Get Mystery Box with random crypto!

ለስንፈተ ወሲብ የሚወሰደው ቫያግራ የመርሳት በሽታን ሊከላከል ይችላል - ተመራማሪዎች ======== | Feya Medical center Bale Robe

ለስንፈተ ወሲብ የሚወሰደው ቫያግራ የመርሳት በሽታን ሊከላከል ይችላል - ተመራማሪዎች
=================
ለስንፈተ ወሲብ የሚወሰደው የቫያግራ እንክብል የመርሳት በሽታን [አልዛይመርስ] ለመከላከል ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል ክኒኑን ሲያጠኑ የነበሩ የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ገለጡ።

በአእምሮ ሴሎች ላይ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከዚህ ወሲብ ቀስቃሽ መድኃኒት የሚገኙ ፕሮቲኖች የመርሳት በሽታን ሊፈውሱ ይችላሉ።

ክሊቭላንድ በምትሰኘው የአሜሪካ ከተማ የሚገኙት እኒህ ተመራማሪዎች የ7 ሚሊዮን ሰዎችን የጤና ሂደት ተከታትለው ነው ቫያግራ የሚውጡ ወንዶች ለመርሳት በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው የጠበበ ነው ያሉት።

'ኔቸር ኤጂንግ' በተሰኘው መጽሔት ላይ ውጤታቸውን ይፋ ያደረጉት ተመራማሪዎቹ በዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ጥናት መሠራቱ እርባና ከፍ ያለው ነው ብለዋል።

ሳይንቲስቶች በዚህ ውጤት ደስተኛ የሆኑበት ምክንያት ጥቅም ላይ እያዋለ ያለው እንክብል ሌላ በሽታን እንዲከላከል ማድረግ ቀላልና ፈጣን ስለሆነ ነው።

ሰማያዊው እንክብል

ቫያግራ አሊያም ሲልዴፊል በመባል የሚታወቀው እንክብል መጀመሪያ ሲመረት ዓላማው የልብ በሽታን መከላከል ነበር። መድኃኒቱ ዋነኛ ሥራው የደም ቧንቧን በማስፋት ደም እንደልብ እንዲሸንሸራሸር ማድረግ ነው።

ነገር ግን ቆይቶ ዶክተሮች አንድ ነገር ተገለጠላቸው። እንክብሉ ከደም ቧንቧ በተጨማሪ ሥራውን በሌሎች የሰውነት አካላት ላይ ሲሰራ ነበር። በተለይ ደግሞ በወንድ ልጅ ብልት ላይ።

ይሄኔ ነው መድኃኒቱ ለድክመተ ወሲብ ፍቱን እንደሆነ ተመራማሪዎች የደረሱበት።

ቫያግራ ለድክመተ ወሲብና ለልብ በሽታ ከመዋል አልፎ 'ፐልሞናሪ ሃይፐርቴንሽን' የተሰኘ የሳንባ በሽታ ላለባቸው ወንዶችና ሴቶች ጥቅም ላይ ይውላል።

አሁን ደግሞ ሳይንቲስቶች አልዛይመር ቀንደኛ የመርሳት በሽታ ዓይነት በተጨማሪ ቫስኪዩላር ዲሜንሽያ የተሰኘውን የመርሳት በሽታ ለመርዳት ያገለግል እንደሆነ እያጣሩ ይገኛሉ።

ዲሜንሺያ የተሰኘው የመርሳት ችሎታን የሚፈታተን በሽታ ከምን እንደሚመነጭ በውል ባይታወቅም ዶክተሮች ግን በአእምሮ ውስጥ ያለ ያለልክ የተከማቸ የፕሮቲን መጠን ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ቫያግራ ለመርሳት በሽታ ፍቱን ሊሆን እንደሚችል በጥናት ደርሰንበታል ያሉት ተመራማሪዎች መድኃኒቱን አብዝቶ መውሰድ ለአእምሮ ሴል ዕድገትና ከልክ ላላለፈ የፕሮቲን ክምችት እንደሚረዳ ምርምራችን ያሳያል ይላሉ።

ቫያግራን አዘውትረው የሚጠቀሙ ሰዎች እንክብሉን ከማይጠቀቀሙ ሰዎች በተሻለ የመርሳት በሽታን ላያጋጥማቸው እንደሚችልም ይናገራሉ።

ዶክተሮቹ ይህን ጥናት ያካሄዱት ባለፉት ስድስት ዓመታት ሲሆን የ7.3 ሚሊዮን ሰዎችን የሕክምና ሬኮርድ አጥንተዋል።

የጥናቱ ቡድኑ መሪ ዶክተር ፌዚዮንግ ቼንግ ውጤቱ አበረታች እንደሆነ ጠቅሰው ነገር ግን ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያሻ አያወላውልም ብለዋል።

ሌሎችም የመስኩ ሰዎች የክሊቭላንድ ዶክተሮች ያገኙትን ውጤት ካበረታቱ በኋላ ተጨማሪ ጥናቶችን ሠርቶ እንክብሉ በተገቢው መልኩ ለታካሚዎች እንዲደርስ ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ።

ምንጭ፤ ቢቢሲ