Get Mystery Box with random crypto!

'ኢኽላስ ማለት ኢኽላስን አለማየት ነው!' ========================= መስለማ ኢብኑ | Tofik Bahiru

"ኢኽላስ ማለት ኢኽላስን አለማየት ነው!"
=========================
መስለማ ኢብኑ ዐብዱል‐መሊክ አሚር የሆነበት ሰራዊት በግንብ የታጠረ የሮሞችን ከተማ ከቧል። ከተማዋ ግን ግንቧ ከፍ ያለ፣ በሮቿም በሚገባ የተዘጉ በመሆኑ ሙስሊሞች አጥሩን አልፈው መግባት ተሳናቸው። አጥሩ ላይ ያደፈጡት ቀስተኞች በቀስት በመደብደብ አላስቀርብ አሏቸው። የሮሞቹ ኃይል አመዘነ። ሙስሊሞቹ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቁ።
:
ሙስሊሞች ከበው በቆዩበት አንዱ ሌሊት ላይ ከሙስሊሞቹ መሀል አንዱ ወታደር ለማመን የሚቸግር ዘዴ ፈጠረ!…

ከሰዎች ተነጥሎ በመደበቅ መሬቱን ውስጥ ለውስጥ መቆፈር ጀመረ። ወደ ውስጥ መሸጋገሪያ ሊሆን የሚችል ቦይ አበጀ። ሥራውን ሰርቶ ከጨረሰ በኋላ ግን ለማንም ሳይናገር ከሰራዊቱ ጋር ተቀላቀለ።
:
በሚቀጥለው ቀን እንደተለመደው ሙስሊሞች ለውጊያ ተሰናዱ። ይህ ጀግና የቆፈረው ቦይ ውስጥ በመግባት የከተማዋን በር ከፈተ።
ሙስሊሞቹ ግርርር ብለው ወደ ከተማው ገቡ። አጥሩ ላይ በመውጣት ወደ ውስጥ ዘለቁ። ሮሞች በድንጋጤ የተዋጡት የተክቢራ ድምፅ በከተማው ውስጥ በቤተመንግስቱ ሜዳ ላይ ሲሰሙ ነው! በአንድ ጀግና ምክንያት ሙስሊሞቹ ድል ተጎናፀፉ!
:
ከውጊያው በኋላ መስለማ ኢብኑ ዐብዱል‐መሊክ ሰራዊቱን ሰበስቦ ከፍ ባለ ድምፅ "በከተማው በር ላይ ቦዩን የቆፈረው ማን ነው!? ወደኛ ይምጣና እንሸልመው!" በማለት ተጣራ።
ማንም አልወጣም!…
ጥሪውን ደገመው!…
"በከተማው በር ላይ ቦዩን የቆፈረው ማን ነው!? ወደኛ ይምጣና እንሸልመው!" አለ።
ማንም ሰው አልወጣም!
የሰውየው ማንነት ሳይታወቅ ታደረ። በጧት መስለማ የትላንቱን ጥሪ ደገመው። "በከተማው በር ላይ ቦዩን የቆፈረው ማን ነው!? ወደኛ ይምጣና እንሸልመው!"
አሁንም እንደትላንቱ ማንም አልወጣም!…
ሦስተኛ ቀን ሆነ። መስለማ እንዲህ አለ: — "ቦዩን የቆፈረው ሰው በቀንም ሆነ በማታ ወደኔ እንዲመጣ ምዬበታለሁ!"…
:
ሌሊት ላይ አሚሩ በድንኳኑ ውስጥ ተቀምጦ ሳለ ፊቱን የሸፈነ አንድ ሰው ወደ ውስጥ ዘለቀ። መስለማ "ቦዩን የቆፈርከው አንተ ነህ?" አለ።
ሰውየውም "የቦዩ ቆፋሪ አሚሩ መሀላውን በማፍረስ እንዳይያዝ ሊያጠራው ይፈልጋል። ነገርግር ሦስት መስፈርቶች አሉት።" አለ።
"መስፈርቶቹ ምንድን ናቸው?" አለ፤ መስለማ።
"⑴ ስሙን ላትጠይቅ።
⑵ ፊቱን ላታስከፍት።
⑶ ሽልማት ላትሰጠው።" አለ።
መስለማ "መስፈርቶቹን ተቀብያለሁ።" አለ።
ሰውየውም "የቦዩ ቆፋሪ እኔ ነኝ።" አለውና ከድንኳኑ በመውጣት በሰራዊቱ ድንኳን ውስጥ ተሰወረ።
መስለማ በእምባ ተሞልቶ ከተቀመጠበት በመነሳት ተከታዩን አንቀፅ አነበበ: —

مِّنَ ٱلْمُؤْمِنِينَ رِجَالٌ صَدَقُوا۟ مَا عَٰهَدُوا۟ ٱللَّهَ عَلَيْهِ فَمِنْهُم مَّن قَضَىٰ نَحْبَهُۥ وَمِنْهُم مَّن يَنتَظِرُ وَمَا بَدَّلُوا۟ تَبْدِيلًا
"ከአማኞቹ በእርሱ ላይ ለአላህ ቃል ኪዳን የገቡበትን በእውነት የፈጸሙ ወንዶች አልሉ፡፡ ከነርሱም ስለቱን የፈጸመ (ለሃይማኖቱ የተገደለ) አልለ፤ ከነርሱም ገና የሚጠባበቅ አልለ፡፡ (የገቡበትን ቃል) መለወጥንም አልለወጡም፡፡"
:
መስለማ ከዚህ ክስተት በኋላ በሱጁዳቸው ላይ "አላህ ሆይ ከቦዩ ባለቤት ጋር ቀስቅሰኝ። አላህ ሆይ ከቦዩ ባለቤት ጋር ቀስቅሰኝ።" ይሉ ነበር።
:
የዚህ ታሪክ ፍሬ ሃሳብ:
——— ——— ———
⚀ ለአላህ ካልሆነ ለምንም ነገር ቢሆን መጨረሻው አፈር ነው!
⚀ በአላህና ባንተ መሀል ማንም ያልገባበት መልካም ሥራ ደብቀህ አስቀምጥ። ከቻልክ ከራስህም ደብቀው። ገንዘብም ሆነ ልጆች በማይጠቅሙበት ወቅት ይጠቅምሃል!
⚀ በርካታ የሰለፍ ሰዎች አንድ ሰውም ቢሆን ያየውን ሥራቸውን ውድቅ ነው ብለው በማሰብ ከምንም አይቆጥሩትም ነበር!
⚀ ኢኽላስ የመልካም ስራዎች ህይወት ነው። ያለ ኢኽላስ ስራዎቻችን ሁሉ ህይወት አልባ ቅርጾች ናቸው!
⚀ ኢኽላስ በህይወት የተኖረ፣ አንተም መፈፀም የምትችለው እውነታ እንጂ የማይጨበጥ፣ በሰው ዓቅም ሊፈፀም የማይችል ልዩ ነገር አይደለም። በልምምድ ኢኽላስን መላበስ ይቻላል!