Get Mystery Box with random crypto!

የደማስቆው ኮከብ፤ የአልባኒያው ልጅ! **** «ከሰማይ ጠለል በታች በዘ | 🌹 የኢስላም ልጆች 🌻

የደማስቆው ኮከብ፤ የአልባኒያው ልጅ!
****
«ከሰማይ ጠለል በታች በዘመነ ሐዲስ እንደ ሸይኽ ሙሀመድ ናሲሩ አድ-ዲን አል-አልባኒ ስለ ሐዲስ ይበልጥ የሚያውቅ ሰው አላየሁም።» ሲሉ ሸይኽ ዐብዱል ዓዚዝ ቢን ባዝ መስክረዋል።
"ሸይኽ ሙሃመድ ናሲር አድ-ዲን አልባኒ" ይባላሉ!

ሸይኹ በ1914 ዓ·ል መገኛዋን ደቡብ ምስራቅ አውሮፓ ባደረገችው አልባኒያ ምድር "አሽቁደራ" በተሰኘችው ጥንቲቷ ከተማ ተወለደ። ምንም እንኳን ቤተሰቡ በዝቅተኛ ኢኮኖሚ ውስጥ የነበሩ ቢሆንም አባቱ ወደ ኢስታንቡል በማቅናት የተማረውን የሸሪዓ አስተምህሮት በሀገሩ ላሉ ወገኖች በማስተማር ያገለግል የነበረ ታላቅ ባለአደራ ሰው ነበር። በዘመኑ የተሾመው ገዥ መሪ [አህመድ ዙጞ] በሁሉም የህይወት ትግበራዎች ላይ ምዕራባዊያንን አርአያ በማድረግ የሀገሩን የአስተዳደር ስርዓት ወደ secularism(መንፈሳዊነትንና ሸሪዓን ያገለለ አለማዊ አገዛዝ) በመለወጥ ብዙ የጥፋት መስመሮችን ዘረጋ።
ሙስሊሟ የአልባኒያ ሴት በግድ ሒጃቧን እንድታወልቅ ፣ ወንዱም አለባበሱ ምዕራባዊያንን የተከተለ እንዲሆን ተደረገ። ብዙ… ብዙ… ብዙ ተደረገ። በዚያን ወቅት ስለ እምነታቸው የተጨነቁ፣ ስለ መጨረሻው መጥፎ ፍፃሜ የሰጉ ምስኪን የሀገሩ ህዝቦች ወደ ሌሎች ሀገራት መሰደድ ጀመሩ። የአልባኒ ቤተሰቦችም ስለ ሀገሩ ዕጣ ፈንታ በማሰብ በሀዘን ቢጨለጡም ምርጫቸውን ስደት አድርገው ሻም ወደምትገኘው የስልጣኔ ማዕከል "ደማስቆ" ገቡ።
ይህ ሀገሩን ለቆ የተሰደደው ልጅ "አል-ኢስዓፍ አል-ኸይሪይ" በተባለችዋ የደማስቆ ትምህርት ቤት ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ተማረ። ነገር ግን ከዚያ በኋላ አባቱ ትምህርቱን እንዲቀጥል አልፈለገም። ታዲያ እምነታዊ ትምህርቶችን የሚማርበት የተስተካከለ መደበኛ ፕሮግራም ቀረፀለት። ቁርአን፣ ተጅዊድ፣ ሰርፍ፣ የሀነፊያ መዝሀብ ፊቅሂን በማስተማር ይኮተኩተው ያዘ።
ልጁን ከራሱ በላይ ለማድረግ የሚታትር እንዲህ አይነት አባት ያስደስታል። የሀዲስ ጠቢብን የቀረፀ አባት መቼም ቢሆን አሻራው አይለቅም። ይህ ልጅ በአባቱ እጅ ላይ ቁርአንን በመሀፈዝ ለማኽተም በቃ ፣ ብዙ የትምህርት ዘርፎችንም ወረሰ። እንዲሁም አቅራቢያው ከነበሩት ሸይኾች የዓረብኛን ሰዋሰው ትምህርት ቀሰመ።
ወጣቱ እድሜው ወደ 20 ዓመት ገደማ ሲሆን ሸይኽ መሀመድ ረሺድ ሪዳ የሚባል ሰው ያዘጋጀው በነበረው "አል-መናር" ጋዜጣ ጥናት ተፅዕኖ ስር በመውደቅ ወደ ሀዲስና ስነ ሀዲስ ዘርፍ ጥናት በጥልቀት ይመራመር ገባ። በርግጥ አባቱ የሀነፊያን መዝሀብ አጥብቆ እንዲይዝ ይመክረውና በስነ ሀዲስ ጥናት ስር እንዳይገባ ያስጠነቅቀው ነበር። ወጣቱ ግን ሱንናን በግልፅና ትክክለኛ በሆነ መረጃ መከተል የሚሻ ስለነበር ጉዞውን በሀዲስ መስመር ላይ አደረገ። እጅግም ወደደው። ደማስቆ ውስጥ "ዟሂሪያ" በተሰኘችው ቤተ መፅሃፍት በቀን ውስጥ ለ12 ሰዓታት በዚህ ዘርፍ ጥናት ሲቸክል ይቆይ ነበር። ምግብ ትዝ ሲለው ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ ቤተ መፅሀፍት ውስጥ ነበር የሚመገበው። ሁኔታውን ሲመለከቱ የቤተ መፅሀፍቱ አስተዳደር በጥናቱ ጉዳይ እንዲበራታ ልዩ ክፍል አበጁለት። እጅጉኑ ለፋ! የሀዲስ ጠቢብ ለመሆንም በቃ! ሙሀዲስ(የሀዲስ ጠቢብ) የሚለው የማዕረግ ስም እንዲሁ የተወሰኑ ትምህርቶችን ላስተማረ ሰው የሚሰጥ ተራ ስም እንዳይመስላችሁ! ብዙ ልፋት ያስፈልገዋል።
(ከአሁን በኋላ ከሊቃውንት ተርታ ተሰልፏልና በአንቱታ ልጥራው)

ሸይኹ ደማስቆ ውስጥ ስማቸው በስፋት ይጠራ ጀመር። ለመጀመሪያ ጊዜ የፃፉትና በተደጋጋሚ ለህትመት የበቃው መፅሃፍ "ተህዚሩ አስ-ሳጂድ ሚን ኢት-ቲኻዚል ቁቡር አል መሳጂድ" ተሰኝቷል። ከዚያ በኋላ ስማቸው እጅግ ከመሰራጨቱ የተነሳ መዲና የምትገኘው ኢስላማዊቷ ዩኒቨርሲቲይ በስነ ሀዲስ አስተማሪነት አጨቻቸው። ለ3 አመታት መዲና ውስጥ ካገለገሉም በስተኋላ የሀዲስ ጥናታዊ ትምህርታቸውን ለማሟላት ወደ ደማስቆ ተመለሱ።
ሸይኹ እጅግ ይደንቃሉ። በሀዲስ ቁልመማ ኡማውን ሲያወናብዱ የነበሩ ቀጣፊዎችን በማጋለጥ የሱንና ጠበቃ ሁነው ነበር።
የሀዲስ ጥናት የህይወታቸው አንድ ክፍል ሆነ። በደም ስራቸው ውስጥ የሚተላለፈውም ደምም የሀዲስ ጥናት ነበር ማለት ማጋነን አይሆንም። በጊዜው የነበሩ ጎጠኛ የቢድዓና የመዝሀብ ጭፍን ተከታዮች እርሳቸውን በጥቁር ዓይናቸው እያዩ የጥላቻን እንባ ያቀሩ ነበር። ሸይኹን በምን አጊንተን እንበቀል የሚለውም የዘወትር ጭንቀታቸው ነበር።ምንም አጥፍተው አይደለም። ቁርአናዊና ሀዲሳዊ መረጃን መሰረት ያደረገን ጉዞ ስለተጓዙ እንጂ! በግፍና በጥላቻ ስሜት ምክንያት ሁለት ጊዜ እስር ቤት ተወረወሩ። ሸይኹ እንዲህ የሚለውን የዩሱፍ (ዐለይሂ ሰላም) ንግግር ይደጋግሙ ነበር፦ «ጌታዬ ሆይ! ወደርሱ ከሚጠሩኝ ነገር ይልቅ መታሰር ለእኔ የተወደደ ነው፡፡»

ወህኒ ቤትኮ ለሊቃውንት ራሳቸውን የሚያሰለጥኑበት መድረክ፣ ደስታን የሚላበሱበት ጨፌ እንጂ ምንም አይደለም። ሸይኹም ወህኒ ቤት ውስጥ ለነበሩት ሰዎች ለአላህና ለመልዕክተኛው ቃል ተገዥ እንዲሆኑ ዳዕዋ አድርገውላቸው ብዙ ሰዎች ዳዕዋቸውን ያለማቅማማት ተቀብለው ነበር። የሚገርመው በደማስቆ የተሳሩበት ወህኒ ቤት ሸይኹል ኢስላም ቢን ተይሚያህ ታስረው የነበሩበት ወህኒ ቤት ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢብኑ ተይሚያህ በኋላ ወህኒ ቤት ውስጥ ሰላተል ጁሙዓ የተቋቋመው እኚህ የአልባኒያ ተወላጅ በታሰሩ ጊዜ ነው።
ሸይኹ በህይወታቸው በርካታ መፅሃፍትን አበርክተው ያለፉ ሲሆን ለህትመት ያልበቁም መፅሃፍትም አሏቸው።
"ኢርዋኡል ጘሊል" ፣ "ሲልሲለቱል አሓዲሲ ሰሒሓ" ፣ "ሲልሲለቱል አሓዲሲ ዶዒፋህ" ዝነኞቹ ሲሆኑ
"ተወሱል" ፣
ኹጥበቱል ሓጃህ፣
ሲፈቱ ሰላቲ አን-ነቢይ፣
ሰላቱ አትተራዊህ ፣
አህካሙል ጀናኢዝ፣
አዳቡ አዝ-ዚፋፍ ………… ወዘተ ለአብነት ተጠቃሾች ናቸው።
ከርሳቸው የእውቀት ማዕድ የተጠቀሙና ሌሎችን በመጥቀም የሚለፉ የርሳቸው ተማሪዎች በርካታ ናቸው።
ሸይኽ ሓምዲ ዐብዱል መጂድና ሸይኽ ዐብዱርራህማን ዐብዱል ኻሊቅ ……ግዙፎቹ ናቸው።
ህልፈት
ሸይኹ ኡርዱን ውስጥ በምትገኘው ኦማን ከተማ በ1999 ዓ·ል ጥቅምት ወር ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ቶሎ ቅበሩኝ ሲሉ አደራ ብለው ነበርና ከዒሻእ ሰላት በኋላ ሊቀበሩ ችሏል።
ሊቃውንት ስለክብራቸው ሲናገሩ፦
«ከሰማዩ ጠለል በታች በዘመነ-ሀዲስ ስለ ሃዲስ እንደ ሸይኽ ሙሀመድ ናሲሩ አድ-ዲን አል-አልባኒ ይበልጥ የሚያውቅ ሰው አላየሁም።» ሸይኽ ቢን ባዝ
ሸይኽ መሀመድ አል አሚን አሽሺንቂጢ መዲና ላይ እያስተማሩ ሸይኽ አልባኒን ሲያልፉ ከተመለከቷቸው ትመህርታቸውን አቋርጠው ቆመው ሰላም ይሏቸው እንደነበር ተወስቷል።
" መፅሃፎቹን ባነበብኩባቸው ጊዜያት ውስጥ በሀዲስ ላይ የብዙ እውቀት ባለቤት መሆኑን አውቂያለሁ።" ሸይኽ ቢን ዑሰይሚን
"በሸይኽ (አል-አልባኒ) መፅሃፎች እውቀትን የምንጨምር ከመሆን አልተወገድንም።" ሸይኽ ሙቅቢል አል-ዋዲዒ
"ይህ ሰው ተበድሏል። ዐረብ ደረጃውን አላወቀለትም። " ሸይኽ ረቢዕ አልመድኸሊ
"ሸይኽ(አል-አልባኒ) ልትተው የማትገባን ድልብ ለትውልዱ አስተላልፈዋል።"
(ሃፊዝ ቢን ዓብዱር'ራህማን አልመደኒይ)
በጣም የደነቀኝ ሸይኽ ቢን ባዝ የዚህ ዘመን (ሙጀዲድ) የተሓድሶ አራማጅና የለውጥ ኃዋሪያ ማን ነው?