Get Mystery Box with random crypto!

እመቤቴ ሆይ አንቺ ኑሮ የጀመርሽው ገና በሥላሴ ልቡና ውስጥ ነበር፡፡ በዛሬው ዕለት የሥላሴ ሃሳባቸ | ግጻዌ

እመቤቴ ሆይ አንቺ ኑሮ የጀመርሽው ገና በሥላሴ ልቡና ውስጥ ነበር፡፡ በዛሬው ዕለት የሥላሴ ሃሳባቸው ተከናወነ፡፡ የነቢያት ትንቢታቸው የመላዕክት እህታቸው እመቤታችን ሆይ ተስፋችን በአንቺ ተፈፀመ፡፡ " ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ" እንዲል አንቺን ተስፋ አድርጎ ከገነት የወጣው አዳም ዛሬ ተስፋው ለመለመ፡፡ የቅዱሳን እናትና አባትሽን ሐና እና ኢያቄምን ልጅ በማጣት ያዘኑትን ኃዘን ብቻ ሳይሆን እኛም ገነትን በማጣት የተሰቃየነውን ስቃይ በልደትሽ አጠፋሽልን፡፡

ፀሐይን ያስገኘ አምላክ የወጣብሽ ምሥራቅ፣ እውነተኛው የሕይወት ውኃ የፈለቀብሽ ንጹሕ ምንጭ፣ ሁሉንም በቸርነቱ የሚያስጠልለው ዛፍ የበቀለብሽ ለምለም መሬት፣ ሥጋውና ደሙን ያስገኘሽ አማናዊት መቅደስ ያንቺን ልደት በምን መስለን እንናገረው? ያንቺን ልደት ስናስብ የሚሰማንን እውነተኛ ደስታስ በምን እንግለጸው?

ፍጥረት ሁሉ በደስታ የደነገጠብሽ የምሥራች ሆይ እስቲ ከወንድሞችሽ መላዕክት አንዱን ላኪና ያንቺን ልደት ያብስረን፡፡ ቅዱስ ገብርኤል እንኳን ሊያበስርሽ ተልኮ ሰላምታ ለማቅረብና ያንቺን ክብር ለመናገር ቃላት አጥሮት ሲጨናነቅ አይተነዋል፡፡ አሁንስ ስለእኔ ልደት ንገራቸው ብለሽ ብትልኪው መቶ ምን ይለን ይሆን?

እመቤቴ ሆይ የሰላም ባለቤት ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘሽ አንቺ ነሽና ከአንቺ ሌላ የሰላም ሚኒስቴር አናውቅም፡፡ " ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት፤ ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት" የሚያክም እውነተኛው ሐኪምን ያስገኘሽ አንቺ ነሽና ከአንቺ ሌላ ጤና ሚኒስቴር አናውቅም፡፡ ዛሬ የዓለም ጤናና ሰላም ሚኒስቴር የተመሰረተችበት ቀን ነው፡፡

ወላዲተ አምላክ ሆይ እንዴት ነው ታድያ የሰማይ ቤት ጉድጉድ? የአንቺን ልደት ለማክበር ቅዱሳን መላዕክት ፣ ፃድቃን ሰማዕታት በሰማይ ቤት እንዴት ተጨንቀው ይሆን? ምንስ ስጦታ ሊሰጡሽ አሰቡ? ቢያስቡስ ላንቺ ያልተሰጠሽ ምን አለ? ግን ደግሞ ልጅሽ በልደትሽ ቀን " ምን ላድርግልሽ?" ብሎ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ታድያ የመስቀል ስር ስጦታዬ እመቤቴ ሆይ ልጅሽ ክርስቶስ " እነሆ ልጅሽ" ብሎ በመስቀል ስር እኔንም ላንቺ አደራ እንደሰጠ እንዳትረሺ፡፡

እመቤቴ ሆይ አንቺ በፍጹም ንጽሕና ተወልደሽ እንደ ልጅሽ አርገሻል፡፡ እኔ ግን በኃጢአት ታስሬ በልጅሽ ሥጋና ደም መወለድ አቅቶኛል፡፡ እናቴ ሆይ አንቺስ ከወለድሽ በፊትም በኋላም በፍጹም ድንግልና ኖረሸል፡፡ እኔ ግን ዘወትር በኃጢአት እየረከስኩ " አመንዝራውን ድንግል" የሚያደርገውን ቁርባን ተቀብዬ ድንግል መሆን አቅቶኛል፡፡ ወላዲተ አምላክ እባክሽን እኔም ልደቴን ከአንቺ ጋር አከብር ዘንድ ልጅሽ ከኃጢአት አንጽቶ ዳግም በቅዱስ ሥጋውና ደሙ እንዲወልደኝ ለምኝልኝ፡፡

እንኳን ለእመቤታችን፣ ለእናታችን፣ ለአማላጃችን፣ ለወዳጃችን፣ ለስጦታችን፣ ለምርኩዛችን፣ ለመመኪያችን፣ ለአጽናኛችን፣ ለደስታችን፣ ቅድስት ብጽዕት ክብርት ድንግል ማርያም ልደት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡
ዓዲ
እንኳን ለልደታችን አደረሰን፡፡ ልደቷ ልደታችን ነውና፡፡

ዲያቆን ዮሐንስ ደረጀ
ግንቦት 01/2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ
https://t.me/dnJohannes