Get Mystery Box with random crypto!

#ጠላፊዎቹ ፡ ፡ #ክፍል_አስራ_ስምንት ፡ ፡ #በኬንፎሌት ፡ ፡ #ትርጉም_ወንዳየሁ_ንጉሴ | 📚📚ቤተ__መፅሀፍት📖📗🧾📜

#ጠላፊዎቹ


#ክፍል_አስራ_ስምንት


#በኬንፎሌት


#ትርጉም_ወንዳየሁ_ንጉሴ


.... ሄሪ ዙሪያ ገባውን ተመለከተና ‹‹እዚህ ክፍል ውስጥ አራቱ ወንበሮች
ክፍት ናቸው፣ ሌሎቹ ክፍሎች ውስጥም እንዲሁ ነው፡፡››

‹‹አልተሳሳትክም፧ ይህ ክፍል ቀን ቀን አስር ሰው፣ በመኝታ ጊዜ ግን ስድስት ሰው ብቻ ነው የሚይዘው፡፡ ከራት በኋላ መኝታ ስናመቻች ታያለህ፡ እስከዚያው ዘና ብለህ ቁጭ በል›› አለው።

ሄሪ ዊስኪውን እየተጎነጨ ነው፡፡ አስተናጋጁ ታዛዥና ፈጣን ቢሆንም ለንደን ሆቴሎች ውስጥ እንደሚሰሩት አስተናጋጆች ግን ጠብ እርግፍ
አይልም፡፡ አሜሪካውያን አስተናጋጆች የተለየ የደምበኛ አቀባበል ስርዓት
ሳይኖራቸው አይቀርም ሲል ገመተ፡ በለንደን ሆቴሎች አስተናጋጆች በአክብሮት አንገታቸውን እያጎነበሱ ‹‹ጌታዬ ምን ልታዘዝ›› የሚሉትም አቀባበል የበዛ ትህትና ሆኖ ነው ያገኘው፡፡

ሻምፓኟን እየተጎነጨች መጽሔቷን የምታገላብጠውን ማርጋሬት ኦክሰን ፎርድን መወዳጃው ሰዓት ሳይደርስ አይቀርም ሲል አሰበ ሄሪ፡፡ ከእሷ ዓይነት ኮረዶች ጋር ብዙ ጊዜ የማገጠ ስለሆነ ሴቶችን የመቅረብ ችግር የለበትም፡

‹‹ለንደን ነው የምትኖሩት?›› ሲል ጨዋታ ጀመረ፡

‹‹ለንደን ውስጥ ቤት አለን ነገር ግን ብዙ ጊዜያችንን የምናጠፋው ገጠር
ነው:፡ አባታችን በርክሻየን የሚባል አገር ርስት፣ ስኮትላንድ ውስጥ ደግሞ
የጠመንጃ ተኩስ መለማመጃ ቦታ አለው›› ስትል በተሰላቸ ሁኔታ መልስ
ሰጠችው ርዕሱ እንዲነሳ እንዳልፈለገች ሁሉ፡

‹‹አውሬ ታድናላችሁ?›› ሲል ጠየቃት፤ሃብታሞች በሙሉ አደን ስለሚወዱና ስለእሱም ማውራት ደስ እንደሚላቸው ስለሚያውቅ፡፡

‹‹ብዙም አናድንም›› አለች ‹‹ከዚያ ይልቅ ተኩስ እናዘወትራለን››

‹‹ተኩስ ታዘወትሪያለሽ?›› ሲል ጠየቃት ተገርሞ ተኩስ የወይዛዝርት
ተግባር እንዳልሆነ ስለሚያውቅ፡፡

‹‹እንደዚህ አይነት የማይረቡ ጥያቄዎችን ለምን ትጠይቀኛለህ?››
አለችው ፊቷን ወደእሱ አዙራ፡

ሄሪ ያልጠበቀው ምላሽ በመሆኑ ደንገጥ አለ፡፡ ቀጥሎ ምን ሊላት
እንደሚችል አላወቀም፡ የዚህ አይነት ጥያቄዎች በርካታ ኮረዶችን ጠይቋል፧
ሁሉም ግን እንደዚህ አይነት ምላሽ አልሰጡትም፡፡ ‹‹እነሱ የማይረቡ ሆነው
ነው?›› ሲል ጠየቃት፡፡

‹‹እኔ የት እንደምኖር ወይ አደን ላድን አላድን አንተን ምን ያገባሃል?››

‹‹ታዲያ እኮ ባለጸጎች ይህን ነው ሲያወሩ የሚውሉት››
‹‹አንተ ታዲያ ባለጸጋ አይደለህ›› አለችው፡፡
ወደ እንግሊዛዊ የአነጋገር ዘይቤ ተመለሰ፡፡
ማርጋሬት ሳቀችና ‹‹ይሻላል›› አለችው፡፡

‹የአነጋገር ዘይቤዬን ቶሎ ቶሎ መቀየር አልችልም እደነጋገራለሁ››
‹‹እንግዲያው የጅል ጥያቄ የማትጠይቀኝ ከሆነ የአሜሪካውያንን
የአነጋገር ዘይቤህን እታገስልሃለሁ››
‹‹አመሰግናለሁ ማርዬ›› አላት ሄሪ ቫንዴርፖስት ነኝ ብሎ ራሱን አሳምኖ፡፡ ብዙም አስቸጋሪ እንዳልሆነች ገምቷል፡፡ ይህንንም ሁኔታዋን ወዶላታል
‹‹ሽወዳውን ተክነኸዋል›› አለችው፡፡

የውይይታቸውን ርዕስ መለወጥ ፈለገ፡፡ ልቧን እንዴት ማሸነፍ እንደሚችል አልከሰትልህ አለው። ከሌሎች ጋር እንደማገጠው ከእሷ ጋር ለመማገጥ ቀላል እንዳልሆነ አውቋል፡፡

‹‹እኔ ብዙም ትምህርት የለኝም›› አላት፡፡ ብዙዎቹ ባለጸጎች ስለተማሩት
ትምህርት ሲያወሩ ውለው ሲያወሩ ቢያድሩ አይሰለቻቸውም፡፡ ማርጋሬት
እንደ እሷ ካሉ ሴቶች ጋር ስትነጻጸር ጨዋ መሆኗ አስደስቶታል፡፡

‹‹ስለ ትምህርት ሲነሳ ምን እንደሚሰማኝ እኔ ነኝ የማውቀው ምክንያቱም እኔም ብሆን በስርዓቱ አልተማርኩም›› አለች፡፡

‹‹ይሄ ሁሉ ገንዘብ እያላችሁ?›› ሲል ጠየቃት፡፡

በአዎንታ ራሷን ነቀነቀች ‹‹ይኸውልህ ትምህርት አልተማርንም››

ሄሪ ጆሮውን ማመን አቃተው፡ ለሰራተኛው መደብ የለንደን ነዋሪ
ልጅን ትምህርት ቤት አለማስገባት እንደ ውርደት ነው የሚቆጠረው፡
ተማሪዎች ጫማዎቻቸውን ለጫማ ሰፊ ሲሰጡ ከትምህርት ቤት አስፈቅደው ይቀራሉ ተለዋጭ ጫማ ስለሌላቸው፡፡ ‹‹ነገር ግን ልጅን ትምህርት ቤት
አለማስገባት ማለት የሚታሰብ አይደለም›› አለ ሄሪ፡፡ ‹‹የማይታመን ነው፡
ሃብታሞች ሁሉን ማድረግ የሚችሉ ነበር የሚመስለኝ፡፡››

‹‹አባታችን ግን ለየት ያለ ሰው ነው››

‹‹ወንድምሽ?›› ሲል ጠየቃት ባገጩ ወደ እሱ እያመለከተ።

‹‹ኦ እሱ ኢንተን ነው የሚማረው›› አለች በምሬት በለንደን ውስጥ አሉ
ከሚባሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱን እየጠቀሰች ‹‹ለወንዶች ሲሆን
ጉዳዩ የተለየ ነው››

ሄሪ ‹‹ይህ ማለት ከአባትሽ ጋር ለምሳሌ እንደ ፖለቲካ በመሰለ ጉዳይ ልዩነት አለሽ ማለት ነው?››

‹‹አዎ ልዩነት አለን፡፡ እኔ የሶሻሊዝም ደጋፊ ነኝ፡፡››

‹‹እኔ የኮሚኒስት ፓርቲ አባል ነበርኩ›› አለ፡፡ እውነቱን ነው፡፡ አስራ
ስድስት ዓመት ሲሞላው አባል ሆነና ከሶስት ሳምንት በኋላ ወጣ፡፡

ይህን ስትሰማ ለወሬ አቆበቆበች ‹‹ለምን ወጣህ?››

እውነታው የፖለቲካ ስብሰባዎች ስልችት ስለሚሉት ነው፡፡ ‹‹በቃላት
መግለጽ ይከብደኛል›› አላት፡፡

እሷ ግን በቀላሉ አለቀቀችውም ‹‹ለምን እንደተውከው ማወቅ
እፈልጋለሁ››

“ለኔ እነዚያ ስብሰባዎች የሰንበት ትምህርት ቤትን ያስታውሱኛል›› አላት።

ይህን ስትሰማ በሳቅ ተንከተከተች፡፡

‹‹ለማንኛውም የወዛደሩ መደብ በላቡ ሰርቶ የሚያገኘውንና በበዝባዦች
የተነጠቀውን ሀብት ለአምራቹ ለራሱ በመመለስ በኩል ከኮሚኒስቶች በተሻለ
ሁኔታ ሳልሰራ አልቀረሁም››

‹‹እንዴት ማለት? ሀብታሞችን ብቻ ነው የምትመነትፈው ማለት ነው?

‹‹ደሀው የሚዘረፍበት ምንም ምክንያት የለም ምንም ስለሌለው፡››

እንደገና ሳቀችና ‹‹መቼም በስርቆት ያገኘኸውን ሀብት እንደ ሮቢን ሁድ አታከፋፍልም?››

‹‹እኔ የእርዳታ ድርጅት አይደለሁም›› አለ ትከሻውን እየሰበቀ ‹‹ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ደሃ የምረዳበት ጊዜ አለ››

‹‹የሚገርም ነው›› አለች ‹‹እንዳንተ ያሉ ሰዎች መኖራቸውን አውቃለሁ፡ ነገር ግን ከእንደዚህ ያለ ሰው ጋር በአካል መገናኘት ሌላ ነገር ነው:.

‹ብዙም አታካብጂው ነፍሷ አለ በሆዱ፡፡ ስለ እሱ ማወቅ የሚፈልጉ ሴቶች ሰላም ይነሱታል፡፡ ‹‹እኔ ከሌላው ምንም የምለይበት ነገር የለም የመጣሁት አንቺ ከምታውቂው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡››

በዚህ ርዕስ ላይ ብዙ ተነጋገርን፤ አሁን ሌላ ርዕስ መቀየር ይኖርብናል› ሲል አሰበና ‹‹ድህነቴን እንዳስታውስ አድርገሽ እፍረት ውስጥ ከተሺኛል›› አለ ፊቱ በሃፍረት ቀልቶ፡፡

‹‹ኦ ይቅርታ›› አለች ተሰምቷት፡፡ ትንሽ አሰብ አደረገችና ‹‹አሜሪካ
ለምን ትሄዳለህ?›› ስትል ጠየቀችው፡፡

‹‹ከሬቤካ ሞግሃም ፍሊንት ለማምለጥ››

ሳቀችና ‹‹አይ የምሬን ነው የምልህ››

ይቺ ሴት አንዴ ከያዘች የምትለቅ አይደለችም አለ በሆዱ ‹‹እስር ቤት
እንዳልገባ ነው አገር ለቅቄ የምሄደው››

‹‹እዚያ ስትደርስስ ምን ልትሰራ ነው ያሰብከው?››

ካናዳ አየር ኃይል ለመግባት ሃሳብ አለኝ፡፡ አይሮፕላን ማብረር መማር እፈልጋለሁ››

‹‹እንዴት ደስ ይላል!››
‹‹እናንተስ ለምንድነው አሜሪካ የምትሄዱት?››

‹‹አገር ጥለን እየጠፋን ነው›› አለች እያንገሸገሻት፡፡

‹‹ምን ማለትሽ ነው?››
‹‹አባታችን የፋሺስት አስተሳሰብ አራማጅ እንደሆነ መቸም ሳታውቅ
አትቀርም››

ሄሪ ራሱን በአዎንታ ነቀነቀ ‹‹ጋዜጣ ላይ አንብቤያለሁ››

‹‹በእሱ አስተሳሰብ ናዚዎች ግሩም ሰዎች ስለሆኑ ከእነሱ ጋር ውጊያ መግጠም ተገቢ አይደለም ብሎ ያምናል፡ አገር ውስጥ ከቆየም ወህኒ መውረዱ አይቀሬ ነው፡››

‹‹ስለዚህ አሜሪካ ልትኖሩ ነዋ››