Get Mystery Box with random crypto!

ብዙዎቻችን በምንወዳቸው ሰዎች የልደት ቀን ፍቅራችንን በውብ ቃላት ሰድረን ጽፈን እንልክላቸዋለን፥ | ግጻዌ

ብዙዎቻችን በምንወዳቸው ሰዎች የልደት ቀን ፍቅራችንን በውብ ቃላት ሰድረን ጽፈን እንልክላቸዋለን፥ መልካም ምኞታችንን እናዥጎደጉድላቸዋለን። ታዲያ የመወለዷ ደስታ ለወላጆቿ እና ለወዳጆቿ ብቻ ሳይሆን ለአዳም ዘር በሙሉ ለሆነው ለእመቤታችን ልደት ምን ልትጽፉላት አሰባችሁ? ምን ልትሏትስ ትወዳላችሁ? ልደቷ ልደታችን ለሆነው ንጽሕት ምኞታችሁ ምንድነው? እኔ ውለታዋ የከበደኝ ልጇ የተወለደችውን ወላዲተ አምላክ በልደቷ ስዕል ፊት ቆሜ እያየኋት ይህንን ጻፍኩላት:

"የተወለድሽ እናት ሆይ ለእኛ የተሾሙልን ብጹዓን ሊቃነ-ጳጳሳት በሥዕልሽ ፊት ቆሙ፥ ለመኑሽም አላፈሩም፤

ቅድስት ሆይ አባቶቻችን ካህናት በሥዕልሽ ፊት መልካም መአዛ ያለውን ዕጣን አጠኑ ፥ ነግህ ሰርክ ሳይሉ ለምሥጋናሽ ተፋጠኑ አላፈሩም፤

ድንግል ሆይ ከእኛ ፊት ሐዘናቸውን እየደበቁ አባቶቻችን በደጀ ሰላምሽ በሥዕልሽ ፊት አነቡ አንቺም አጽናናሻቸው፤

ማርያም ሆይ በእንብርክክ እየዳሁ እጃቸውን ዘርግተው እናቶቻችን በደጃፍሽ ተማጸኑሽ፥ የእናት ሆድ አያስችል ነውና ብሒሉ የለመኑትን ከሆድሽ ፍሬ ዘንድ አሰጠሻቸው፤

እኔም ይኸው በመቅደስሽ በሥዕልሽ ፊት ቆምኩ። የጳጳሳቱ የረቀቀ ክህነት፣ የካህናቱም ትጋት፣ የአባቶቼ ፍቅር፥ የእናቶቼም የዋሃት የለኝም፥ አንቺን ግን ተስፋ አደርጋለሁ።

ሕጻን እና ሽማግሌ፥ ድሃና ሀብታም ብሎ የማይለይ የተአምርሽን በረከት ለእኔም ለባርያሽ ታደርጊልኝ ዘንድ በሊቃውንቱ ውብ ዜማ "በሥዕልሽ ፊት መቆምን አላፍርም" ብዬ ዘወትር በመቅደስሽ አውጃለሁ።"

ንጽሕት ሆይ ልደት የለንም እኛ፥ ልደትሽ ነው ልደታችን!!

ዲያቆን እስጢፋኖስ ግርማ