ እውነቶች እና ለቤተክርስቲያን ህንጸትና ብስለት በክርስቶስ ኢየሱስ የተሰጡንን ስጦታዎች ለመመልከት ሞክረን ነበር።

በዛሬው ክፍል ደግሞ የቀደመውን ምንባብ በማሰብ ("ስለዚህ") ቤተክርስቲያን ከተተከለችበት መሠረት እና ከተቀበለችው ስጦታ የተነሳ፤ ሐዋርያው ጳውሎስ በጥብቅ ሊናገር እና በጌታ ስም ዐደራ ለማለት የፈለገውን ነገር እናያለን።

ዐደራ ማለት እንግዲህ፤ ትልቅ ዋጋ የምንሰጠውን ሃላፊነት ሌላውም ሰው እንዲሸከም የምናደርገው የጠበቀ ተማጽኖ፣ ልመና ወይም ማሳሰቢያ እንደመሆኑ መጠን፤ ታዲያ ሐዋርያው ጳውሎስ ዐደራ የሚለን ነገር ምንድነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። መልሱም አጭር እና ግልጽ ነው፦ እንደ አህዛብ (ያላመነ ሰው) አትመላለሱ ወይም አትኑሩ ነው!

በአማኝና ባላመነ ሰው መካከል እጅግ በጣም ብዙ እና መሠረታዊ ልዩነቶች ስላሉ፤ የቱንም ያህል የሕይወት ዘይቤአቸው ማራኪና አጓጊ መስሎ ቢታየን እንኳን እንደእነሱ መኖር እና ለመኖር ማሰብ ስህተት ነው። ግን ለምን?

1. አስተሳሰባቸው ከንቱ ነው፦ እንግዲህ በእግዚአብሔር ሚዛንና እይታ ያላመኑ ሰዎች አስተሳሰብም ሆነ ኑሮ "ከንቱ" በሚል ቃል ተገልጿል።

2. ልባቸው ደንዳና ነው፦ ከዚህ የተነሳ መረዳታቸው (Their Understanding) ብርሃንን ስላላገኘ በጨለማ የተሞላ ነው።

3. ሕይወት የላቸውም!፦ ልባቸው ስለደነደነ፤ መረዳታቸው ወይም ስለ እግዚአብሔር ያላቸው እውቀት በጨለማ የተሞላ ስለሆነ፤ እግዚአብሔር ከሰጠው ሕይወት ተካፋዮች አይደሉም። አሁንም ከቁጣ በታች ናቸው!

4. ኅሊናቸው የደነዘዘ ነው፦ የማይረካ ምኞታቸውን በርኵሰት ሁሉ በማስደሰት እንዳሻቸው ለመኖር ቅጥ ለሌለው ብልግና ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። ስለዚህ መሠረታዊ የሆነ የስነምግባር (Moral values) ልዩነት አለን።

በአማኝ እና ባላመነ ሰው መካከል መሠረታዊ የሆነ የአስተሳሰብ፣ የርዕዮተዓለም፣ የመረዳት፣ የስነምግባር እና የመንፈሳዊ ሕይወት ልዩነት ስላለ፤ አማኝ ባላመነ ሰው የሕይወት ፍልስፍና መጎምጀትም ሆነ እንደ አለአማኝ ለመኖር መሞከር ስህተት ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር የሚለን ዐደራ እንደነርሱ እንዳትኖሩ ነው!

አይ እንግዲህ! ለሚል ሰው “...ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” ያሉትን እስራኤላውያንን፤ እንዲሁም “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና...” ያለውን እግዚአብሔርን፤ ብሎም የሰጣቸውን ምላሽ ከታሪክ መማር ብልህነት ነው። (1ኛ ሳሙ 8:1-22)። ሰናይ ቀን!


ዛሬ የማሰላስለው የቃሉ እውነት፦ የእኔ የሕይወት ዘይቤ ካላመነ ሰው የተለ ነው!

የዛሬ ፀሎት፦ እግዚአብሔር ሆይ የሚረባኝን የምታውቅልኝ፣ እጅግ በጣም ጠቢብ፣ በምክርህ ደግሞ አስተዋይ ነህና አንተን መታዘዝ ይብዛልኝ።

ነገ እስከ ምንገናኝ ደህና ሁኑ!!
@Godshaday
301 views05:25
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-27 07:07:36 . Shaday DEVOTION
ⒺⓅⒽⒾⓈⒾⒶⓃⓈ

(ቀን #17)
ጸጋ ተሰጥቶናል
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የኤፌሶ 4:7-16
"ነገር ግን ክርስቶስ በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል። ስለዚህም እንዲህ ይላል፤ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ፣ ምርኮ ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ።” ታዲያ፣ “ወደ ላይ ወጣ” ማለት ደግሞ ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ወረደ ማለት ካልሆነ በቀር ምን ማለት ነው? ወደ ታች የወረደውም፣ መላውን ፍጥረተ ዓለም ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው። አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ሲሆን፣ ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው። ከእንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኰልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕፃናት አንሆንም። ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው፤ ከእርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፤ ራሱንም ያንጻል።"
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

ማንኛውም ሰው ሲወለድ ከአንዳች ልዩ ተሰጥኦ ጋር እንደሚወለድ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ ዳግም ለተወለደ ሰው ቢያንስ አንድ የጸጋ ስጦታን ሰጥቷል ። ይህም የጸጋው ባለቤት የሆነው፤ ክርስቶስ በወሰነው መጠን እንጂ በእኛ ፍላጎት ልክ አለመሆኑንና ስጦታው ለቤተክርስቲያን እንደተሰጠ ሐዋርያው ጳውሎስ ያስረዳናል።

ይህ ክፍል ስለ ስጦታዎች ከሚናገሩ አራቱ የአዲስ ኪዳን ምንባባት መካከል አንዱ ሲሆን የተጠቀሱትም ስጦታዎች፦ ሐዋርያት፣ ነቢያት፣ ወንጌል ሰባኪዎች፣ አስተማሪዎች እና መጋቢዎች ናቸው።

ሐዋርያት፦ የቃሉ ትርጉም "የተላከ" ማለት ሲሆን የአገልግሎቱ ዓላማ የትንሣኤው ምስክር መሆን እና የቤተክርስቲያንን መሠረት መጣል ነበር (ሐዋ 1:15-22 ፤ ኤፌ 2:20)። ለዚህም በአካለ ስጋ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን ማየት የግድ ነበር (1ቆሮ 9:1-2)።

ነቢያት፦ የትንቢት ዓላማ እና ትኩረት የእግዚአብሔርን ቃልና ፈቃድ በመግለፅ (በማስተማር)፣ እግዚአብሔርን በመታዘዝ የሚጓዙትን ሰዎች በማበረታታት (በማጽናናት)፣ የተበላሸ የሕይወት ዘይቤን እየገሰጹ ሰዎችን ወደ ንስሐ በመጥራት (በማስጠንቀቅ) እና ወደፊት ሊሆን ያለውን በማሳወቅ (በመተንበይ) የጽድቅ እና የቅድስና ኑሮን ማበረታታት ሲሆን ነቢያትም ለዚህ ዓላማ የተለዩ አገልጋዮች ናቸው።

ወንጌል ሰባኪዎች፦ ሁሉም አማኝ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ቢሆንም፣ ወንጌላውያን እግዚአብሔር ለወንጌል ስራ የለያቸው በየሄዱበት ያላመኑትን እየማረኩ ወደ መንግሥቱ የሚያመጡ ሃያላን ናቸው።

አስተማሪዎች እና መጋቢዎች፦ እነዚህ ሁለቱ የእረኝነት አገልግሎት ሀላፊነት ሲሆኑ፤ ዓላማቸው ተማርከው የመጡትን እየመገቡ፣ እየተንከባከቡ እና እያስተማሩ ለመንግሥቱ ማጽናት እና እውነተኛ ደቀመዛሙርት እንዲሆኑ ማሰልጠን ነው።

"በዚህ ዘመን ሐዋርያት እና ነቢያት አሉ?" የሚለው ጥያቄ ብዙ ዘመናት የክርክር ርዕስ የሆነ የነገረ-መለኮት ጥያቄ ነው። የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ይህንን ጥያቄ መመለስ ባይሆንም ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ግን ወንጌላውያን አማኞች ለድርድር የማናቀርበውን ሁለት ነገር እናስታውስ፦

አንደኛው የትኛውም አገልጋይ፣ "ነቢይ ነኝ ባይ" ወይም "ሐዋርያ ነኝ ባይ" ልክ የብሉይ ኪዳን ነቢያት እንዲሁም በአዲስ ኪዳን አስራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት እና ሐዋርያው ጳውሎስ የተቀዳጁትን አይነት "ሥልጣን" እንደሌለው ወይም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የሥልጣን ምንጭ አለመሆኑን ሲሆን፤ ሁለተኛው በዚህም ዘመን እግዚአብሔር ሰዎችን (Missionary) በልዩ ሁኔታ አስታጥቆ ለወንጌል እንደሚለይ እና እነርሱም ወንጌልን ወዳልደረሰበት ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ሀይል ይዘው እንደሚገቡ ነው።

ዋናው ቁምነገር ግን እግዚአብሔር ስጦታዎችን በመንፈሱ አማካይነት በነፃ የሰጠን አካሉ እንዲገነባ፣ ቅዱሳን ክርስቶስን በሚያከብር እና አማኝን በሚጠቅም መንገድ እንድናገለግል፣ ልጁን በማወቅ እና በማመን ወደሚገኘው አንድነት እንድንመጣ፣ ፍጹም ጌታን መስሎ በመኖር በሳል ሰዎች እንድንሆን ነው።

ዛሬ የማሰላስለው የቃሉ እውነት፦ "ክርስቶስ በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል"

የዛሬው ፀሎት፦ ጌታችን ሆይ በትምህርት ንፋስ እንዲሁም በሰዎች ረቂቅ ተንኮል እንዳንጠፋ ይልቁንም በነገር ሁሉ ወደ አንተ እንድናድግ ስለሰጠኸን የጸጋ ስጦታ ስምህ ይባረክ!


ነገ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ!!
@Godshaday
467 views04:07
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-26 12:47:19 .Shaday DEVOTION
ⒺⓅⒽⒾⓈⒾⒶⓃⓈ

(ቀን #16)
መሠረታችን ይኼ ነው!
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የኤፌሶን 4:4-6
"በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ፤ ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።"
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

የመንፈሳዊ አንድነት መሠረቱ እምነት /አስተምህሮ/ ነው። ሁሉም ወንጌላውያን ክርስቲያኖች በሁሉም የክርስትና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እኩል መረዳትና ስምምነት አላቸው ባይባልም፤ መሠረታዊ በሆኑ የክርስትና አስተምህሮና እምነት ላይ ግን በጭራሽ አይለያዩም። በዚህ ክፍል ጳውሎስ የአንድነት መሠረት የሆኑትን ሰባት መንፈሳዊ እውነታዎች ያነሳል፦

አንድ አካል፡ በአንዱ መንፈስ በመጠመቅ አይሁድም አህዛብም አንድ አካል የሆንባት፤ የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተክርስቲያን ነች (1ቆሮ 12:12-13 ፤ ኤፌ 2:11-18)።

አንድ መንፈስ፡ ለቤዛ ቀን የታተምንበት እና ለላይኛው እርስት መያዣ ሆኖ በሁሉም አማኝ ውስጥ በመኖር የአንድ አባት ልጆች መሆናችንን የሚመሰክርልን መንፈስ ቅዱስ ነው። (ሮሜ 8:15)

አንድ ተስፋ፡ ይህም ከነገድ፣ ከቋንቋ፣ ከወገን፣ ከህዝብ ሁሉ ዋጅቶ ለአምላኩ መንግስትና ካህናት ያደረገን የተባረከው ተስፋችን ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አዘጋጀልን መኖሪያ ሊወስደን በጠላቶቹ ላይ ደግሞ ሊፈርድ ዳግም በክብር ተገልጦ የሚመጣበት ጊዜ ነው። (ቲቶ 2:13 ፤ ራዕይ 5:9-10)

አንድ ጌታ፡ ለእኛ ሲል ሰው የሆነ፣ ስለ እኛ የሞተሞትን ድል አድርጎ የተነሳ፣ ያረገ፣ በሰማያት ስለ እኛ የሚማልደው፣ ሊወስደን በክብር የሚመጣው የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

አንድ እምነት፡ ሕይወትን ያገኘንበት፣ እንድንኖርበትና እንድንጋደልለት ለቅዱሳን አንዴ ፈጽሞ የተሰጠ እምነት ነው።(ይሁዳ 3) ይህም መዳን በእምነት፣ በክርስቶስ፣ በጸጋ ብቻ መሆኑን የሚያረግጥ ነው።

አንድ ጥምቀት፡ አማኝ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን በመሸጋገር፤ በክርስቶስ አካል ውስጥ የተቀላቀለበት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው። (1ቆሮ 12:13)

አንድ አምላክ እና አባት፡ እግዚአብሔር አምላካችን ደግሞም በፍቅር፣ በአክብሮት እና በመሰጠት እንድናገለግለው አካል ለተደረግንበት ቤተሰብ አባታችን ነው።

እንግዲህ የተጠራነው ወደዚህ መሠረት ነው። መሠረቱም እግዚአብሔር አምላክና አባት ወደሆነበት፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛና አስታራቂ በሆነው፣ ሰው በሆነው አምላክ ብቻ በማመንና በአንዱ መንፈስ ቅዱስ በመጠመቅ በቤተክርስቲያን ጥላ ስር አንድ ሆነን የመድኃኒታችንን ዳግም መምጣት በፍቅር መጠባበቅ ነው።

በዚህ መሠረት ላይ የቆመ ክርስቲያን የሚኖርለትና የሚሞትለት ተስፋ ስላለው በሄደበት የጽድቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንጂ ችግር ፈጣሪ አይሆንም። በሚቀጥለው ክፍል ደግሞ በዚህ መሠረት ላይ ቆመን ለተጠራንለት ጥሪ የሚመጥን ኑሮ እንድንኖር የተሰጡንን ስጦታዎች እናያለን።

ዛሬ የማሰላስለው የቃሉ እውነት፦ የቆምኩበት መንፈሳዊ መሠረት እንዴት ግሩም ነው!

የዛሬው ፀሎቴ፦ "እግዚአብሔር ሆይ የቆምኩበትን መሠረት አስደናቂነት ተረድቼ ለተጠራሁበት ጥሪ የተገባ ኑሮ እንድኖር እርዳኝ?"


ነገ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ!!
@Godshaday
435 views09:47
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-25 07:37:34 . Shaday Devotion
ⒺⓅⒽⒺⓈⒾⒶⓃⓈ
ⒹⒶⓎ #15

እንደሚገባ መመላለስ

ኤፌሶን 4፥1-3
--------------------------------
"እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ፣ ለተቀበላችሁት ጥሪ የሚገባ ኑሮ ትኖሩ ዘንድ እለምናችኋለሁ። ፍጹም ትሑታንና ገሮች ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁም በፍቅር እየተቻቻላችሁ ትዕግሥተኞች ሁኑ። በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።"
--------------------------------
የጌታ ጸጋ በእጅጉ ረድቶን ላለፉት ሁለት ሳምንታት ከምዕራፍ 1-3 ያሉትን መሰረታዊ የሆነውን አስተምህሮቶች (Doctrinal) ስናይ ቆይተናል፥ጌታ ቢረዳን ደግሞ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ተግባራዊ ክርስትና (Practical) የሆነውን ክፍል እንመለከታለን።

በክርስቶስ ስራ ሁላችንም ስፍራችን እንደተቀየረ ከነበርንበት የዓመፃና የቁጣ ልጅነት ወደ ዘላለማዊው የዕረፍት ቀጠና መግባታችን በእርሱም ወደ ድነት መምጣታችን እርግጥ ነው።

እንግዲህ የዳነ ሰው እንዴት ይመላለስ? ነው ጥያቄው። መልሱን ሐዋርያው ጳውሎስ እራሱ ነግሮና፤ እሱም "እንደሚገባ" ነው።

የቤተክርስቲያን አካል እንደ መሆናችን በዚህ ውስጥ በምን አይነት የህይወት ምልልስ ልንሄድ እንደሚገባ መርህ ያስቀምጥልናል።

በትህትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፥ ይህ አይነት ማንነት ክርስቶስ እራሱ በምድር ኖሮት አሳይቶናል። እራሱን ደግሞ ያለ ምስክርነት የማይተው አምላ፤ በየዘመናቱ ከሕይወታቸው እንድንማር ጌታ ሰዎችንም አሳይቶናል።

ትዕግስታችንም በፍቅር እንዲሆን መገለጫው እና መነሻው በዚህ መሰረት ላይ እንዲሆን ጌታ ፀጋውን ያብዛልን።

በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ እንድንተጋ እንደሚያስፈልግ ሐዋርያው ጳውሎስ ያሳስበናል።


ዛሬ የማሰላስለው የቃሉ እውነት፦ እንደሚገባ መመላለስ

የዛሬው ፀሎት፦ በትህትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም እንድንኖር ጌታ ሆይ እርዳኝ።

ነገ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ!!
@Godshaday
486 views04:37
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-24 06:20:30 . Shaday Devotion
ⒺⓅⒽⒺⓈⒾⒶⓃⓈ
ⒹⒶⓎ #14

የክርስቶስ ፍቅር
ኤፌሶን 3፥18-21

--------------------------------
"የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የመገንዘብ ኀይልን እንድታገኙ ነው። እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው። እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ክብር ይሁን፤ አሜን።"
--------------------------------

በዚህ ጥናታችን የምዕራፍ 3 የመጨረሻው ክፍል እና የኤፌሶንን መጽሐፍ ጭብጥ (Theme) እናያለን። ይህም ስለ "ክርስቶስ ፍቅር" እና ከዘላለም እስከ ዘላለም ባለው ታላቁ የማዳን ዕቅድና ስራ ውስጥ ሁሉ ነገር ለእርሱ ክብር ብቻ የመሆኑን እውነት ነው።

ዓለም ሳይፈጠር የመዳንን እቅድ እግዚአብሔር በልጁ በኩል እንዳሰበ ቀደም ሲል "በምዕራፍ 1" ላይ ተመልክተናል። ይህም የሆነው ጥግ እና መዳረሻ ከሌለው "ፍቅር" የተነሳ ብቻ እንደ ሆነ ያሳያል። ፍፃሜውም ከዘላለም የነበረውን ክብሩ እንዳይቀንስ አልያም እንዲበዛለት ሳይሆን ክብር የእርሱ ብቻ እንደ ሆነ ለመግለጥ ነው።

ጳውሎስም በአራቱ የመለኪያ መስፈርቶች የክርስቶስን ፍቅር:-ስፋት (width)፣ ርዝመት (length)፣ ከፍታ(high)፣ ጥልቀት(depth)፥ ምን ያህል እንደ ሆነ ከመታወቅ ስለሚያልፈው ዘላለማዊ ፍቅሩ እንድናስተውል እና ከቅዱሳን ጋር ለማወቅ እንድንበረታ ግድ ይለናል።

ፍቅር ግድ ስላለው አብ አባት ለአንድ ልጁ መሰዋዕትነት ያልራራለት ፥ ወልድም ስለ አመፀኞች እራሱን ለመስጠት ለነፍሱ ያልሳሳበት ይህ ድንቅ ፍቅር በዘመናት መካከል ለእኛ ተገልጧል።

የክርስትናም ሆነ የፍቅር ቱምቢው (Standard) ክርስቶስ እራሱ በሆነበት በዚህ ረዥሙ የህይወት ጐዳና ላይ እርሱን እያየን ወደ ፍፅምና ደርሰን ለመሞላት እራሳችንን እያተጋን መኖር ያስፈልጋል።

"በአመታት መካከል ሥራህን ፈፅም" ተብሎ እንደተጻፈ በሥራው ግሩም የሆነ አምላክ ከሰው አሳብ እና አዕምሮ በላይ በሆነው ዘላለማዊ ፈቃዱ ይከውናል።

ዛሬ የማሰላስለው የቃሉ እውነት፦ መለኪያ የሌለው የክርስቶስ ፍቅር።

የዛሬው ፀሎት፦ የክርስቶስ ፍቅር እንዳውቅ እንዳስተውል ፀጋ ይብዛልኝ።

ነገ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ!!
@Godshaday
516 views03:20
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-23 08:53:57 . Shaday Devotion
ⒺⓅⒽⒺⓈⒾⒶⓃⓈ
ⒹⒶⓎ #13

በውስጥ ሰውነት ማደግ
ኤፌሶን 3፥14-17

--------------------------------
"በዚህም ምክንያት በአብ ፊት እንበረከ ካለሁ፤ ከእርሱም በሰማይና በምድር ያለ ቤተ ሰብ ሁሉ ስያሜ ያገኛል። በውስጥ ሰውነታችሁ እንድትጠነክሩ፣ ከክብሩ ባለጠግነት በመንፈሱ በኩል ኀይል እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤ ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣"
--------------------------------

በዛሬው ጥናታችን እጅግ ሰፊ እና ጥልቅ ሀሳብ ያለውንና ጳውሎስ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን የደረገውን ጸሎት፤ ዛሬም እኛ አማኞች በጸሎት እራሳችንን ዕለት ዕለት የምናቀርብበትን እውነት እናያለን።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቶቹን ስለ ፀሎት ማስተማር ሲጀምር “...በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ..." በማለት እግዚአብሔር አብ አባታችን የሁሉ ነገር ምንጭ እንደ ሆነ አስተምሮናል ፤ ያዕቆብም በምንፀልይበት ወቅት በልግስና ሳይሰስት የሚሰጠን እግዚአብሔር እንደሆነ ነግሮናል።

ጳውሎስም አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት "እንበረከካለሁ" በማለት ይህንኑ ተግባር በመልዕክቱ ያሳየናል።

ይህም ፀሎቱ በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ነው። መቼስ ጌታን በማመናችን አዲስ ህይወት እንዳገኘን ተነግሮናል፥ ይህም ህይወት የሚያድግ፣ የሚጠነክር፣ ወደ ፍጹምነት የሚደርስ (Spiritual Maturity) እንደሆነ ቃሉ ያሳስበናል፥ ይህም ዕድገት እና ጥንካሬ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በውስጣችን የሚሆን ነው።

እድገቱም አቅጣጫ ያለው እርሱም ክርስቶስ በልባችን እንዲኖር ነው። በክርስቶስ ላይ ያለን መረዳት እና እምነት ህይወታችንን እና አኗኗራችንን ይለየዋል። ይህን አይነት ህይወት እግዚአብሔር እንደባለጠግነቱ መጠን በልባችን ያብዛልን።

የእድገታችንም ሆነ የህይወታችን ቁመና ብሎም መሰረትነቱ በፍቅር ላይ ቆሞ እንዲፀና ይፀልያል። ዛሬም እራሳችንን በዚህ እውነት እያበረታን መኖር እንድንችል ጌታ ይርዳን።

ዛሬ የማሰላስለው የቃሉ እውነት፦ በውስጥ ሰውነታችን መጠንከር ።

የዛሬው ፀሎት፦ እግዚአብሔር ሆይ ክርስቶስን በልባችን በማመን እንድንኖር እርዳን።

ነገ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ!
@Godshaday
536 views05:53
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-22 07:37:18 . Shaday Devotion
ⒺⓅⒽⒺⓈⒾⒶⓃⓈ
ⒹⒶⓎ #12

የዘላለም ሀሳቡ በቤተክርስቲያን

ኤፌሶን 3፥8-13
--------------------------------
"ምንም እንኳ ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ ብሆንም፣ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ ይህ ጸጋ ለእኔ ተሰጠኝ። እንዲሁም ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ላለፉት ዘመናት የተሰወረውን የዚህን ምስጢር አሠራር ለሁሉም እገልጥ ዘንድ ተሰጠኝ። አሳቡም በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ ላሉት አለቆችና ባለ ሥልጣናት ይታወቅ ዘንድ ነው፤ ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን በፈጸመው ዘላለማዊ ዕቅዱ መሠረት ነው። በእርሱና በእርሱ ላይ ባለን እምነት አማካይነት፣ በነጻነትና በልበ ሙሉነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን። ስለዚህ ክብራችሁ በሆነው ስለ እናንተ በደረሰብኝ መከራ ተስፋ እንዳትቈርጡ ዐደራ እላችኋለሁ።"
--------------------------------

በትላንትናው ጥናታችን ላይ እንዳየነው ለጳውሎስ የተገለጠው ምስጢር በየትኛውም ዘመን እና ትውልድ ያልታወቀ ነገር ግን የአህዛብ እና አይሁድ በአንድ ላይ ወራሽ እና የተስፋ ቃል ተካፋይ መሆናቸውን፤ ስለዚህም እውነት ደግሞ ጳውሎስ እስረኛ መሆኑን ተመልክተን ነበር።

በዛሬው ጥናት ላይ ከ ቁ.8 ጀምሮ ያለው የማይመረመረውን ብሎም ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን የፀጋውን ባለጠግነት ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ብሎም በአይሁድ እና አህዛብ መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በማፍረስ አካሉ የሆነችውን ቤተክርስቲያንን ሊገልጥ ጌታ የሄደበትን ርቀት ከሁሉ ለማንሰው ለእኔ ተሰጠኝ ብሎ ጳውሎስም ስለሚነግረን እውነት እናያለን።

ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል Ekklēsía የሚውለውን የግሪክ ቃል የሚተካ ሲሆን፤ የቃሉ አቻነት በተመለከተ ዛሬም ድረስ የተለያዩ ሀሳቦች ይነሳሉ።

በአማርኛው ቤተክርስቲያን የሚለው፦ "የክርስቲያን ቤት" የሚለውን አመልካች ነው።
ግሪኩ ቃል (ekklēsía) የሚለው ፦ "የተለዩ" ወይም ከዓለም ተጠርተው የወጡ አማኞችን አመልካች ነው።

በዚህ ክፍል ዓውድ መሠረት ቤተክርስቲያን ሲባል ህንፃ እና አዳራሽ ሳይሆን አማኞችን፣ ቅዱሳኖችን ወይም "እኛ" በእርሱ ያመንን እንደሆነ እውን ነው።

ቤተክርስቲያን ማንነቷ የክርስቶስ አካል የሆነች ሰማያዊ እንደ መሆኗ የእግዚአብሔርን ጥበብ እና መንግስት በምድርም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም ላይ የምትገልጥ በዚህም ለአለቆች እና ሥልጣናት የምትታወቅ ናት።

የትንሣኤው መንፈስ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ከእርሷ ጋር ያለ፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የፈፀመውን ዘላለማዊ አሳቡን፣ ታላቅነቱንና ልዩ ልዩ ጥበቡን የሚገልጥባት ናት።

በእርሱ ላይ ባለን እምነት በነፃነት ያለፍርሃት በእርሱ ፊት መቅረብ እና መግባት የቻልንበትን ታላቅ ስራ የፈጸመበት ግሩም ዕቅድ ነበር።

በስተመጨረሻም ጳውሎስ ስለ እነርሱ በደረሰበት መከራ፤ ክብራቸው ስለሆነ ተስፋ እንዳይቆርጡ አደራ ይላል።

ዛሬ የማሰላስለው የቃሉ እውነት፦ በቤተክርስቲያን በኩል ስለሚገለጠው የእግዚአብሔር ጥበብ።

የዛሬው ፀሎት፦ እንደ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን የዘለዓለም ዕቅድ እንድናስብ።

ነገ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ!!
@Godshaday
550 views04:37
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-21 06:39:10 . Shaday Devotion
ⒺⓅⒽⒺⓈⒾⒶⓃⓈ
ⒹⒶⓎ # 11


ለጳውሎስ የታወቀው ምስጢር

የኤፌሶን 3፥1-7
--------------------------------
"ስለዚህም አሕዛብ ስለ ሆናችሁ ስለ እናንተ የክርስቶስ ኢየሱስ እስር የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር እንበረከካለሁ።ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል፤አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፤ይህም፥ አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ፥ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን እንደ ተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ ለሰው ልጆች አልታወቀም። እንደ ኃይሉ ሥራ እንደ ተሰጠኝም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠን የወንጌል አገልጋይ ሆንሁለት።"
--------------------------------

ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ባለው የእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ረዥሙ የሰው ልጅ የድነት ታሪክ፥ ገና ከፍጥረቱ የወደቀውን የመጀመሪያውን አዳም እንዴት ባለ ታላቅ የማዳን ምስጢር እና ተስፋ የኋለኛው አዳም በሆነው በክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር እንደ ፈፀመው ቅዱሱ መጽሐፍ ያስረዳናል።

ቀደም ሲል ባየናቸው ጥናቶች እግዚአብሔር በአብርሃም፣ ከዚያም በእስራኤል በኩል ለዓለም በገለጠው የድነት ተስፋ፤ አህዛብም በአንዱ በክርስቶስ በኩል አብሮ ወራሽ እንደሆኑ የአህዛብ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ ይህ አስደናቂ መለኮታዊ ምስጢር እንደተገለጠለት ይነግረናል።

ጌታ ኢየሱስ በአስደናቂ መገለጥ በደማስቆ ጎዳና ላይ ሳውል የነበረውን ጳውሎስ እንዳገኘው ይህም በአህዛብ መካከል ስሙን እንደሚሸከም እንደተናገረው፤ ብሎም ከሌሎች ሐዋርያት በተለየ መልኩ ከስጋ እና ደም ባልሆነ መገለጥ የአህዛብ አብሮ ወራሽነታቸው፣ ወገን መሆናቸው፣ በአንዱ በክርስቶስ በኩል ያለ ልዩነት አንድ መሆናቸውን ጳውሎስ በመልዕክታቶቹ በተለይም በኤፌሶን መፅሐፍ ይነግረናል።

ግሩም የሆነው የጌታ ስራ የአይሁድ ወይም የአህዛብ ያልሆነ ነገር ግን ከአይሁድ እና ከአህዛብ የሆነ "በአንድ አካል አብረው እንዲሆኑ " ይህም አንድ አዲስ ሰው የተገኘበት አካሉ የሆነችው ቤተክርስቲያን ነች። ምናልባት ጌታ ቢፈቅድ እና ብንኖር በሚቀጥለው ቀን ስለ ቤተክርስቲያን በሰፊው እናያለን።

ለዚህም እንደ ተሰጠው ጸጋ የወንጌል አገልጋይ በመሆኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ጸጋ መጋቢ መሆኑን በመናገር ይህ ታላቅ ምስጢር ለእርሱ እንደ ተገለጠ፥ በየትኛውም ትውልደ ዘመን እንዳልታወቀ ለዚህም ስለክርስቶስ ወንጌል እስረኛ እንደ ሆነ ይፅፍላቸዋል።

ይህ ለእኛ ቀድሞ ወገን፣ ወራሽ፣ የተስፋ ቃል ተካፋይ ላልነበርን ትልቅ ትርጉም ያለው ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ የተፈጸመው የመስቀል ላይ ስራ እኛም አህዛብ የሆነውን የመዋጀቱ ምስጢር በባሪያውም በኩል ስለተገለጠው እውነት እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት መሰረታችን ነው።

ዛሬ የማሰላስለው የቃሉ እውነት፦በአንድ አካል አብረን የተስፋው ቃል ተካፋይ መሆናችንን።

የዛሬው ፀሎት፦ እግዚአብሔር ሆይ ይህን በባሪያህ በሐዋርያው ጳውሎስ በኩል የገለጥከውን ታላቁን ምስጢር እያሰብኩ እንዳመሰግንህ ፀጋህን አብዛልኝ።

ነገ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ
@Godshaday
580 views03:39
ክፈት / አስተያየት ይስጡ