Get Mystery Box with random crypto!

ማርጋሬት አጭበርባሪ ነው ብላ እንደማታጋልጠው ምን መተማመኛ አለው? ታዲያ ለዚህ መድሀኒቱ እሷን መ | 📚📚ቤተ__መፅሀፍት📖📗🧾📜

ማርጋሬት አጭበርባሪ ነው ብላ እንደማታጋልጠው ምን መተማመኛ አለው? ታዲያ ለዚህ መድሀኒቱ እሷን መቅረብ ነው፡፡ ፍቅር ካስያዛት ለእሱ ታማኝ መሆኗ አይቀርም፡፡
ማርጋሬት ኦክሰንፎርድን መግባባት መጥፎ አይደለም፡፡ እየደጋገመ
እየሰረቀ ያያታል፡ የእናቷን ወዘና ነው የያዘችው፤ ቅርጿ ምን እንደሚመስል ማወቅ ባይችልም ሸንቀጥ ያለች ልጅ መሆኗ ያስታውቃል የለበሰችው ልብስ ውድ ቢሆንም እንደ እናቷ ደርበብ አላደረጋትም፡፡ ምናልባት
ከዕድሜዋ ለጋነት ይሆናል፡፡ ያደረገችው ያንገት ጌጥ ውድ የሚባል አይደለም፡፡ ልጅቷ እሱ ከዚህ በፊት የጠበሳቸው ዓይነት አይደለችም፡፡ እሱ
የሚያሳድደው በቀላሉ እጁ ላይ የሚወድቁትን አስቀያሚ ሴቶች ነው:
ማርጋሬት ደግሞ ቆንጆ ሆናበታለች፡፡ ሆኖም ከጅምሩ እንደፈቀደችው
አውቋል፡፡ ስለዚህ ልቧን ሊሰርቅ ወሰነ፡፡

ኒኪ የተባለው አስተናጋጅ እነሱ ወደተቀመጡበት ቦታ መጣ፡፡ ኒኪ አጠር ያለ፣ ድብልብል ሴታ ሴት መልክ ያለው ዕድሜው ሃያ ቤት ውስጥ የሚገመት ሰው ነው፡፡ ኒኪ በእንቅስቃሴውና በአረማመዱ ወንዳወንድ ይመስላል፡ ብዙዎቹ ወንድ አስተናጋጆች እንደዚያ ናቸው:: ኒኪ የተሳፋሪዎቹንና
የአስተናጋጆቹን ስም ዝርዝር የያዘ ወረቀት ለተሳፋሪዎቹ አደለ ሄሪ ዝርዝሩን አየ፡፡ የጽዮናዊነት እንቅስቃሴ አራማጁን ሀብታሙን ባሮን ጋቦንን ያውቃቸዋል፡፡ ቀጥሎ ያሉት ፕሮፌሰር ሃርትማን ታዋቂ ናቸው፡፡ ልዕል ባዛሮቭን ባያውቃቸውም ስማቸው ራሻዊት መሆናቸውን ይጠቁማል። መቼም ኮሚኒስቶችን ሽሽት አገር መልቀቃቸው አገር ያወቀው ሃቅ ነው እኚህ ልዕልት እዚህ አይሮፕላን ላይ ተሳፈሩ ማለት ገሚሱን ሀብታቸውን
አሽሽተዋል ማለት ነው፡፡ የፊልም ተዋናይዋን ሉሉ ቤልን ዓለም ያውቃታል፡ ፊልሟን ካየ ሳምንት አልሞላውም:፡ ሊተዋወቃት ከጅሎታል።

ፔርሲ አሻግሮ አየና ‹‹የአይሮፕላኑን በር ዘጉት›› ሲል አበሰረ፡ ሄሪ ይህን ጊዜ ልቡ መሸበር ጀመረ፡፡

ሄሪ የአየር በራሪ ጀልባ ባህሩ ላይ ተቀምጦ ላይ ታች ሲል ለመጀመሪያ
ጊዜ ተገነዘበ፡፡ የአይሮፕላኑ ሞተሮች ተነሱ፡ የሞተሩን ድምጽ ለመቀነስ የድምጽ ማፈኛ በአይሮፕላኑ የውስጥ ክፍል ተገጥሟል፡፡ የኃይለኞቹ ሞተሮች መሽከርከር ደግሞ አይሮፕላኑን ያንዘፈዝፉታል፡ በዚህም ምክንያት የሄሪ ልብ መሸበር ባሰበት፡፡

መፍራቱ እንዳይታወቅበት ጋዜጣ አንስቶ እግሮቹን አቆላልፎ ተቀመጠ፡፡

ማርጋሬትም ጉልበቱን ነካ አደረገችውና ድምጿን ዝቅ አድርጋ ‹‹እኔም በፍርሃት ልቤ ሊወልቅ ነው›› አለችው:

ሄሪ አፈረ፡ ፍርሃቱን ማንም ያወቀበት አልመሰለውም ነበር ማርጋሬት መፍራቱን አውቃበታለች፡፡ ሄሪ በድንጋጤ ፊቱ አመድ መሰለ፡፡

አይሮፕላኑ ሲንቀሳቀስ ሄሪ የወንበሩን መደገፊያ ጨምድዶ ያዘው ማርጋሬት የሄሪ ፍርሃት ተጋብቶባት ሁለት እጆቿን ጉልበቶቿ መሃል ወሽቃ ተቀምጣለች፡፡ በአንድ በኩል የተጨነቀች ሲሆን በሌላ በኩል የአይሮፕላኑ ጉዞ አስደስቷታል፡፡ ጉንጮቿ መቅላታቸው፣ ዓይኖቿ ጎላ ጎላ ማለታቸውና አፏን በመጠኑ ከፈት ማድረጓ ሄሪን ልቡ እንዲከጅላት
አድርጎታል፡ ከልብሶቿ ስር ያለው አካላቷ ምን ይመስል ይሆን?› ሲል ጠየቀ ራሱን፡፡

ሄሪ ሌሎች ተሳፋሪዎችን ያማትራል፡ ፊት ለፊቱ የተቀመጠው ሰው
በጸጥታ የመቀመጫ ቀበቶውን ያጠባብቃል፡፡ የማርጋሬት እናትና አባት
በመስኮት እያዩ ሲሆን እናትየዋ የተሸበሩ አይመስሉም፡፡ ሎርድ ኦክሰንፎርድ አስሬ ጉሮሮዋቸውን ‹እህህ!› እህህ!› እያሉ ያጸዳሉ፡ የፍርሃት ምልክት መሆኑ ያስታውቅባቸዋል፡ ፔርሲ ከመደሰቱ የተነሳ ይቁነጠነጣል፡ ምንም
ፍርሃት አይታይበትም፡፡ ሄሪ ጋዜጣው ላይ ቢያፈጥም አንድ ቃል እንኳን አላነበበም፡፡ ጋዜጣውን ከደነና በመስኮት ማየት ጀመረ፡ ግዙፉ አይሮፕላን
ወደ ማኮብኮቢያው እያመራ ሲሆን ወደቡ ላይ ትልልቅ መርከቦች ከርቀት
ይታያሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ከአይሮፕላኑ መውረድ እንደማይችል ተገነዘበ፡፡

የአየር በራሪው ጀልባ ወደ ባህሩ መሃል እያመራ ነው፡ ሄሪ አይሮፕላኑ በባህሩ ማዕበል ምክንያት መዋለሉ ምቾት ነስቶታል፡፡የአይሮፕላኑ ውስጣዊ ክፍል ቤት ቢመስልም ከፍ ዝቅ ማለቱ በጀልባ
የሚጓዙ እንደሚመስል አድርጎታል።

ከዚያም አራቱ ሞተሮች ሲነሱ ድምጹ ተሰማ፡፡ በዚህ ጊዜ የሄሪ ልብ በፍርሃት ስንጥቅ አለ፡፡ አይሮፕላኑ ጉዞውን ጀመረና ቀስ በቀስ ፍጥነቱን ጨምሮ እንደ ጀልባ በረረ፡ ጀልባ ግን እንደዚህ ዓይነት ፍጥነት የለውም የሰማይ በራሪው ጀልባ ባህሩን ለሁለት እየሰነጠቀና እንደ ጀልባ ላይ ታች እያለ በፍጥነት መጓዙን ተያያዘው፡፡ በዚህ ጊዜ ሄሪ በፍርሃት ዓይኑን ጨፈነ፡፡ ‹መሞቴ ነው አለ በልቡ፡፡

ትንሽ ቆይቶ አይሮፕላኑ ልክ በኮረኮንች ላይ እንደሚሄድ መኪና መርገፍገፍ ያዘ፡፡ ምንድነው እሱ?› ሄሪ አንድ ችግር እንደተፈጠረ ገመተ፡
አይሮፕላኑ ስብርብሩ የሚወጣ መሰለ፡፡ አይሮፕላኑ እንደዚያ የተርገፈገፈው ለመነሳት ከባህሩ ሞገድ ጋር በሚያደርገው ትግል ምክንያት ነው፡ ይህም
ፍርሃት ስለፈጠረበት ሄሪን ሊያስታውከው ምንም አልቀረውም፤ ጉሮሮውን
ተናነቀው።

የአየር በራሪው ጀልባ ፍጥነቱን ጨመረ፡ ሄሪ በባህር ላይ እንደዚህ በሮ
አያውቅም፡፡ እንደዚህ የሚፈጥን ጀልባ የለም፡ ሀምሳ፣ ስልሳ፣ ሰባ ኪሎ
ሜትር በሰዓት እየተምዘገዘገ ነው፡፡ በመስኮት በኩል የሚፈናጠቀው የባህር
ውሃ የውጭ እይታውን እያደናገዘበት ነው፡፡ ወይ እንሰምጣለን›፣ ወይ
የአየር በራሪ ጀልባው ይፈነዳል› ወይም ደግሞ ይገለበጣል› ሲል ሄሪ
አዕምሮውን እያስጨነቀ ነው፡፡

አይሮፕላኑ ቀስ በቀስ ሲነሳ እንደ መርገፍገፍ አለ፡፡ ይህም በራሱ ለሄሪ
የስጋት ምንጭ በመሆኑ ይሄ ነገር የተለመደ ይሆን?› ሲል ራሱን ጠየቀ፡

ቀስ በቀስ የውሃው ጉተታና የመሬት ስበት እየቀነሰ መጥቶ የአይሮፕላኑ አፍንጫ ሽቅብ እየወጣ መሆኑን ተገነዘበ፡፡በዚህ ጊዜ ሄሪ ምራቁን ዋጠ።

የአይሮፕላኖቹ ሞተሮች እንደነጎድጓድ እየጮሁ ይህን የሰማይ በራሪ መሳሪያ ሽቅብ ያጎኑት ገቡ፡፡ ሄሪም በመስኮት ባህሩን ጥሎ ወደ ላይ እየወጣ መሆኑን አየና ይህ የሰማይ ቤተ መንግስት እንደ አሞራ እየበረረ ነው› ሲል ለራሱ ተናገረ።

አሁን አይሮፕላኑ አየር ላይ በሰላም እየበረረ መሆኑን ሲያውቅ ፍርሃቱ ለቆት መፈንደቅ ጀመረ፡፡ ልክ እሱ ራሱ አይሮፕላኑን በአየር እንዲበር እንዳደረገ ሁሉ በኩራት ተጀነነ፡፡ ጮቤ መርገጥ አሰገኘው፡፡ ዙሪያውን ሲመለከት አይሮፕላኑ ውስጥ ያለው ሰው ሁሉ በእፎይታ ይሳሳቃል፡ ታዲያ
ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ተጭኖት የነበረው የፍርሃት ድባብ በላብ ሳያጠምቀው አልቀረም፡፡ መሃረቡን አወጣና ፊቱንና ማጅራቱን አደራረቆ ኪሱ ጨመረው፡፡

አይሮፕላኑ ወደ ላይ የመውጣቱን ጉዞ አጠናቆ ሞተሮቹ ህምምም
የሚል ድምጽ እያሰሙ የፊት ለፊቱን አቅጣጫ ይዞ መብረሩን ሲያያዝ አየር
ላይ የቆመ መሰለ፡ አስተናጋጁ ኒኪ በነጭ ኮትና ጥቁር ክራቫት
ተሽሞንሙኖ መጣና ‹‹ጭማቂ ላቅርብልህ ሚስተር ቫንዴርፖስት?›› ሲል ሄሪን በትህትና ጠየቀው፡፡

‹‹ደብል ዊስኪ›› አለ ፈጠን ብሎ፡፡ ከዚያም አሜሪካዊ ነኝ ማለቱ ትዝ አለውና ‹‹በርካታ በረዶ በአናቱ ላይ ዱልበት›› ሲል አከለበት በአሜሪካውያን የአነጋገር ዘይቤ፡፡

ኒኪ ከኦክሰንፎርድ ቤተሰብ እንደዚሁ ትዕዛዝ ተቀበለና ወደ ኩሽናው ሄደ፡፡