Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል.......7 (በእውነተኛ ታሪክ የተመሰረተ) አዘጋጅ፦ ፍቅርን በቃላት . . | 💕 ፍቅርን በቃላት 💕

<<ጠይሙ !>>


ክፍል.......7

(በእውነተኛ ታሪክ የተመሰረተ)

አዘጋጅ፦ ፍቅርን በቃላት
.
.
.
ልጆቼ ጋር እንኳን አልገባሁም: የመኝታ ቤት በራቸውን ዘግቼ ብቻ ተመለስኩ:: የማጠፋው ጊዜ የለኝም:: ተንደርድሬ የእጅ ስልኩን ከጃኬቱ ኪስ ውስጥ አውጥቼ ወደ መታጠቢያ ቤት አፈተለኩ:: በሩን ቆልፌ መጨረሻ ላይ የደወለው ቁጥር ላይ አፈጠጥኩ: የከተማው ኮድ ለስራ ሲላክ ከሚያርፍበት ሆቴል ስልክ ቁጥር ጋር ተመሳሰለብኝ:: በአጉሉ ስለላዬ ከራሴ ጋር እየተሙዋገትኩ መልእክቱን ለመስማት አንደኛውን ቁልፍ ተጫንኩት:: ገና የሴት ድምፅ ስሰማ ልቤ ወደሆዴ ተንሸራተተች: አቅለሸለሸኝ: ወበቀኝ: አዞረኝ:: እንደምንም ብዬ የተከደነው መፀዳጃ ላይ ተዘረፈጥኩ:: "ቤቢዬ..." አለች ሙልቅቅ ባለ ድምፅ "ምነው ጠፋህ? ስልኩን መቼም ታጠፋዋለህ ብዬ ነው ደፍሬ የደወልኩት:: መንገድ ስትጀምር ደውልልኝ...እሙዋዋዋ!" ጆሮዬን አላመንኩም...የምትስረቀረቀውን ሴትዮ አፌን ይዤ ደግሜ ሰማሁዋት "ምን?!" ለራሴው አንሾካሸኩ:: ለካስ ገደሉም ውስጥ ገደል ኖሮልኛል: በጥቃት ላይ ጥቃት:: ይህን ሁሉ ጊዜ ባሌ ስራ እየሄደ ነው ብዬ ስንቅ እያዘጋጀሁ ሌላ ሴት ጋ ኖርዋል ስልክ የከረምኩት: ቅናት እራሴ ላይ ወጣ:: "አፈር አባትዋ ትብላና" እየዛትኩ ቁጥሩን ተጫንኩት:: "ቤቢዬዬዬዬ....." አለች የጠይሙ ባሌ ሞልቃቃ...ፍንድቅ ብላ ስልኩን እንዳነሳች:: ምላሴ ተሳሰረ: በህልሜ ይሆን? "ሀሎ?! ባክህ አትቀልድ...ቂቂቂ" ትንፋሼ እየተቆራረጠ ለመሳደብ ሞከርኩ "አንቺ...አ-ን-ቺ...ር-ካ-ሽ" ስልኩ ተጠረቀመ: እኔ ግን ጆሮዬ ላይ እንደለጠፍኩት አፌን ከፍቼ ቀረሁ::

ማሰብ አቃተኝ:: ባሌ ወደሳሎኑ ሲመለስ ኮቴውን ሰማሁ:: አሁን ምንድን ነው የምለው? አይኑን እንዴት ነው የማየው? ለሱ እኔ አፈርኩ:: ጊዜ እየተሽቀዳደመኝ ነው: የኔ አይምሮ ደግሞ ለገመ:: ይህንን ስልክ መደበቅ አለብኝ: ግን የት? የት? የት? ባሌን ለማታለል የመፀዳጃ ቤቱን ውሀ ለቀቅሁት:: ሳጥኑን ከፋፍቼ እቃውን ሁሉ በደቂቃ ውስጥ አማተርኩት: እሱ የማይጠረጥረው ቦታ አጣሁ:: ባሌ ሲጣራ ሰማሁት...ምን አስቸኮለው? ስልኩን አጥቶ ይሆን? "መጣሁ" አልኩ መስኮቱን ለመክፈት እየታገልኩ:: ስልኩን በፎጣ ጠቅልዬ ወደውጭ አሽቀነጠርኩትና መልሼ ዘግቼ ወደሳሎን አመራሁ::

ተመልሶ ተቀምጦዋል:: ቶሎ ብሎ እጆቼን አየ: እንደተሸበረ ያስታውቃል:: ጠረጴዛው አጠገብ ቆሜ ተፋጠጥን:: አሁን ለቅሶ የለም: ጥላቻ ብቻ: እጆቼ ተንቀጠቀጡ:: በድንገት እንጣጥ ብሎ ተነሳና ወደመታጠቢያ ቤት ሮጠ:: እኔም ፈጠን ብዬ ከእጅ ቦርሳዬ ውስጥ ስልኬን አውጥቼ የቤት ቀሚሴ ኪስ ውስጥ ከተትኩት: ለክፉም ለደጉም:: ቅድም ከፍቼው የነበረውን ሳጥን በሀይል ሲጠረቅመው ተሰማኝ:: 

"ስልኬ የታል?" ወደሳሎን እየገባ አንባረቀ:: "የምን ስልክ?" አልኩ ረጋ ብዬ "ቀስ ብለህ ፈልገው: ምን አስቸኮለህ?" የሸር ፈገግታዬን ብልጭ አደረኩ: ሞኚትዋ ሚስቱ:: ወደበሩ ተንደረደረና በግራ በኩል የተሰቀሉትን ቁልፎቼን አነስቶ ኪሱ ከተታቸው:: "ስልኬን ካልሰጠሽኝ ..." የቀረውን አልሰማሁትም: ጭንቅላቴ ውስጥ የታመቀው ነገር ሁሉ ፈነዳ: ብሶት: ቅናት: ጥላቻ: ንዴት: ፍርሀት:: አጠገቤ ያለውን ወንበር አንስቼ ወረወርኩበት: ወደጎን ፈንጠር ብሎ አሳለፈውና አፈጠጠብኝ:: ይቺኛዋን ሚስቱን በጭራሽ አይቶዋት አያውቅም: ኧረ እኔም አላውቃት:: በሚያስፈራ ድምፅ አጉዋራሁ:: "አንተ ከኔ ሳይሆን: እኔ ከእንዳንተ አይነቱ ቆሻሻ ፍቺ እፈልጋለሁ...ው-ሻ!" ወደሱ እየተንደረደርኩ "ቁልፌን አምጣ!" ጮህኩ: ኪሱ ውስጥ ልገባ እጄን ስዘረጋ ሁለቱንም እጆቼን ጠርቅሞ ያዛቸው: መነቃነቅ አልቻልኩም:: "አ-ን-ተ...ግ-ፈ-ኛ" እንባዬ መዝነብ ጀመረ "እ-ኔ...ከልጆቼ ጋር እየታገልኩ ስ-ን-ቅ...ስሰራ የ-ከ-ረ-ም-ኩ-ት... ለ-ለ-ው-ሽ-ማ-ህ... ኖ-ር-ዋ-ል" አቤት ፊቱ ላይ ያየሁትን ድብልቅልቅ ስሜት!..ድንጋጤ: እፍረት: ሀዘን: ቁጭት:...ምንም አልተናገረም: እጆቼን ግን አጥብቆ ጠርቅሞ ያዛቸው:: ለመሳሳም እንደተዘጋጁ ፍቅረኛሞች ፊት ለፊት ተፋጠን ቆምን:: "ም-ን... በ-ደ-ል-ኩ-ህ... ይ-ህ-ን-ን... ያ-ህ-ል...ግ-ፍ" ተንሰቀሰቅሁ "ቤ-ቴ-ን... ት-ዳ-ሬን... ባ-ል-ኩ" እንባዬም: ንፍጤም: ለሀጬም ተደባልቆ ተዝረከረከ:: "አንቺ ምንም አላደረግሽም: እ-ኔ-ው...ነ-ኝ" አለ በጎረነነ ድምፅ:: አይኖቹ እንባ አቅረዋል: እጆቼን ጠርቅሞ እንደያዘ ወደጣራው አንጋጠጠ::
ይቀጥላል ...........

ማሳሰቢያ:- ይህን ፅሁፍ ከናንተ ጋር እኩል ክፍል ላይ ነኝ አደራ እጁ ላይ ስላለ ያነባል ብላችሁ አታስቡ።



ይቀጥላል .....


የመወያያ ግሩፑን ይቀላቀሉን
@ethio_lifes_group
@ethio_lifes_group
@ethio_lifes_group


╔═══❖• •❖═══╗
@fkrn_be_kalat
╚═══❖• •❖═══╝
4 any comment
@fkrn_be_kalat_bot
❥❥__⚘_❥❥