Get Mystery Box with random crypto!

ከዓመት እስከ ዓመት ግርግር በማያጣትና ሁሌም በሰውና በገበያተኛ በተጨናነቀችው ኢየሩሳሌም ውስጥ እ | ግጻዌ

ከዓመት እስከ ዓመት ግርግር በማያጣትና ሁሌም በሰውና በገበያተኛ በተጨናነቀችው ኢየሩሳሌም ውስጥ እየተጓዝን ነው:: ጥንታዊትዋ የኢየሩሳሌም ከተማ በአሁኑ ሰዓት በአራት ሩቦች ተካፍላ ትተዳደራለች:: የክርስቲያን እርቦ ፣ የሙስሊሞች እርቦ ፣ የአርመኖች እርቦ እና የአይሁድ እርቦ ይባላሉ::

ለሦስቱ አብርሃማውያን እምነቶች (Abrahamic religions) ለአይሁዳዊነት ለክርስትናና ለእስልምና ትልቅ ፋይዳ ባላት ኢየሩሳሌም "አርብ አርብ" ብቻ ሳይሆን ሁሌም ሽብርና ግርግር አለ:: በሁሉም ሩቦች ተሳላሚዎች ፣ ጎብኚዎች ፣ ሻጮች ፣ ገዢዎሽ እስከ እኩለ ሌሊት ይርመሰመሳሉ::

ዘንድሮ እግር ጥሎኝ ከአንድ ወዳጄ ጋር በአይሁድ እርቦ (Jewish quarter) በኩል ሳልፍ አንድ ልብ የሚነካ ሥዕል ዓይኔ ውስጥ ገባ:: ሥዕሉን ሳይ ዕንባ በዓይኔ ሞላ:: የኢሳይያስ 53ቱን የሕማም ሰው ፣ የማይናገረውን በግ በአንገቱ የእሾህ አክሊል ጌጥ አድርገውለት እንዲህ ሆኖ ሳየው ችዬ የማላነበውን ኢሳይያስ 53 በሥዕል ሲያመጣብኝ ከማልቀስ ውጪ ምንም አቅም አልነበረኝም::

ነቢዩ ኢሳይያስ ሳይናገር በፊት የሚቀበለው እንደሌለ አውቆ "የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል?" ብሎ የተጨነቀበትን ይህን አስጨናቂ ራእይ እንዴት እንረሳዋለን? ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባስ በቀር ኢሳይያስ 53 ን አንብቦ "ማን አምኖአል?" (ሐዋ. 8:26) የእግዚአብሔር ክንዱ የተባለ ክርስቶስስ ለማን ተገልጦአል?

በግርፋቱ ብዛት ፊቱ በደም ተለውሶ "ባየነው ጊዜ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም" የተባለበትን ውበቱ ስለ እኛ የጠፋው የሕማም ሰው እንዴት ከሕሊናችን ተሰወረ?

"እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።ተጨነቀ ተሠቃየም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም" የሚለው ቃል ምንኛ ያስጨንቃል? ቆስሎ የሚፈውስ ታምሞ የሚያድን ታስሮ ነፃ የሚያወጣውን የእግዚአብሔር በግ ለመግለፅ ቃላት አቅም ቢያጥራቸው እንዲህ በብሩሽ ኃይል ተሥለው ሳያቸው ሁሉን ነገር ዘነጋሁት::

አንድ ልብሱ በቀለም ያደፈ ሰው በሥዕል ጋለሪው ደጃፍ ቁጭ ብሎ ይፈርማል:: እንደ መታደል ሆኖ ሰውዬው የሥዕሉ ባለቤት UDI MERIOZ ነበረ:: ቀርቤ ስለ ሥዕሉ የተሰማኝን ስነግረው እሱም ስሜቱ ተነካ:: "ይሄንን ሥዕል እኔ ብሥለውም የእኔ ፈጠራ አይደለም:: ሸራውን ወጥሬ በቀለም ላይ የሠራሁት እኔ ነኝ:: ነገር ግን ከመሣሌ በፊት በተደጋጋሚ በሕልሜ አየው ነበር:: የሣልሁትም ያየሁትን ነው" አለኝ:: ሥዕሉንም ፈርሞ ለእኔና ለወዳጄ ሠጠን::

ቅዱስ ኤፍሬም "ጌታ ሆይ ረዥሙን ሥቃይህን ማን ሊገልጸው ይችላል?" እንዳለው የጌታን መከራ የሚገልፅ አንደበት የሚሥለው ብሩሽ ባይኖርም ለአፍታ ግን እንዲህ በየሰዉ ላይ ባሳረፈው ጸጋ ሕማሙን ያስታውሰናል::

ይህ የበገና መዝሙር ግጥም ግን ከሕሊናዬ መጣ

"ያ ሁሉ መከራ እንዴት ይግባ ልቤ
አልበጠስ አለኝ የኃጢአት መረቤ

ተው ልቤን ስበረው ልመንህ አጥብቄ
መቼ ሕይወት ሆነኝ ቃልህን ማወቄ
ቃሉን ተናጋሪ ምግባር የሌለኝ
ተገርፎአል ተሰቅሎአል የምል ብቻ ሆንኩኝ" (ዘማሪት አዳነች አስፋው)

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሚያዝያ 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ