Get Mystery Box with random crypto!

መለየት የለም ! የለም ! መለየት ሞት አይደለም ሞትም መለየት አያክለው መለየትም ሞትን አይመስለ | ጥበብ

መለየት

የለም ! የለም !
መለየት ሞት አይደለም
ሞትም መለየት አያክለው
መለየትም ሞትን አይመስለው
ትርጓሜያቸው ለየቅል ነው
አንቺም እኔም ጅረት ኾነን
ከራሳችን ምንጭ ፈልቀን
በራሳችን ፈለግ ፈስሰን
አገር ምድሩን አድርሰን
ሄደን ! ሄደን ! ሄደን ! ሄደን
ወርደን ! ወርደን ! ወርደን ! ወርደን !
ሞት በሚሉት ውቅያኖስ
አንድ ስንኾን ተዋሕደን
ተገናኘን 'ንጂ መች ጨርሰን ተለያየን


የለም ! የለም !
መራቅ መለየት አይደለም
ሰው በሰዎች ግዞት
ችግር መከራ ይዞት
አገር ቀዬውን ጥሎ
ስልቻውን በጫንቃው አዝሎ
ቅሉን ጨርቁን አንጠልጥሎ
ብቻውን ሄደ ቢለው ሰፈርተኛው ተጃጅሎ
እርሱ በልቡ ሕንፃ በማይዘመው በማይፈርሰው
ከተጓዘ አኑሮ ሰው
አሁን ይኼ መለየት ነው ?
የለም የለም !
መለየት ይህ አይደለም


ትርጓሜያቸው እንቀይረው
ላ 'ንቺና ለ'ኔ ሌላ ነው
ከፊቴ ቁጭ ብለሽ
ከፊትሽ ቁጭ ብዬ
ክንድሽን ከአንገቴ ጥለሽ
ክንዴን ከአንገቴ ጥዬ
የምታወሪው ሳይገባኝ
የማወራሽ ሳይገባሽ
ለይስሙላ ጥርስሺ ሲሥቅ
ቻው ቻው ሲለኝ ቀልብሽ
ደህና ኹኚ ሲልሽ ዐይኔ
መለየት ይህ ነው ለ'ኔ፡፡

በእውቀቱ ስዩም