Get Mystery Box with random crypto!

ሀምራ አልአሰድ ላይ ... (ፉአድ ሙና) . ቀኑ ለሙስሊሞች ከባድ ነበር። አይደለም ምዕመኑ ውዱ ነ | Fuad Muna (Fuya)

ሀምራ አልአሰድ ላይ ...
(ፉአድ ሙና)
.
ቀኑ ለሙስሊሞች ከባድ ነበር። አይደለም ምዕመኑ ውዱ ነብያቸው እንኳን ከጥቃት አልተረፉም። አብላጫው ሶሀባ ሰውነቱ ክፉኛ ቆስሏል።

ጦርነቱ የዕሁድ ጦርነት ነበር። ሙስሊሞች ድልን የተነሱበት ... ውድ ሰሀባዎች የተቀጠፉበት ጦርነት! ሙሽሪኮች በበላይነት መንፈስ የበድርን ጦርነት ቂም መወጣታቸው ቢያስደስታቸውም፤ ድላቸው ግን ሙሉ ጠዓምን አልሰጣቸውም።

«ወዮልን! ሙሀመድን ሳንገድል .... ሴቶቻቸውን ሳንማርክማ ምኑን አሸነፍነው?» ሲሉ ራሳቸውን ለዳግም ጥቃት አደራጁ።

የሙሽሪኮች ጦር እየመጣ የመሆኑ ዜና ከውዱ ነብይ ዘንድ ደረሰ። ባልደረባዎቻቸው በከባዱ የቆሰሉባቸው ነብይ ጆሮዎች ይህን ዱብዳ ሰሙ።

ምን ያሉ ይመስላችኋል?

የቆሰለ ሰራዊታቸውን የሙስሊሞችን አለመዳከም ያሳይና አጋሪዎችን ይመክት ዘንድ ተጣሩ። በዚህ ጥሪ ላይ እንዲሳተፉ የተፈቀደላቸው ደግሞ እነዚያው የዕሁድ ተራራ ላይ ከባድ ስቃይ የደረሰባቸው የእሁድ ዘማቾች! ከደረሰባቸው ጉዳት አንፃር በሰው ተደግፈው የሚሄዱ ሰሀባዎች ጭምር ነበሩ።

አጋሪዎቹን ለማስቆም ስቃያቸውን እያስታመሙ ወደ ሀምራ አል አሰድ ተመሙ። በዚህ ጊዜ ሁኔታው ፍርሀት ያለበሳቸው ሙሽሪኮች በቀጣይ አመት ብንጋጠም ይሻላል ብለው ተመለሱ።

አላህ የእነዚህን ለነብሳቸው የማይሳሱ ሰሀቦች ጉዳይ አስመልክቶ በወህይ እንዲህ ሲል ጀብዷቸውን ተረከው።


الَّذِينَ اسْتَجَابُوا لِلَّهِ وَالرَّسُولِ مِن بَعْدِ مَا أَصَابَهُمُ الْقَرْحُ ۚ لِلَّذِينَ أَحْسَنُوا مِنْهُمْ وَاتَّقَوْا أَجْرٌ عَظِيمٌ

እነዚያ መቁሰል ካገኛቸው በኋላ ለአላህና ለመልክተኛው የታዘዙት ከእነሱ ለነዚያ በጎ ለሠሩትና ለተጠነቀቁት ታላቅ ምንዳ አላቸው፡፡


الَّذِينَ قَالَ لَهُمُ النَّاسُ إِنَّ النَّاسَ قَدْ جَمَعُوا لَكُمْ فَاخْشَوْهُمْ فَزَادَهُمْ إِيمَانًا وَقَالُوا حَسْبُنَا اللَّهُ وَنِعْمَ الْوَكِيلُ

እነዚያ ሰዎቹ ለእነርሱ፡- «ሰዎች ለእናንተ (ጦርን) አከማችተዋልና ፍሩዋቸው» ይሉዋቸውና (ይህም) እምነትን የጨመረላቸው «በቂያችንም አላህ ነው ምን ያምርም መጠጊያ!» ያሉ ናቸው፡፡


فَانقَلَبُوا بِنِعْمَةٍ مِّنَ اللَّهِ وَفَضْلٍ لَّمْ يَمْسَسْهُمْ سُوءٌ وَاتَّبَعُوا رِضْوَانَ اللَّهِ ۗ وَاللَّهُ ذُو فَضْلٍ عَظِيمٍ

ከአላህም በኾነ ጸጋና ችሮታ ክፉ ነገር ያልነካቸው ኾነው ተመለሱ፡፡ የአላህንም ውዴታ ተከተሉ፤ አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው፡፡
(2/172–174)

ይህም ገድል አላህን በምቾት ውስጥ ብቻ ሳይሆን አይታሰብም በሚባልበት ሁኔታ ውስጥ እንኳን ከልብ የማሳደር ምሳሌ ሆኖ ዘመናትን እየተሻገረ አለ።

አላህ ሁሌም በወደደው መንገድ ላይ ከሚቆሙ፤ እምነታቸውን በንፍቅና እና በክህደት ከማያበላሹ ደጋግ ባሮቹ ዘንድ ያድርገን።
.
@Fuadmu
@Fuadmu
ለአስተያየትዎ
@Fuadmubot