Get Mystery Box with random crypto!

በሐይማኖት ማስገደድ ሊኖር አይገባም!! በደቡብ ክልል በሀድያ ዞን  ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩበት | ፈትህ አባቦራ መስጂድ

በሐይማኖት ማስገደድ ሊኖር አይገባም!!

በደቡብ ክልል በሀድያ ዞን  ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩበት በጭንጎ ቀዴ ቀበሌ ባሳለፍነው ቅዳሜ በቀበሌው ነዋሪ ሙስሊሞች ላይ የተፈፀመው ድብደባ እና ጥቃት ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ፣ከኢትዮጵያውያን እሴት ያፈነገጠ በሁሉም ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ ሊወገዝ የሚገባው ወንጀል ነው::

በተመሳሳይም በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን በጉንችሬ ሙስሊም ተማሪዎችን በሂጃብ ምክንያት ከትምህርት ማገድ እና ይህን በአግባቡ የጠየቁ ወላጆችን እና ታዳጊዎችን ማዋከብ እና ማሰር አግባብ አለመሆኑ ለመግለፅ እወዳለው ::

በሀገራችን ኢትዮጵያ የሐይማኖት ነፃነት በይፋ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ዜጎች የፈለጉትን ሀይማኖት የመከተል፣ የማምለክ፣ የሌሎችን እምነት ሳይጋፉ ስብከት ማካሄድ እና በመረጡበት እምነት ላይ ፀንቶ የመቆየት መብታቸው የተጠበቀ ነው::

የአንድ ሀይማኖት ተከታዮች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ የሚኖሩ ቁጥራቸው አናሳ የሆኑ የሌላ እምነት ተከታዮችን መብት እና የሀይማኖት ነፃነት መጋፋት ሀይማኖተኛ ከሚባል ማህበረሰብ የማይጠበቅ ፅንፈኝነት ነው::

በሀድያ ዞን በጭንጎ ቀዴ ቀበሌ የተፈፀመውም ሃይማኖትን ለይቶ የተፈፀመ ጥቃት ከፅንፈኝነት አስተሳሰብ የመነጨ፣ ባጭሩ ካልተቀጨም ሀገር የሚያጠፋ እሳቤ ነው::

ሀይማኖት ሰላምን፣ መተዛዘንን እና መከባበርን የሚሰብክ ሆኖ እያለ ከሀይማኖት እሴት ባፈነገጠ መልኩ የራስን ሀይማኖትን በግዳጅ ሌሎች እንዲቀበሉ ማስገደድ እና ማጥቃት ኢ ሞራላዊ እና ህገ ወጥ የሆነ ወንጀልም ነው::

ይህን በእምነት ሽፋን የተፈፀመን ወንጀል ከማንም በላይ የሀይማኖቱ አባቶች፣ ሰባኪያን እና ማህብረሰቡ ሊያወገዘው እንዲሁም ዳግም እንዳይፈፀምም በስህተት አካሄድ ላይ ያሉ ሰዎችን የቤተ እምነቱ መምህራን ተከታዮቻቸውን ሊገስፁ ይገባል::

ይህን አስነዋሪ ጥቃት በሙስሊሞች ላይ ያደረሱ ወንጀለኞችንም የሐድያ ዞን አስተዳደር እና የፀጥታ ክፍሉ ባስቸኳይ ለህግ በማቅረብ ፍትህን እንዲያሰፍን ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለው::

በተመሳሳይ ጉንችሬ ባሉ ትምህርት ቤቶችም ላይ እየተስተዋለ ያለው ከሂጃብ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮችም የትምህርት ቢሮ እና የትምህርት ቤቱ አመራሮች ከሀይል አማራጭ ይልቅ ከተማሪዎች እና ከወላጆች ጋር  ውይይት በማካሄድ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑት ተማሪዎች በሀይማኖታቸው ምክንያት የማግለል እና ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ የተደረገበትን አግባብ በማረም የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ሊያደርጉ እንደሚገባም ለማሳሳብ እወዳለው:

በመጨረሻም በሀገራችን በሁሉም ቦታዎች ሀይማኖትን፣ ብሄርን እና ማንነትን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች፣ ግድያዎች፣ ጭቆናዎች እና ማፈናቀሎች በዘላቂነት ያበቁ ዘንድ የተናጠል ውግዘት  ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው እምነት እና ብሄር ሳይለየው በጋራ ግፍን ለመቃወም እና ለማስቆም በአንድነት መቆም ይገባል::

የአንዱ መጠቃት ለሌላው ህመም መሆን ሲችል፣በማንም የሰው ልጆች ላይ የሚፈፀም በደል እና ጭቆና በራስ ላይ የተፈፀመ ጭቆና እና ግፍ መሆኑን ማመን መቻል ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ነው::

ይህን አስተሳሰብ ማምጣት ከተቻለ አጥፊዎንም ለማጋለጥ፣ ጭቆና እና በደሎችን፣ ግድያዎችን እና መፈናቀሎችን ለማስቆም ያግዛል ብቻ ሳይሆን ይቻላልም!

በሀገራችን በሰላም እና በመከባበር እንዲሁም እውቅና በመሰጣጠት በፍትህ እና በእኩልነት ለመኖር በጋራ እንስራ!
ኡስታዝ አቡበከር አህመድ



https://t.me/fethmedia
https://t.me/fethmedia
https://t.me/fethmedia