2022-04-21 17:00:03
☞ ዝክረ ኸሚስ #6
-
መሀባ
-
አንዳንዶቻችን መሀባ ፍቅር የሁሉም ነገር ጅማሮ ፣ የመድረስ ሁሉ መነሻው እንደሆነ
ዘንግተነዋል ። እንኳን የሰው ልጅ ቀርቶ የእህል ቡሆ ‘ንኳ ለምጣድ ቢደርስም ሙሀቻው
እርሾ አይኖረውም ። " ኺትማ ድረስ ያልዘለቀ እንኳን መሀባ ቡንም ደግ አይደለም ። "
ብላናለች ሙሂቧ አቲቃችን ... መሀባ የደግ እድል በር ነው ። የሸጋ እጣ ደጃፍ ነው ፣
የእህል ውሃ መፍለቅለቂያ የዱንያ ሰታቴዋ ነው ። ተውበትን ( ንሰሃን ) ማስታወሻ ነው ።
የተጥራራ ኒያ ሸጋ ሀርፍ ፈትሎ " ያረሂም " የሚያስለፈልፍ ያብጀልኝ ደጅህን ማዜሚያ ነው ።
የጀነት መሻገሪያው መሰላልም .... መሀባ ፣ ፍቅር ።
---
.
ወቅቱን ነው አሉ ።
.
ያ የጎጋ ቅኝት ፣
በቁርበቱ ዜማ ፣
በደግ እድል በሩ ፣
በእጣው ጆሮ ግርጌ ፣
ተንጓጉቶ አንዳልነበር የገረረው ለዝቦ የጠናው ገራለት፣
ዱንያ አውታሩ ብዙ ስልት እየለወጠ ለስልሶ አዜመለት።
.
( ማነው ? አይባልም ... ! )
.
ካልሆነም ንጋቱ ፣
ካልገጠመም ምሽት ፣
ታጓጉል እሮሮ አፍታ ሳያላዝን ፣
ቀን ሰባራ ፍርዱን በመሀባ ፈጅር ይንጋልኝ እያለው፣
ሰው ብሎ ያለው ነው ... የመቸሩ ጤዛ ደጁን የበቀለው።
----
አንደዎ ሸህ ናቸው ። ደረሳቸውን ለሽንታቸው ማዳረቂያ ( ለኢስቲብራዕ ) የሚሆን ጠጠር
ድንጋይ ይዞላቸው እንዲመጣ አዘዙት አሉ ። ደረሳውም በጠጠሩ ፋንታ ትልልቅ ድንጋይ
በትክሻው ተሸክሞ መጣና ፊታቸው ላይ አስቀመጠው ። የዛኔ ሸህዮው " ኧረ አኸይ ምነው
አንተዬ ይህንን ምን ላደርገው ነው ለመቀመጫ አላልኩህ " ሲሉት « እነሸህ ላንቱ ትንሽ
ነገር እንደት ብየ ይዤ ልምጣ ! » ብሎ መለሰላቸው አሉ ። # መሀባ
⇩
አባቴም እንዲህ ሲሉ አዳምጫለሁ ። አንድ ቀን ከቁርአን ቤት ሸሆቹ ገርፈውኝ እያለቀስኩ
ቤት ገባሁ ። ምን ሆነህ ነው ? ተባልኩ ። " ሉህህን ከትክሻ ለምን አወረድክ ብለው መቱኝ "
አልኩ አቀርቅሬ ። ( ሉህ ) ከእንጨት የተሰራች መድ ቀለም እያጠቀሱ በሽንበቆ ስንጣሪ
ገላዋ ላይ ተከትቦባት ተፅፎባት ጀማሪ ልጅ አሊፍ ብሎ የሚቀራባት ማንበቢያ ናት ።
ጠፍጠፋ ሆና ከጫፍ እና ከጫፏ ተቦርቡራ ገመድ ገብቶባት ከትክሻ ትንጠለጠላለች ።
አባቴም እንዲህ አሉኝ ። « እኔ በደረስነቴ በሸሆቹ ብትር አላለቅስም ። የሸሆቹ ብትር
ያሳድጋል ። የትልቅ ሰው ቁጣ በረካ አለው ። » ካሉኝ ቡሀላ አብሯቸውቤት ለተቀመጠው
ሰው እንዲህ አሉት ። « ምን የዛሬ ልጅ አዳብ የላቸው ። እኛ ስንቀራ ሸሆቻችን ካላዋጡን
ቂረዐቱ አይያዘንም ነበር ። » ሱብሃነሏህ ... # መሀባ
----
መሀባ የሰውነት ግንዱ ዛፉ ነው ፣ ሓድራ ቅርንጫፉ ጥላው ነው ። ሓድራም ገበያ ነው
ያደባልቃል ። እንደኒያችን እንደቅዋችን የነፍስ ቀለብ የምንሸምትበት ። ሸሬታው ኸለዋ
መጅሊስ ነው ። እገሌ ተገሌ በሚል መኩራራት ሆሳ ጥላ ሓድራ ታዛውን አይዞርበትም ።
የእኔ እንዲህ ነኝ የሚል የመኮፈስ አዛ ጠለሽ ሓድራ ቀዬውን አይጥልበትም ። ሰው በመሆን
ብቻ በመርሀባ አደጌር የሚታደሙባት የፍቅር ሰርግ ያብሮነት ድግስ ነው ። ተጥራርተው
ለአቅል የሶብር ውዱእን ተጅዲድ ( እድሳት ) የሚፈጠምባት የቀልብ ወጌሻነትም ዳኢም
አሺት ነው .... መሀባ ።
.
ዛሬ ዛሬ የሓድራን ልቅና ፣ የመሀባን ደረጃ ፣ የምናይበት መልኩ ያበግናል ። « ታልደረሱ
አይደረስም ! » ቢሆንም ነገሩ ፣ ግን ክረምቱን ሳያዩት ስለወንዙ አካሄድ ያለሸርጡ ያለሃቁ
በራስ ቢሆን ግልብ የፈትዋ ኩሬ እንቀላቅልበት ማለቱን ስንሰማ ። አንዲት የዘማቾች
የሓድራ ስንኝ ድንቅ ትልብናለች በጫሌ ቀበሌ ነው ።
አርሂብ ተብሎ ደግ ሳይታደም ፣
ሓድራ አይገባም በመቀዳደም ።
-
ግደለም ሰው ማለት አያከስርም ጎበዝ ። አተረፈ አሉ ። ማን ? " ሰው ብሎ የገበየ " መገን
። .... ይቅናን ያቀናን ። መሀባም ሓድራ ነውና ቅሉ የገባያም ገድ አለውና .... ተገዱ
ሳይታገዱ የወንድም ቁናው ላይንገረበብ ቲም ያለው ሂድያ ይስጠን ። # አሚን
.
ሀቢቢ ... ረሱል ሶለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል « አንድ ወንድሙ የሚወደውን
ነገር በማግኘቱ መደሰቱን የገለፀለት ሰው የትንሣኤ ቀን ልእልናው ከፍ ያለ አላህ
ያስደስተዋል »
« መልካምን ነገርን ትንሽ ናት ብለህ አትናቅ ።
ወንድምህን ፈታ ባለ ፊት ማግኘት ቢሆንም እንኳ » ሙስሊም ሙስሊም ወንድሙን ሲያገኝ
እሱን በማግኘቱ ብቻ
ከምንም በላይ መደሠትና ደስ መሰኘቱንም በፊቱ ላይ
ማስነበብ ይኖርበታል ። የወንድም የወዳጅ ሀቁን ስንቶቻችን እናውቀዋለን ።
-----
ያረብ
።።።።።።
በአሪፎች ቅልስ ... ከውንህ ይሞጠላል ፣
በተቅዬች ግርዶሽ ... ሀምድ ይንከባለላል ፣
ያመሰጋኝህ ግብር
መርሀባን ሲታደል ...
ቀኑን ሊደላደል - - ምንዳው ሲሞናደል ...
እዝነትህ ሲዘንበው - - በረካህ ሲጎርፈው፣
ሰው ብሎ ይተማል ነፍስያ ሳይጠልፈው።
..
ምናለ ጌትዬ ...
.
ስለሰው ብባባው ፣
ስለሰው ባነባው ፣
ነክሮኝ ብንቧችበት - - ባህሩን ብዋኝበት ...
ሰው ብሎ ሰው ሊሆን ሰውነት ካለበት ።
ምናለ ...
( እኔም በተመኔ በቀኔ ብቃና ... ! )
በገረረው ንጋት ...
ወዙ በተላሰ ድርቅና ሰንጥቆት በተፍረከረከው ፣
የሙሂቡን ኪታብ ገልጦ ካለመቅራት ...
አይኔን በገለጥከው - - ልሳኔን ባዳንከው ?!
ሓድራ መሀል ውዬ - - ሓድራ መሀል ባድር ፣
በቻልኩት ዘምቼ ፣
ከዘመኔ አልቦ ላይ - - የቀልቤን ብሰድር ?!
..
ኸሚስ አባ መደድ ፣
ኸሚስ አባ መውደድ ፣
የሓድራ ወናፉን ባድማሱ ሲያጋግም ፣
ምሽቱን ኮልኩሎ እየገሰገሰ ህዋው ሲያስገመግም፣
እየቀጠቀጠ ፣
ደግ እያቀለጠ ፣
ሆሳን ጊዜ ‘ንዲቆርጥ - - የዛገው ቀን ሊሳል ፣
ሞረድ ያዘለው ለይል ...
ሰው በሚል ቡራቁ ከሚኔው ይደርሳል ።
.
የዛኔ ...
ያን የማይሸርፈውን ፣
የመኣና ‘ጀታ አስጨብጠኝ አንተው ፣
ሰው ብዬ ቀን ስዬ ሰው ልሁን እንደሰው ።
..
ምናለ ጌትዬ ...
አንተ ላይሳንህ - - በትናንት መከለስ ፣
በሙሂቦች ቀለም - - በደግ መሰለስ ፣
( አኔም በተመኔ በቀኔ ብቃና ... ! )
በገረረው ንጋት ...
ወዙ በተላሰ ድርቅና ሰንጥቆት በተፍረከረከው ፣
የሙሂቡን ኪታብ ገልጦ ካለመቅራት ...
አይኔን በገለጥከው - - ልሳኔን ባዳንከው !?
ሓድራ መሀል ውዬ - - ሀድራ መሀል ባድር ፣
በቻልኩት ዘምቼ ...
ከዘመኔ አልቦ ላይ የቀልቤን ብሰድር ?!
..
ምናለ ... ?!
_Semir ami
@semiraklu
3.3K viewsسمير ايمي, 14:00