Get Mystery Box with random crypto!

በክቡር ሸይኽ ሀጅ ኢብራሂም ቱህፋ የሚመራዉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤ ከኦሮሚያ ክልላዊ | ፈትህ አባቦራ መስጂድ

በክቡር ሸይኽ ሀጅ ኢብራሂም ቱህፋ የሚመራዉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር ዉይይት ካደረጉ ቡኀላ የተሰጠ መግለጫና ማብራሪያ:-
••••••••••••••••••••••••••••••
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የተከበሩ ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱህፋ የተመራ ልዑክ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት የተከበሩ አቶ ሸመልስ አብዲሳ ጽ/ቤት በመገኘት በሸገር ከተማ እየተከናወነ ባለው የመስጊድ ፈረሳ ጉዳይ ላይ አምስት ሰዓታት የፈጀ ዉይይት አድርገናል።በዉይይቱ ላይ ከኦሮሚያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት የተገኙ እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራር አባላት  ላይ ተገኝተዋል።

በዉይይቱ ላይ የልዑኩ አባላት በሸገር ከተማ ስለፈረሱት መስጂዶች ጉዳይ በዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዉይይቱ ላይ በሙስሊም ተወካዮች ከተነሱት ነጥቦች መካከል፡-

• በሀገራችን የተለያዩ አከባቢዎች የመስጂድ መሬትን በህጋዊ መንገድ የማግኘትና የመሥራት እንዲሁም ለተሠሩት መስጂዶች ካርታና የማስፋፊያ መሬት የማግኘት ሁኔታ ላይ በርካታ ችግሮች እንዳሉ በዝርዝር ተብራርተዋል።
• የሸገር ከተማ አስተዳደር ከፕላን ዉጭ ተሠርተዋል ያላቸውን መስጂዶች ለማፍረስ ሲነሳ የሚመለከተውን የእስልምና ጉዳዮች አካላትን እንዳለወያየ፥እንዲሁም በጉዳዩ ላይ እንወያይ በሚል በተደጋጋሚ ጊዜ የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ ለማወያየት አለመሞከሩ ተገቢ አለመሆኑ በቅሬታ መልክ ቀርቧል።
• ሕዝበ ሙስሊሙ የሸገር ከተማ መስጂድ ፈረሳ ጋር በተያየዘ በተፈጠሩት ሁኔታዎች እጅጉን መጎዳቱንና ማዘኑን በማብራራት ተገቢውን ካሳና የሞራል ህክምና እንደሚያስፈልገው ተጠቅሷል፥

• የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም ሆነ ሕዝበ ሙስሊሙ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ከተሞችን ለማዘመን የሚደረገውን እቅድን፥ ልማትንም ሆነ እድገትን የሚደገፍው እንጂ የሚቃወመው እንዳልሆነ ሆኖም እቅዱ በቂ የእምነት ተቋማትን ለአማኞች ማቅረብንና ሰው ተኮር መሆን እንደሚገባው ተብራርቷል።
•  በሸገር ከተማ አስተዳደር ዉስጥ ያለ ፕላንና ሕጋዊነት ተሠርተዋል በሚል የፈረሱት 22(ሃያ ሁለት) መስጊዶች መሆናቸውን በመጥቀስ ለሕዝበ ሙስሊሙ የመስጊድ ጥያቄዎች በሙሉ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚገባ፥
• ቀደም ብሎ በጉዳዩ ላይ ከጅምሩ በመነጋገር መፍታት እየተቻለ እስከ ትናንትናው እለት ድረስ መሰል ዉይይት ሳይደረግ መስጂዶችን ወደ ማፍረስ በመገባቱ በመንግስትና በሕዝብ መካከል ቅሬታ ፈጥሮ ጉዳዩ እስከ ነፍስ መጥፋት ማምራቱ እጅግ የሚያሳዝን መሆኑን፥
• የጸጥታ አካላት ሰላማዊ ሙስሊሞች ላይ በቀጥታ በመተኮስ ሙስሊሞችን መግደላቸውና ማቁሰላቸው ተገቢ አለመሆኑን፥እንዲሁም ንጹሃን ላይ በመተኮስ የገደሉና ያቆሰሉ አካለት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ።
• እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር የተያያዘ በርካታ ችግሮች በዝርዝር ተብራርተዋል።

በክልሉ ፕሬዝዳንት በኩል የተጠቀሱት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦

1.  ቀደም ብሎ በጉዳዩ ላይ ዉይይት አለመደረጉ ስህተት መሆኑን።

2. በተፈጠረው ሁኔታ ሕይወታቸውን ላጡት ሙስሊሞች ማዘናቸውን።

3. የሸገር ከተማ የሃይማኖትን እሴትን መሠረት አድረጎ እንደሚገነባ እና የእሰልምናን ጨምሮ የሌሎችም ቤተእምነቶችም ተቋማት በብዛት በሸገር ከተማ ፕላን ዉስጥ እንደተካተቱ።

4. አስፈላጊውን የቤተእምነት መሥሪያ መሬቶችን በፕላኑ መሠረት ለምዕመኑ እንደሚሰጥና በቆርቆሮ ሳይሆን የከተማዋን ፕላን የሚመጥን በርካታ ዘመናዊ መስጊዶች በከተማው እንዲሰሩ እንደሚፈልጉ።

5. በሸገር ከተማ ላይ በሀገር ደረጃ  ሊጠቀስ የሚችል ትልቅና ዘመናዊ መስጂድና ለሌሎች እምነት ተቋማት መሥሪያ ቦታ እንደሚሰጥ።

6. በሸገር ከተማ ለኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ የሚሆን መሬት እንደሚሰጥ።

7. ሸገር ከተማ ከ20 እስክ 30 ሚሊዮን ነዋሪዎች ያላት፥ዘመናዊና በፕላን ብቻ ግንባታ የሚካድባት ከተማ ሆኖ ለመግንባት ሕግ ወጥ ግንባታን መከላከል፥የተገነቡትን ማፍረስ እንደሚቀጥል ለዚህ ሂደት የእምነት ተቋማት ተባባሪ እንዲሆኑ እንፈልጋለን።

8. አዲሱ የሸገር ከተማ ፕላን ወደ ተግባር እስኪገባ ድረስ ሙሉ ለሙሉ መኖሪያ ቤቶች ባልፈረሱባቸው አከባቢዎች ለሚኖሩ ሙስሊሞች በጊዜያዊነት የሚሰግዱባቸው መስጊዶች የኦሮሚያ ክልል መጅሊስና የሸገር ከተማ አስተዳደር በጋራ በመጋገር መስጂድ መሥሪያ ቦታ እንዲያዘጋጁ።

9. የሸገር ከተማ ማስተር ፕላን በመጪው ሀምሌ ወር ወደ ተግባር ማዋል ከመጀመሩ በፊት በማስተር ፕላኑ ለእምነት ተቋማት የተዘጋጀውን ስፍራዎችን የሙስሊም ተወካዮች ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ ቀድመው ፕላኑን እንዲመለከቱና እንዲያረጋግጡ።

10. በሸገር ከተማ ሕዝቡ ሙስሊሙ ያቀረባቸውና የሚያቀርባቸው የመስጊድ ጥያቄዎች በፕላኑ መሠረት ምላሽ እንደሚሰጥ።

11. ሸገር ከተማን ጨምሮ በመላው ኦሮሚያ ክልል ከዚህ ቀደም ሲደረግ  እንደነበረው የእምነት ተቋማት እና የመቃብር ሥፍራ መስጠት እንደሚቀጥል።

12. በሸገር ከተማ ዉስጥ ካሉት ስምንት መቶ(800) የሁሉም እምነት ተቋማት መካከል 656(ስድስት መቶ ሀምሳ ስድስት) የሚሆኑት ከፕላን ዉጭ የተሠሩ በመሆናቸው እነዚህን የሚገነባውን ከተማ ፕላን የማይመጡትን የተለያዩ ቤተእምነቶችን ወደ በሕጋዊና ከተማውን በሚመጥኑ ተቋማት ለመተካት የሚደረገውን ሂደት የኦሮሚያ ክልል መጅሊስም ባለበት የኦሮሚያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አቅሙን በማጠናከር በዉይይት የእምነት ተቋማቱ ራሳቸው መፍረስ ያለባቸውን እንዲያፈርሱ እንጂ ከአሁን በኋላ መንግስት በራሱ ማፍረስ እንደሚያቆም።

የእስረኞችን መፈታትና የተጎዱትን ሙስሊሞች በተመለከተ


1. ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ የታሠሩትን ሙስሊሞችን መፈታትን አስመልክቶ ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ከፌደራልና አዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮች ጋር ዉይይት ይደረጋል።ያለምንም ልዩነት የታሠሩት ሙስሊሞች በጠቅላላው እንደሚፈቱ እንጠብቃለን።

2. ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአንዋር እና ኑር መስጂድ በሸገር ከተማ የፈረሱትን መስጂዶችን በመቃወም ላይ እያሉ የተገደሉ ሙስሊሞችን ቤተሰቦችን አላህ መጽናናቱን እንዲሰጣቸው ለሟቾች ደግሞ አላህ የሸሂደትነት(ሰማዕትነትን) ደረጃ እንዲለግሳቸው እየተማጸንን በሸገር ከተማ በፈረሱት መስጂዶች ምትክ ከሚሠሩት መስጂዶች መካከል አንዱ «የሸሒዶች መስጂድ» ተብሎ እነርሱን ለማስታወስ ይሰየማል። በመስጂዱ ቅጥር ጊቢ ዉስጥም የሟቾችም ስም ዝርዝር በጉልህ በሚታይ መልኩ ይጻፋል።

3. ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከሸገር ከተማ ከፈረሱት መስጂዶች ጋር በተያየዘ በተፈጠሩት ሂደቶች  ጉዳት የደረሰባቸውን ሙስሊሞችን ሕዝበ ሙስሊሙ በመደገፍ ከጎናቸው በመሆን እንዲያግዝ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን

ሰኔ 01 ቀን 2015



https://t.me/fethababora
https://t.me/fethababora
https://t.me/fethababora