Get Mystery Box with random crypto!

እንኳን ልጅሽ ማረችሽ ............................................. | ግጻዌ

እንኳን ልጅሽ ማረችሽ
............................................................

በሰው ልጅ ከንፈር ላይ በጣም የሚያምር ቃል "እናት" የሚለው ቃል ሲሆን በጣም የሚያምር ጥሪ ደግሞ "እናቴ" የሚለው ነው። "እናቴ" በተስፋ እና በፍቅር የተሞላ፣ ከልብ ጥልቅ የሆነ ጣፋጭነት ያለው ከማር ይልቅ የሚጣፍጥ ቃል ነው።

ከሁሉ ይልቅ ግን አምላክ "እናቴ" ሲል በጣም ይደንቃል። እኛም የወለደችንን "እናቴ" እንላለን አምላክም የወለደችውን "እናቴ" ይላል እንዲያው ሌላ ቃል በኖረ እና ከፍ ከፍ አድርገን ለእርሷ ሌላ የእናትነት ስም ባወጣንላት፤ ለነገሩ እርሱ አማላኳ እና ልጇ ከፍ ከፍ ያደረጋት እኛ ምን ልንጨምርላት? ግን ቢሆንም እሷን ከፍ ከፍ ከማድረግ አንቦዝንም ያሉንን ቃላት ሁሉ እንጠቀማለን ምክንያቱም እናት ሁሉም ነገር ነች። እሷ በሀዘን መጽናኛችን ናት ፣ በመከራ ውስጥ ያለችን ተስፋ እና ጥንካሬያችን ናት፣ እሷ የፍቅር፣ የምህረት፣ የህይወት እና የይቅርታ ምንጭ ነች።

በ1ኛ ቆሮንጦስ መልዕክቱ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው "ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን?" እናትነትን ተፈጥሮም ውስጥ እናየዋለን ፀሐይ ልክ እናት ልጇን እንደምትመግብ ምድርን በብርሃን ትመግባታለች ለህልውናዋ የሚሆኑትን ንጥረ ነገሮችም ትለግሳታላች። የባሕርን ዝማሬና የወፎችንና የወንዞችን መዝሙር ምድርን ሲሞላ ልክ ልጇ እንደሚቦርቅ ህፃን ፍዝዝ ብላ ታያታለች።

ይህች ምድርም ብትሆን የዛፎች እና የአበባዎች እናት ናት። በውስርጧ ያለውን ጥረነገር ያለ ስስት ትለግሳቸዋለች፣ ፍሬ ያፈሩ ዘንድ፣ አበባን ያፈኩ ዘንድ፣ እናታቸውን በልምላሜ ካባ ያስዉቡ ዘንድ ትንባከባቸዋለች የእነሱ መለምለም እና መፍካት ለእናታቸው ውበትን ያላብሳታል። ከአምላክ በሚሰጣት ጠል እና በላዩአም በመላት ወንዞች እና ምንጮች ልጆቿን ጡት ታጠባለች ታረሰርሳቸዋለች። ዛፎቹ እና አበቦቹም ቢሆኑ ለታላቅ ፍሬዎቻቸው እና ዘሮቻቸው ደግ እናቶች ናቸው።

እናትነት በውበት እና በፍቅር የተሞላ ዘላለማዊ መንፈስ ነው። እና እኚህ ሁሉ እናቶች አምላካችን የሚሉትን እርሷ ልጄ ብላ የምታየው እናት፣ እርሱ አለማትን የሚመግበውን የመገበች እናት፣ እርሱ ሁሉን ፈጥሮ ሲያበቃ ለሰውነቱ እድገት የሚሆነውን ወተት የመገበችው ድንግል እናት፣ እርሱ ፍጥረትን እንደ ሰጎን ዐይኑን ሳይነቅል በስስት የሚመለከተንን እኛን በስስት አይኗን ሳትነቅል በምድር ለይ በቆየበት ጊዜያት በሙሉ የተመለከተች እናት፣ ገና አይኑን ሲገልጥም ነፍሱን ከሥጋው በፈቃዱ ሲለይም የተመለከታት እናት፣ እኛ አምላካችን፣ አባታችን እያልን አንገታችንን ወደ ሰማይ አንጋጠን የምንለምን እርሷ ግን አለምን በመዳፉ የጠቀለለውን በጨርቅ ጠቅልላ በእቅፏ ይዛ ልጄ ብላ አይን አይኑን በፍቅር እየተመለከተች የምታናግረው እናት። ከቶ ለዚህች እናት ምን የሚል ስም እናወጣ ይሆን?

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም "ጌታ ሆይ እናትህን ማን ብለን እንጥራት? እናት ብቻ እንዳንላት ድንግል ሆና አገኘናት ፣ ድንግል እንዳንላት ልጅ ታቅፋ አየናት። ጌታ ሆይ እናትህን ለመጥራት እንዲህ የሚያስቸግር ከሆነ አንተን ከቶ ምን ብለን እንጠራሃለን?"በማለት በምን ስም እንደሚጠራት እንዲህ ከተጨነቀ እኛ ከቶ ማን ብለን ልንጠራት እንችላለን?

ጠቢቡ ሰሎሞንም “፤ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት ፤ለእናትዋ አንዲት ናት ለወለደቻትም የተመረጠች ናት። ቈነጃጅትም አይተው አሞገሱአት፥ ንግሥታትና ቍባቶችም አመሰገኑአት። ፤ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ፥ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠራች፥ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት?” እያለ በትንቢት መነጽር ተመልክቷት በመደነቅ የዘመረላትን ብላቴና ከቶ እኛ ማን ብለን ስም እናውጣላት?

"እግዚአብሔር መረጠሸ፥ ልቶኚው እናቱ
ይኸው ሊፈፀመ፥ የአዳም ትንቢቱ
የሔዋን ተስፋዋ፥ የአዳም ዘር ህይወት
የእያቄምወ ሀና፥ የፍሬ በረከት
ኪዳነምህረት የድህነታችን ምክንያት
ድንግል ተወለደች፥ የክርስቶስ እናት"
እናም ለእርሷ "የአምላክ እናት" ከመባል ሌላ ምንም ክብርን ይሚያላብስ ስም አላገኘንምና በአምላክ ስሞች ለይ ሁሉ "እመ" እየጨመርን እንጠራታለን፡

እመ አምላክ

እመ ፍቅር

እመ ብርሃን

እነሆ ስለዚህች ብላቴና የተነገረላት ነገር ይገለጥልን ዘንድ እናትና አባቷ ማን ብለው ይጠሯት እንደሆነም እንሰማ ዘንድ ኑ ወደተቀደሰዉ ተራራ እንሂድ።

ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ የነገረ ማርያም መጽሐፋቸው "ትንቢት ከተነገረለት ከአንበሳ ጉድጓድ፤ ድንግል ሙሽራ በተገኘሽ ጊዜ የንጉሦች ንጉሥ የሰሎሞን ልቡ እንደተደሰተ፤ ደስ ባላቸው በመላእክት አንድነት ፊት ታምርሽን እየተናገርኊ የሐና አበባ ማርያም እዘምርሻለኊ፤ ወተትን ጠብቶ እንደሚዘልል እንቦሳም ዝለል ዝለል ይለኛል" በማለት ሰሎሞን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቶ ታላቅ ደስታን ለኹላችን እንደሰጠን አብራርተው እንደገለጡ፤

እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች፤ ዛሬ በሊባኖስ ተራራ የመድኃኒት እናት እርሷም እመ አምላክ የሆነች ተወልዳልናለችና። ይህም ምልክት ይሆንልናል ሕፃኗን ተጠቅልላ በተራራው ጫፍ ተኝታ እናገኛታለን፤ ፍጠኑ ወደ ተራራው እንውጣ።

እነዚያን ደጋግ ቅዱሳን ባልና ሚስት ሃና እና እያቄምን እናይ ዘንድ፣ እነሆ መካኒቱ ቅድስት ሃና ሰባቱ ሰማያትን ሰንጥቃ መጥታ በማሕፀኗ ስታድር ያየችትን ፀዓዳ ርግብ የሆነችውን ሕፃን እናይ ዘንድ ወደ ተቀደሰው ድንኳን እንሂድ። እነሆ ቅዱሱ እያቄም ከሰባተኛው ሰማይ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ ያየውን ነጭ ዖፍ ምስጢር ይገለጥልን ዘንድ ፍጠኑ እንሂድ ወደ ተራራው እንውጣ። ከመላእክቱ ጋር እናመሰግን፥ እናደንቅም።

ህጻኗንም በእናቷ እቅፍ ከአባቷ ጋር ባገኘናት ጊዜ ልክ እንደ ሊቃውንቱ እጅ ነስተን "እነሆ ውዲቷ ሐና አንቺን የፀነሰችባት የደስታ ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ አረጋዊው ኢያቄምም ለሕይወት አንቺን ያፈራባት ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ አንዲቱ ርግቤ ማርያም አንቺ የዓለሙ ኹሉ መድኀኒት ኾነሻልና ታምርሽን አመሰግናለኊ" በማለት ምስጋናን እናቅርብ።

፤እነሆ ከዕሴይ ሥር የወጣችውን በትር ከርሷም ያበበውን አበባ እናይ ዘንድ ኑ ፍጠኑ እንሂድ ወደ ተራራው እንውጣ። ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ እያልን ከመላእክቱ ጋር እንዘምር። የእናታችንን የልደቷን ቀን ከእናቷ እና አባቷ ጋር በመሆን እናክብር።

አያታችንን እንኳን ልጅሽ ማረችሽ እንበላት።
"ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በማርያም ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ሆነ!" (ቅዱስ ያሬድ)
"ይህች ዕለት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀባት ዕለት ናት" (ቅዱስ እንድርያስ)
ዮርዳኖስ.21

ግንቦት 01, 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ