Get Mystery Box with random crypto!

+ ድንገት የተበጠሰ ገመድ + የደብረ ዳሞ ገዳም በገመድ ብቻ የሚወጣ እጅግ ጥንታዊ ገዳም ነው:: | ፍልስፍና ከፈላስፎች💆

+ ድንገት የተበጠሰ ገመድ +

የደብረ ዳሞ ገዳም በገመድ ብቻ የሚወጣ እጅግ ጥንታዊ ገዳም ነው:: ይህንን አቡነ አረጋዊ በዘንዶ የወጡትን ታላቅ ገዳም ለመውጣት በግንባታው ወቅት በአፄ ገብረ መስቀል የተሠራ ደረጃ ነበረው:: ሆኖም አቡነ አረጋዊ ደረጃውን ዳህምሞ (አፍርሰው) ብለው በማዘዛቸው እስከ አሁን ድረስ በገመድ የሚወጣበት ገዳም ሆኖአል::

የደብረ ዳሞ መውጫ ገመድ እጅግ ወፍራም ሲሆን እስከ አሁን ድረስ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተንጠላጥለው ወጥተው ወርደውበታል:: ይህ እጅግ ወፍራም ገመድ ለዘመናት ሲያገለግል ተበጥሶ ሰው ጥሎ አያውቅም:: በታሪክ የማይዘነጋና መሃል ላይ የተበጠሰበትና ሰው የጣለበት ቀን አለ:: (የዲያቢሎስ መተናኮል ነው የሚል አለ)

በዚያ ቀን በተበጠሰው ገመድ ላይ የወረደው መንገደኛ ጻድቁ አባ ተክለ ሃይማኖት ነበሩ:: መነኮሳቱን ተሰናብተው በዚያ ገመድ ሲወርዱ ተበጥሶ የማያውቀው ገመድ ድንገት ተበጠሰ:: ከላይ የሚያዩት አባቶች ቁልቁል እያዩ በድንጋጤ ጮኹ:: ሆኖም እግዚአብሔር ለጻድቁ የብርሃን ክንፍ ሠጥቶአቸው ከተበጠሰው ገመድ ተለይተው እንደ መልአክ በርረው ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ወርደው መሬት ላይ አረፉ:: ባረፉባት ሥፍራም ቤተ ክርስቲያን ተሠራባት::

ወዳጄ በሕይወትህ ድንገት የተበጠሰ ገመድ የለም? ሳትጠብቀው የተበጠሰ ገመድ ማንም ላይ ሳይበጠስ አንተ ላይ የጨከነ ገመድ የለም? ምን ዓይነት ገመድ አትበለኝ:: የእንጀራ ገመድ የኑሮ ገመድ የትምህርት ገመድ የፈለግኸው ገመድ በለው:: እሱን ተጠምጥመህ ይዘህ ወደ አንዳች ቦታ ለመድረስ የተማመንክበት ተስፋህን ሙሉ በሙሉ የጣልክበት ገመድ የለም? ድንገት ተበጥሶ ዙሪያው ገደል አልሆነብህም? ሰዎች ማንም ላይ ያልተበጠሰ ገመድ አንተ ላይ ሲበጠስ አይተው "ምኑ ዕድለ ቢስ ነው?" ብለው የተደነቁብህ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ "ከባሕር አደጋ ተርፎ ዕባብ የነደፈው እንዴት ኃጢአተኛ ቢሆን ነው?" ብለው በትዝብት ዓይን እንዲያዩህ ያደረገ በሕይወትህ ሳታስበው ተበጥሶ ዙሪያው ገደል የሆነ ሥፍራ ላይ የጣለህ የሕይወት ገመድ ይኖር ይሆናል::

በዕድልህ አትማረር በሕይወትህ ድንገት የሚበጠስብህ ገመድ የምትወድቅበት ሳይሆን ክንፍ አውጥተህ የምትበርበት ነው:: ፈጣሪ የተማመንክበትን የምታየውን ገመድ እንዲበጠስብህ ከፈቀደ ያላየኸውን ክንፍ ሊሠጥህ እንጂ ሊጥልህ አይደለም:: የሕይወትህን ገመድ የተበጠሰበትን ቀን "እግዚአብሔር ለመልካም አሰበው" ብለህ እንደ ዮሴፍ ታመሰግንበታለህ::
ገመድህን የሚበጥሰው ከገደል ሊጥልህ ሳይሆን በክንፍ አብቅሎ ሊተክልህ ነው:: የሚተክልህ በበረሃ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ነው:: ተራ ተክል የምትሆን እንዳይመስልህ:: የሃይማኖት ተክል (ተክለ ሃይማኖት) ትሆናለህ:: ተክለ መንፈስ ቅዱስ ተክለ ወልድ ተክለ አብ ትሆናለህ:: አብ የተከለው ደግሞ አይነቀልም!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 24 2013 ዓ ም

https://t.me/filsifina_kefelasfoch
https://t.me/filsifina_kefelasfoch
https://t.me/filsifina_kefelasfoch