Get Mystery Box with random crypto!

ስምምነት የተደረሰባቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ለማስፈጸም ሁላችንም ተግተን እንስራ! ————————— | ፈትህ አባቦራ መስጂድ

ስምምነት የተደረሰባቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ለማስፈጸም ሁላችንም ተግተን እንስራ!
—————————

በሸገር ሲቲ የመስጊዶች ፈረሳ የፈጠረውን ቀውስ ለመቆጣጠር በእስልምና ጉዳዮች መሪነት ብዙ ጥረት ሲደረግ የቆየ ሲሆን ከክልል መንግስቱ እና ከሌሎችም የመንግስት ኃላፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በተደረገው ውይይት በፈረሳውና አስከትሎ በተፈጠረው የተቃውሞ ሂደት በሙስሊሙ ላይ የደረሰው በደል በስፋት ተዘርዝሮ የቀረበ ሲሆን በመንግስት ኃላፊዎች በኩልም የተፈጸመው ተግባር ስህተት መሆኑ ታምኖበት ችግሩን ለመፍታት የታሰቡ እርምጃዎች በውይይቱ ሂደት ወደፊት ወጥተዋል።

በዚህም የመስጊድ ፈረሳው በአስቸኳይ እንደሚቆምና ከፕላን ውጭ ያሉ መስጊዶች ጉዳይ ከመጅሊሱ ጋር በመሆን እንደሚታይ፣ የፊታችን ሀምሌ በሚጸድቀው የከተማዋ ፕላን ላይ መጅሊሱን በማማከር ደረጃቸውን የጠበቁ መስጊዶች እንደሚሠሩ፣ ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲና ግዙፍ ማዕከላዊ መስጊድን ጨምሮ መንፈሳዊ ማዕከላት እንደሚኖሩ፣ ነዋሪ ባለባቸው አካባቢዎችም ጊዜያዊ የመስገጃ ቦታዎች እንደሚዘጋጁ ከመንግስት በኩል ቃል ተገብቷል። በተቃውሞው ሂደት የታሰሩ ሰዎች ጉዳይም ከዛሬ ጀምሮ ከጸጥታ አካላት ጋር በሚደረጉ ቀጣይ ውይይቶች እንደሚታይ ስምምነት ላይ ተደርሷል። (ከመንግስት ኃላፊዎች ጋር ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን የመፍትሄ አማራጮች በዝርዝር በመጅሊሱ መግለጫ ማግኘት ይቻላል።)

በሂደቱ የተፈጠረው ቀውስ ሙስሊሙን ለበርካታ ህመም የዳረገ እንደመሆኑ ለጉዳዩ አስቸኳይ እልባት ለማግኘት መንቀሳቀስ የግድ ነበር። ህዝበ ሙስሊሙም የተባበረ ድምጹን በማሰማት በሸሂዶቹ ደም የከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አይደለም። አሁን ላይ ደግሞ ሁላችንም ወደመፍትሄው አፈጻጸም በማተኮር የሸሂድና የተጎጂ ቤተሰቦችን መንከባከብ፣ በእስር ላይ ያሉ ወንድም እህቶቻችንን ማስፈታት እና በመንግስት በኩል ቃል የተገቡትን ነጥቦች ተከታትሎ ማስፈጸሙ ላይ ልንረባረብ እንደሚገባን ለማሳሰብ እንወዳለን።

ህዝበ ሙስሊሙ በዘወትር ጨዋነቱ ይህንን የመፍትሄ ክትትል ሂደት ከሚያስተጓጉሉ አካሄዶች ተቆጥቦ ነገሮች ወደነበሩበት መረጋጋት ይመለሱ ዘንድ ጁሙዓን የመሳሰሉ የስብስብ አጋጣሚዎቻችን መሪ ድርጅታችን ባስቀመጠው አቅጣጫ ብቻ እንዲካሄዱ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት እንደሆነ አጥብቀን እናምናለን። በግልም ሆነ በቡድን በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በሌሎች የመገናኛ መንገዶች የሚኖሩን ሂደቶች በተቻለ መጠን መፍትሄውን ተከታትሎ የማስፈጸም መንፈስ ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ እና ሙስሊሙን ወዳልሆነ አቅጣጫ መምራት ለሚፈልጉ አካላት በር የማይከፍት አካሄድ እንድንከተል ጥሪ እናደርጋለን። የመሪ ተቋማችንን ትእዛዝ እና የትግበራ አቅጣጫ መከተል በዚህ መሰል የቀውስ ወቅቶች እጅግ አንገብጋቢ እና ብቸኛ አማራጭ መሆኑንም ለማስታወስ እንወዳለን።

በሌላ በኩል በመንግስት ኃላፊዎች በኩል ቃል የተገቡትን የመፍትሄ ሀሳቦች ከዳር ማድረስ ችግሩ ይፈታ ዘንድ ቁልፍ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን የመንግስት የጸጥታ ኃላፊዎች ይህንኑ ያገናዘበ አካሄድ ሊሄዱ ይገባል። የሰላም ቀንዲል በሆነው የህዝበ ሙስሊሙ መስጊዶች ከእንግዲህ ወዲህ አንድም ጠብታ ደም ሊፈስ አይገባምና ህዝበ ሙስሊሙ ላይ ጉዳት ከሚያደርስ አካሄድ ፈጽመው እንዲቆጠቡ በጥብቅ ልናሳስብ እንወዳለን።

ለመስጊድ ክብር ሲሉ ደማቸውን ላፈሰሱት ሸሂዶቻችን መታወሻ በሸገር ሲቲ በሚገነባው "የሸሂዶች መስጊድ" ስያሜ ሁሌም በዱዓ እንድናስታውሳቸው ያበቃን ዘንድ አላህን እንለምናለን! በቀጣይ ወቅቶች ሁላችንም ከሸሂድና ተጎጂ ቤተሰቦች ጎን በመቆም ጉዳታቸው ይጠግግ ዘንድ እስልምና ጉዳዮች ይፋ ባደረጋቸው የባንክ ሂሳቦች እርዳታ በማሰባሰብ እና በመንከባከብ በኩል እንበራታ! አላህ ለዲኑ የተከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ይቀበል! አገራችንንም ሰላም ያድርግልን! አሚን ያረበል ዓለሚን!

Ustaz abubeker ahmed