Get Mystery Box with random crypto!

' በእስር ላይ የሚገኙ ሙስሊሞች በሙሉ ከእስር በሚፈቱበት አግባብ ላይ ስምምነት ተደርሷል ' - ኡ | ፈትህ አባቦራ መስጂድ

" በእስር ላይ የሚገኙ ሙስሊሞች በሙሉ ከእስር በሚፈቱበት አግባብ ላይ ስምምነት ተደርሷል " - ኡስታዝ አቡበከር አህመድ

ዛሬ ከፌደራል እና አዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽነሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረግ  መቻሉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የስራ አመራሮች ሼይኽ ሁሴን ጨምሮ የፕሬዝዳንቱ አማካሪዎች ኡስታዝ አቡበክር አህመድ ፣ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ፣ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ እንዲሁም ከኦሮሚያ መጅሊስ ሼይኽ ሚስባን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል  ጋር ውጤታማ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የፈደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና እና ምክትል ኮሚሽነሮችን ጨምሮ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እና ከፍተኛ የፀጥታ ሐይሉ አመራሮች ተካፍለዋል።

በውይይቱ ላይ በሸገር ከተማ የፈረሱ መስጂዶችን ተከትሎ በሁለት ጁምዓዎች በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የተወሰዱት ኢ ሰብዓዊ እና ከልክ ያለፉ የኃይል እርምጃዎች ተቀባይነት የሌላቸው እና ህዝበ ሙስሊሙን እጅግ ያሳዘነ መሆኑ ተገልፆል።

ሀገር ወዳድ እና ሰላማዊ ለሆነው ህዝበ ሙስሊም ህጋዊ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በማቅረቡ በምላሹ በፀጥታ ኃይሉ የተወሰደው የኃይል እርምጃ  በምንም መመዘኛ የሚገባው እንዳልነበር እና ጥፋት እንደሆነ ለፀጥታ አመራሮቹ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።

በፀጥታ ኃይሉ በኩልም የሙስሊሙን ህጋዊ ጥያቄ ሽፋን በማድረግ የራሳቸው አጀንዳ ለማራመድ የሞከሩ ኃይሎች መኖራቸውን መረጃ እንዳላቸው በማንሳት የነበራቸውን ስጋት ገልፀዋል።

በውይይቱ መቋጫ ላይ በሁለቱ ጁምዓዎች በተወሰደው የኃይል እርምጃ በእስር ላይ የሚገኙት ሙስሊሞች በሙሉ ከእስር በሚፈቱበት አግባብ ላይ ከስምምነት ላይ መድረስ መቻሉ ተገልጿል።

ከህግ አግባብ ውጪ የኃይል እርምጃ የወሰዱ የፀጥታ ሀይሉ አባላትም በህግ  አግባብ እንዲጠየቁ ኮሚቴ ተዋቅሮ የማጣራቱ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

ህዝበ ሙስሊሙ ያቀረባቸው ህጋዊ ጥያቄዎቹ በኦሮሚያ ክልል መንግስት በኩል መፍትሄ ለመስጠት ቃል በመገባቱ እና ይህም መፍትሄ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ህዝበ ሙስሊሙ በተለመደው ጨዋነቱ በትዕግስት በመጠበቅ ከመሪ ድርጅቱ መጅሊሱ ጎን በመቆም በተቋሙ የተሰጡትን መመሪያ እና የመፍትሄ አቅጣጫ በመተግበር እና በዱዓ በማገዝ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።

ከፀጥታ አመራሩ ጋር የተደረገው ፍሬያማ ውይይት በመግባባት የተቋጨ ሲሆን በቀጣይ ባሉ ጁምዓዎች ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን በማጠናከር እና በዱዓ በመበርታት መደበኛ የጁምዓ ሰላቱን ብቻ እንዲያከናውን ጥሪ ቀርቧል።

በሸገር ከተማ መስጂድ ፈረሳ ጋር በተያያዘ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ያቀረበው ጥያቄ የመፍትሄ አቅጣጫ የተቀመጠለት በመሆኑ በሁሉም መሳጂዶች ከቁኑት ዱዓ ውጪ  የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች አስፈላጊ ባለመሆናቸው ህዝበ ሙስሊሙ የተለመደ ታዣዥነቱን በማሳየት የጁምዓ ሰላቱን ሰግዶ ብቻ መመለስ እንዳለበት ማሳሰቢያ ተላልፏል።

Via ኡስታዝ አቡበከር አህመድ



https://t.me/fethababora
https://t.me/fethababora
https://t.me/fethababora