Get Mystery Box with random crypto!

በዓለ ክብሩ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ••●◉ ✞ ◉●•• ነቢዩ | የገኃነም ደጆች አይችሏትም❗️

በዓለ ክብሩ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል
••●◉ ✞ ◉●••
ነቢዩ ዳንኤል ዐይኖቼንም  አነሣሁ አለና አስከትሎ እነሆም በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ፡፡ አካሉም እንደ ብረሌ ይመስል ነበር፤ ፊቱም እንደ መብረቅ አምሳያ ነበረ፤ ዐይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፣ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ፡፡…ይህንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኀይልም አልቀረልኝም፤ ክብሬም ወደ ውርደት ተለወጠብኝ ኀይልም አጣሁ፡፡ የቃሉንም ድምፅ  ሰማሁ፤ የቃሉን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምደር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ አለ፡፡ዳን 10÷5-9
••●◉ ✞ ◉●••
ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ብሎ የተናገረው የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤልን አስፈሪ ግርማ በተመለከተ ጊዜ ነበር፡፡ የዚህ መልአክ ግርማ የአምላክን ግርማ ይመስላል፡፡ ይህን ለመረዳት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ መለኮቱ ለወንጌላዊው ዮሐንስ የተገለጠበትን መገለጥ መመልከት በቂ ነው፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእይ ስለተመለከተው የክርስቶስ ግርማ ሲናገር ከኋላዬም እንደ መለከት ድምፅ ያለ ታላቅ ድምፅን ሰማሁ፡፡…የሰው ልጅ የሚመስልን አየሁ፤ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ የሚደርስ ልብስ የለበሰ ፣ ወገቡንም በወርቅ ዝናር የታጠቀ ነበር፡፡ራሱና የራስ ጠጉሩም እንደ ነጭ የበግ ጠጉር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፡፡እግሮቹም በእሳት የነጠረና የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ብዙህ ውኃ ድምፅ ነበረ፡፡… ባየሁትም ጊዜ ከእግሩ ሥር ወደቅሁ አንደ ሞተ ሰው ሆነሁ አለ፡፡ራእይ 1÷2-17 በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ቅዱስ ገብርኤል በግርማው አምላኩን እንደሚመስል አንረዳለን፡፡የስሙም ትርጓሜ የሚያስዳው ይህን እውነታ ነው፡፡ ገብርኤል ማለት አምላክ ወሰብእ ማለት ነውና፡፡
••●◉ ✞ ◉●••
ቅዱስ ገብርኤል በብሉይ ኪዳን በቅድስና ሕይወት ለተጋውና በገዢዎች ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ያደረበት ሰው(ዳን 5÷11)ተብሎ ለተመሰገነው ለነቢዩ ዳንኤል ማስተዋልንና ጥበብን የሰጠ መልአክ ነበር፡፡ ለዚህ ነቢይ እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጆችን ከሰይጣንና ከሞት ባርነት ነጻ ሊያወጣቸው ሰው እንደሚሆንና ሰማይንና ምድርን አሳልፎ በቅዱሳን ላይ ነግሦ እንደሚኖር በምሳሌ ገልጾ ያስተማረው መልአክ ነው፡፡ዳን 9÷21-22) አሁንም ነቢዩ ዳዊት አቤቱ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ብፁዕ ነው፡፡ በልቅሶ ሸለቆ በወሰንኸቸው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና፡፡መዝ 83÷5-6 እንዳለው በቅድስና ሕይወት በመጽናታቸው ምክንያት ቅዱስ ገብርኤል መምህር የሆናቸው ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው፡፡ የእኛ እውቀት በሰማያት ከትመው ካሉት ቅዱሳን መላእክት እውቀት ጋር ሲነጻጸር እኛን እንደ ሕፃናት ያደርገናል፡፡ እኛ የእነርሱን እውቀት ገንዘባችን የምናደርገው በትንሣኤ ነው፡፡
••●◉ ✞ ◉●••
ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ዛሬ በመስታወት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን ያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፡፡ አሁን በከፊል ኋላ ግን እንደተገለጠልኝ መጠን ሁሉን አውቃለሁ(1ቆሮ 13÷12) ብሎ አስተማረን፡፡ ስለዚህም እውቀታችን የተሟላ እንዲሆንና ሰይጣንን ለመቃወም እንድንበቃ የቅዱሳን መላእክት የእውቀት ድጋፍ በእጅጉ ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ከእኛ ይልቅ ሳጥናኤልን የሚያውቁት እነርሱ ናቸውና፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን በእውቀታቸው እኛን እንዲረዱን ለእያንዳንዳችን  ጠባቂ መልአክትን ሰጠን፡፡ማቴ 18÷10፤ሉቃ 13÷6-9
••●◉ ✞ ◉●••
ቅዱስ ገብርኤል ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ለተጠሩት መንፈሳዊ እውቀቱን የሚያካፍላቸው መልአክ ብቻ አይደለም፤ ለእግዚአብሔር በመገዛታቸው ምክንያት ከአላውያን ገዢዎች ከሚደርስባቸው መከራም የሚታደጋቸው መልአክም ነው።ንጉሥ ናብከደነፆርም ሠልስቱ ደቂቅ እሳቱ አንዳች ጉዳት ሳያደርስባቸው በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ ከእነርሱ ጋር የሰው መልክ ያለው ነገር ግን አምላክን የሚመስል መልአክ ተመለከተ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሊቀ ካህናቱን ቀያፋን ፊቱን ጸፍቶ አፉን ከፍቶ ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡምን (ዮሐ 11÷49) ብሎ እንዳናገረው እንዲሁ ናብከደነፆርንም እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን በዚያ አያለሁ ምንም የነካቸው የለም፤የአራተኛውም መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል ብሎ እንዲናገር አደረገው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅን መልክ ያለው ያለው በኋላም መልአክ ብሎ የተናገረለት ቅዱስ ገብርኤልን ነበር፡፡ እርሱ ስለመሆኑ ለነቢዩ ዳንኤል በተገለጠበት ግርማ ማረጋገጥ እንችላለን።
••●◉ ✞ ◉●••
ናብከደነፆርም ወደ እሳቱ እቶን በመቅረብ እነዚህ ብላቴኖችን እናንተ የልዑል አምላክ ባሮች ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው፡፡ እነርሱም ከእሳቱ ወጡ ሹማምንቱና መኳንንቱ፣ አማካሪዎችና የአገር ገዢዎች ሁሉ እሳቱ በእነዚህ ብላቴኖች ላይ አንዳች አቅም እንዳልነበረው፣ ከጠጉራቸው ቅንጣት አንዱን እንኳ እንዳላቃጠለው፣ ሰናፊናቸውም እንዳልተለወጠ፣ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው ተመለከቱ፡፡ ንጉሥ ናብከደነፆርም መልአኩን ልኮ ያዳናቸውን የእነዚህን ቅዱሳንን አምላክ አመሰገነ፡፡ በእነርሱ አምላክ ላይም የስድብን ቃል የሚናገር ሰው እንደሚገደልና ቤቱም የጉድፍ መጣያ እንዲሆን አዋጅ አስነገረ፡፡ አዛርያ አናንያ ሚሳኤልም በንጉሡና በሹማምነቱ ዘንድ ሞገስ አገኙ በክብርም ከፍ ከፍ አሉ፡፡ዳን ም 3 በሙሉ
••●◉ ✞ ◉●••
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን መንጎቹዋ የእምነትን ፍሬ ከእነዚህ ብላቴኖች ተምረው እግዚአብሔርን በማምለክ እንዲጸኑና የመልአኩን የቅዱስ ገብርኤልን ተራዳኢነት እንዲረዱ በታኅሣሥ 19 ቀን ይህን ዕለት ትዘክራለች፤ በታላቅ ድምቀትም ታከብረዋለች፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እምነት በድርጊት ሊታይ የሚገባው ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አምናለሁ የሚል ሁሉ ካመነበት ጊዜ አንስቶ ክርስቶስን መስሎ ለመኖር ሊተጋና መስሎ ሊመላለስ ይገባዋል፡፡ በሠልስቱ ደቂቅ  የታየው እምነት በአንድ ጀምበር የተገነባ እምነት ሳይሆን ከልጅነታቸው ጀምሮ በአንድ እግዚአብሔር ታምነው በቅድስና ሕይወት በመመላለስ የመጣ እምነት ነው፡፡ እነዚህ ብላቴኖች በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙትን የድል አክሊል ተስፋ አድርገዋልና አርባ ዘጠኝ ክንድ ያህል የነደደውን የእሳት እቶን አላስፈራቸውም፤ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው ጽኑ እምነት በእሳት ተቃጥለው ለመሞት እንኳ አስጨከናቸው፡፡ እንዲህም ሆነው በመገኘታቸው በእምነታቸው እግዚአብሔርን ደስ አሰኙት፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ባለሟሉን ቅዱስ ገብርኤልን በመላክ ከእሳቱ እቶን ታደጋቸው፡፡
══════◄✣••✥••✣►══════
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይሁን ። ከምታልቀዋ ከዛሬዋ ቀን እስከማይፈጸም ዘመን ። ከደካማው ልባችን እስከ ጸናው ሰማይ። ለዘላለሙ አሜን
══════◄✣••✥••✣►══════

@Geb19bot @efr21
@Geb19bot @eotc27