Get Mystery Box with random crypto!

+ እኛ ያላወቅነው + ................................................ | ግጻዌ

+ እኛ ያላወቅነው +
..............................................................
    እመቤታችን ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በሥላሴ ኅሊና ታስባ ስትኖር ሥራዋ በጎደለው መሙላት ነበር። እርሷ ከፍጥረት ሁሉ በንጽሕና የተሟላች ስለሆነች ዘወትር እኛ ባጎደልነው ትሞላለች። በአምላክ ኅሊና የታሰበችውም በኃጢአት የምንጎድለው እኛን ለሟሟላት ነበር። ዕድሜያቸው የገፋና ልጅ በማጣታቸው በኃዘን የጎደሉትን ቅዱሳን አባትና እናቷን በደስታ የሞላች እመቤታችን ናት። በሶስት ዓመቷ አባትና እናቷ በስስት ዓይናቸው የሚያዩዋት ልጃቸውን ወደ ቤተ መቅደስ ሲወስዷት አሁንም ቤተ መቅደሱን አሟላችው። እርሷ ከመግባቷ በፊት ገነት ሊያስገባ የማይችል መሥዋዕት ሲሰዋ የነበረበትን አማናዊ የክርስቶስ ሥጋና ደም እንዲሰዋበት በማድረግ የዘለዓለም ሕይወት የሚያሰጥ ቤተ መቅደስ አድርጋዋለችና።

   እመቤታችን ሰርግ ስትጠራ እንኳን ይህን የሟሟላት ሥራዋን አልዘነጋችም። በቃና ዘገሊላ ዕለት ከልጇ ጋር የተገኘችበት ሰርግ ለእኛ ምን መልዕክት ያስተላልፍ ይሆን? እርሷ ወይኑን የሞላችው ተፈልጋ ሳይሆን እርሷ ራሱ እንደጎደለ አውቃ ነው። የትህትና እናት የሆነች፤ እንደርሷና ልጇ በዚያ ሰርግ ውስጥ የከበረ ተጋባዥ ባይኖርም ከሰርጉ ግርግርና ድግስ ይልቅ ያለውን ጉድለት ለሟሟላት ዓይኗን ከአስተናጋጆቹ ጋር አደረገች። ወይን እንደጎደለ ሳይነግሯት በፍጥነት የሟሟላት ሥራዋን ጀመረች። ሙሽራው እንኳን ያላወቀውን ጉድለት ቶሎ በአማላጅነቷ ሞላችው።

    ልክ እንደ ሙሽራው እኛስ ስንት ያላወቅነው ጉድለት ይኖር ይሆን? ማርያም ሆይ ከሀብት ጥግ፣ ከዕውቀት ጥግ የደረስን ሲመስለን፣ "ሁሉ ነገር ሙሉ ነው" ብለን የቆምን ሲመስለን ስንቴ "ወይን እኮ የላቸውም" ብለሽልን ይሆን? ልጅሽስ ስንቴ "አንቺ ሴት ካንቺ ጋር ምን አለኝ?" ብሎ ያልሽውን ሁሉ ፈጽሞልሽ ይሆን? ስንቴ እኛ ሳንጠይቅሽ ወደ ልጅሽ አማልደሽን ይሆን?

   ወላዲተ አምላክ ሆይ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ሙሽራው ለሁሉም ይበቃል ብሎ ያሰበውን ወይን በአቅሙ አዘጋጅቷል። ሳያስበው ግን ወይኑ አለቀ። አንቺ ግን በዚያ ስለተገኘሽ በአማላጅነትሽ ሞላሽለት። እምአምላክ እናታችን አንቺ ያለሽበት ጓዳ፣ አንቺ ያለሽበት ሰርግ፣ አንቺ ያለሽበት ሀገር ሁሌም የተሟላ ነው። እምዬ እባክሽን ዘወትር ከእኛ አትለይን። እኛ በቻልነው እንሰራለን፣ በቻልነው እንማራለን፣ በቻልነው አምላክን እናገለግላለን። አንቺ ግን ሙሽራው ያላወቀውን ጉድለት እንደሞላሽ እኛም ያላየነውና ያላወቅነው እልፍ ጉድለት አለና አንቺ ሙይልን። እመቤታችን እኛም እንደ ብልህ ሰርገኛ እንጠራሻለን። ከነልጅሽ በሥራችን፣ በትዳራችን፣ በትምህርታችን፣ በሕይወታችን ሁሉ ታደሚልን። ቢርበንም ያንቺን ስም ስንጠራ ከበላው በላይ እንጠግባለን። ብናለቅስም ያንቺን ስም ስንሰማ ዕንባችን ይታበሳል። ዘወትር ኃጢአት በማሰብ የሚኖጉደው ሀሳባችን አንቺን ስናስብ ግን ዕረፍትን ያገኛል። እምዬ ማርያም ዘወትር በኃጢአት ውኃ የምንሞላውን ሰውነታችንን ልጅሽ ወደ ጽድቅ ወይን እንዲለውጥልን ለምኝልን።
.............//........//.........//....................
ዲያቆን ዮሐንስ ደረጀ
ጥር 12/2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ

  @dnJohannes
@dnJohannes 
@dnJohannes 
@dnJohannes