Get Mystery Box with random crypto!

+ አይዞህ አልነካህም + ይህ የብዙዎቻችን የልጅነት ታሪክ ነው:: ጥፋት አጥፍተሃል:: ወላጆችህ | ✞ ፍኖተ ጽድቅ ✞

+ አይዞህ አልነካህም +

ይህ የብዙዎቻችን የልጅነት ታሪክ ነው::

ጥፋት አጥፍተሃል:: ወላጆችህን በጣም የሚያስቆጣ ጥፋት ነው:: ወይ ውድ ዕቃ ሰብረሃል:: ወይ አንዳች በጣም የሚጠሉትን ነገር ሠርተሃል:: አለዚያም አድርግ ተብለህ ሳታደርገው የቀረኸው ነገር አለ::

ወላጆችህ ያጠፋኸውን ቢያውቁ ምን ሊያደርጉህ እንደሚችሉ እያሰብህ ተጨንቀሃል::
"አባዬ ዛሬ ገደለኝ"
"እማዬ በጥርስዋ ነው የምትዘለዝለኝ"
"ዛሬ መሞቴ ነው" እያልህ በፍርሃት ውስጥ ነህ::
ስለዚህ ተደብቀሃል::

መደበቅህን ሲያውቁ ወላጆችህ የሆነ ነገር ጠረጠሩ::

"ምን ሆነህ ነው አንተ?"
"ምንም"
"ታዲያ ምን ያርበተብትሃል"
"ምንም"
"ተናገር እንጂ"
ራስህን ወዘወዝህ እንጂ አልተናገርክም::

አባት ቀረብ ይልና
"አይዞህ የኔ ልጅ ምንም አልልህም አልገርፍህም ንገረኝ" እያለ ማባበል ይጀምራል:: ይሄን ጊዜ ለመናገር እያመነታህ ትቁለጨለጫለህ::

አባትም ነገሩ ይገባውና :-
"እኔ እኮ እውነት እንድትነግረኝ ብቻ ነው የምፈልገው:: ሐቁን ከነገርከኝ አልነካህም:: እኔ የማልወደው ውሸት ብቻ ነው" ይልሃል::

ይሄን ጊዜ እየተቅለሰለስክ በሹክሹክታ ጥፋትህን ትናዘዛለህ::

"አያትህ የሠጡህን የሸክላ ጌጥ እኮ ሰበርኩት"

"ለትምህርት ቤት ክፈል ብለህ የሠጠኸኝን ብር ጣልኩት" ወዘተ ብለህ ትዘረግፈዋለህ::

ተናግረህ ስትጨርስና ፊትህ ላይ የመብረቅ ድምፅ ስትሰማ እኩል ይሆናል:: የአባትህ ጥፊ ነው::

"ሥራህን አውቀህ ነዋ የተደበቅከው!? ኸከከከከ"

ሌላ ቀን ከተገረፍከው የላቀ ግርፊያ ይወርድብሃል:: "አይዞህ ያጠፋኸውን ንገረኝ አልነካህም" የሚል ቃል ዋጋ እንደሌለው ትረዳለህ::

ያጠፋኸውን ንገረኝ ብሎ ስትናዘዝ የሚምርህ አባት እግዚአብሔር ብቻ ነው::

"በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው" 1 ዮሐ. 1:9

#ዲያቆን_ሄኖክ_ኃይሌ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

ሼር በማድረግ ለሌሎች ያካፍሉ!!
@finote_tsidk
@finote_tsidk