Get Mystery Box with random crypto!

የሙዚቃን አክሊል የደፋ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ (ታመነ መንግስቴ ነኝ_የአፍሪካ ሕዳሴ ቴሌቪዥን አገልግ | እዚህ ቤት

የሙዚቃን አክሊል የደፋ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ

(ታመነ መንግስቴ ነኝ_የአፍሪካ ሕዳሴ ቴሌቪዥን አገልግሎት ዘጋቢ)

ኢትዮጵያዊያን ስለዚህ ድምጸ መረዋ ዜመኛ፣ገጣሚ እና አቀንቃኝ ምንም በሚባል ደረጃ አያውቁም።የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ሬዲዮ፣ቴሌቪዥን ወይም ጋዜጣ ስሙን አያነሱም ወይም ሙዚቃዎቹን አይጋብዙም።


የእሱን ስም ጎግል በሚሰኘው የእውቀት ባህር ውስጥ ጽፎ የፈለገ ሰው የረባ መረጃ አያገኝም።ሰውየው ግን በግሉ ዘጠኝ አልበም ከሌሎች ጋር ተጣምሮ አንድ የሙዚቃዎች ጥቅል ብቻቸውን እየተብሰከሰኩ ለሚያደምጡት አድናቂዎቹ አቃምሷል።


ዘፋኙ ዓለምን በሥጋ ከተለየ በሗላ ዘፈኖቹን "You Tube"በተሰኘው የድምጽና ምስል መጫኛ የሰቀሉ በሚሊዮኖች በተጎበኙ የኪነት ሥራዎቹ ብዙ ዶላሮችን ሸቅለዋል።

እሱ እንዲህም እንዲያም ነው!

የዛሬው የሰንበት ወግ እንግዳ የሙዚቃን አክሊል በልዩ አዚያዚያም ተሰጥኦው ደፍቶ በአገሩ ሰዎች ልቡና ላይ የነገሰው አክሊሉ ስዩም ነው።

አንድ የዚህን ጠቢብ የሙዚቃ ጣዕሞች በድረ ገጹ ዘግኖ ለአድማጮቹ ያጋራ ጦማሪ ስለዘፋኙ  በብቸኝነት አራት አጫጭር አንቀጾች ወርውሯል።

ጦማሪው አክሊሉ ስዩምን"Aklilu Seyum was one of the most talented singers and songwriters from Ethiopia" ብሎ ይገልጸዋል።

እንደተባለውም አክሊሉ ታላቅ እና ተራቃቂ ዘፋኝ ነው።ዜማው እንደ ቀትሩ የጣና ሞገድ ለስለስ ብሎ በአዕምሮ ግድግዳ ላይ ይንሸራሸራል።ዚያዜም በሙዚቃ መሳሪያዎች ብቻ የሚደመጥ ሙዚቃ እንጅ ግጥም ገብቶበት የሰው ድምጽ የታከለበት አይመስልም።በዜማ ጣዕሙ ሲሳካለት ለታዘበ "ሰውየው የት ተወልዶ ቢያድግ ከየትስ የዜማ ጣዕም ቢቀዳ ይሆን?" ብሎ ይጠይቃል።

ብቸኛው ስለ አክሊሉ ስዩም የተፃፈው ጦማር እንደሚለው ይህ ጥዑም ዜመኛ ተወልዶ ያደገው በዜማ መዲናዋ ጎንደር ከተማ ነው።ጎንደር የዜማ ከፍታ ናት።

"በቆሜ አራራዩን ያላንጎራጎረ
ደብረ ታቦር ተክሌን ያላስመሰከረ
በአንዳቤት ቁም ጽሁፍ መካን ያልሞከረ
ጎንደር በአንች ሞያ ያልተወዳደረ
መቼ እንደተማረ ይቆጠር ነበረ!?"

የሚባልላት የ17ኛው ክፍለ ዘመን የዐለማችን የልህቀት ማዕከል በተለይ በተለይ ዜማ ባህላዊ ሀብቷ ነው።ዛሬም "አረጀች" እየተባለች በምትታማው ጎንደር ከተማ የተገኘ ሰው ወደ ማታ ከአበቅ የለሽ እስከ እንየ ታከለ ፣ከባላገሩ እስከ አንድ ሌላ አዝማሪ ቤት ብቅ ቢል የዜማን ጣዕም ከእኒያ ጠቢባን አዝማሪዎቿ ይልሳል።

አክሊሉ ስዩም እንዲህ ሲያዜም ከአባቶቹ፣ከአያቶቹ፣ከቅደመ አያቶች የዘገነውን ጥበብ እየደጋገመ እንጅ አዲስ ነገር ፈጥሮ አይደለም።

እሱን የሚያስደንቀው ያንን የአብርሆት ዘመን የጎንደር ጥበብ ከአርባ አራቱ አድባራት ቀድቶ ለራሱ ሥራ በኪናዊ ለዛ አሟሽቶ ማቅረቡ ነው።

ለአፍታ በምናብ ሶስት ዓመታትን ወደ ሗላ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገነተ ልዑል ቤተ_መንግስት እንመለስ።በእዚያ የዚህ ዝግጅት ቀማሚ የጠዋት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሰርቶ በእጅ የምትያዝ ትንሽየ ሬዲዮውን ጮክ አድርጎ ከፍቶ ይጓዛል።

አንድ በዕድሜ ጠና፣በአቋም ፈርጠም ያሉ ፊታቸው የሚያበራ ጎልማሳ አስቆሙት።በትዝታ እጅግ እጅግ ወደሗላ ተመልሰው ነጎዱ።የዚያኔው የጋዜጠኝነት ተማሪ ባለ ሬዲዮ እያያቸው የትዝታ ጎርፍ በላቸው።

"ጋሸ ምን ሆነው ነው?" አላቸው።

"ከአክሊሉ ስዩም ጋር በኤርትራ ምድር አብረን ነበርን።እንዴት ያለ መልካም ሰው ነበረ መሰለህ? ጓደኛየ ነበር።ከእነ ጋሻው አዳል፣'አንች ወረተኛ'ን ከሚዘፍነው ዘፋኝ ጋር ይዘፍኑልን ነበር።"እያሉ ይብሰከሰኩ ጀመር።

አክሊሉ "ይሻገራል ይሻገራል ልቤ
            ናፍቆት ነው ቀለቤ"
የሚለውን ዘፈኑ አዚሞ ከሬዲዮው ሞገድ እየወረደ ነው።

ሻምበል ሳሙኤል ግን የትዝታ ክር እያጠነጠኑ  ከሃያ ዓመት በፊት መገንጠሏን አምነው ወደተለዩዋት አገረ ኤርትራ በሃሳብ ነጎዱ።

እናም አክሊሉ ስዩም በፖሊስ ኦርኬስትራ ስር ታቅፎ ማቀንቀን ከጀመረበት የ18 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች በናቅፋ፣አልጌና፣አፍአበት፣ሳህል ጦር ሜዳዎች ኤርትራን ከ"ገንጣይ አስገንጣዮች" ሊያድን ለሚዋደቀው የኢትዮጵያ ጦር እየሄደ ሳይዘፍንለት አልቀረም።

ሻምበል ሳሙኤል ሺህ መላሽ ለአዘጋጁ  ስለ አክሊሉ ስዩም እንደነገሩት አዲስ አበባ የምትኖር ልጅ አለችው።የኢትዮጵያዊያንን የፍቅር ትካዜ ለዓመታት በተለያዩ ርዕሶች ሲያዜም የኖረው አክሊሉ ስዩም አፍቅሮ፣ተፈቅሮ፣አስርጎ ስለማግባቱ ዝርዝር መረጃ የለንም። ሻምበል ሳሙኤል ግን ስለ አስገራሚው የፍቅር ታሪኩ የሚያውቁት አላቸው።

ብቻ ብቻ ዘፈኖቹ ብቻውን በናፍቆትና የሰው ረሃብን ሲሰቃይ የኖረ ኢትዮጵያዊ እሮሮዎች ይመስላሉ።ዜማዎቹም በአብዛኛው ተመሳሳይና በማይም ሰው አረዳድ አራራይ ቢጤ ናቸው።

አክሊሉ በዚች ምድር የኖረው አምሳ ስድስት ዓመታትን ብቻ ነው።በ1946 ተወልዶ በኢትዮጵያውያን የዘመን ቀመር 20ዐ2 ዓመተ ምህረት ዓለምን ተሰናበታት።

ይህን በሙዚቃዎቹ ልዕልና በአድናቂዎቹ ዘንድ በምስጢር የሚወደድ ዘፋኝ "አውቀዋለሁ"የሚሉ ዘፋኞች፣የሙዚቃ ስንኝ ቀማሚዎች፣አቀናባሪዎች ብዙ አይደመጡም።

ምናልባትም ከ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት በሗላ ወደ እስራኤል አገር ስለሄደ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት የ1970ዎቹ ዝነኛ ዘፋኝ ስሙ እየደበዘዘ መጥቷል።ቢሆንም ግን አክሊሉን ከዘመናቸው ጋር እያሰላሰሉ አድናቂዎቹ እየተመሰጡበት አሉ።

የዛሬን አበቃን

ከሰንበት ወጎች ጋር ነበራችሁ።ስለ ጣፋጩ ዘፋኝ በቅንነት የሚያውቁትን የነገሩንን የአሁኑን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ፣የዚያኔውን የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሻምበል ሳሙኤል ሺህ መላሽን እናመሰግናለን!

@Gazetaw