Get Mystery Box with random crypto!

1) አማራ ክልል፤ ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እንደከበደው ገልጿል። በአማራ ክልል ምዕራብ | Feta Daily

1) አማራ ክልል፤ ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እንደከበደው ገልጿል። በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የተፈናቀሉ 300 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከወለጋ፣ ከመተከልና ከወልቃይት የተፈናቀሉ ዜጎች የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በክልሉ ከ700 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ መረጃው አመላክቷል።

2) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በዛሬው የዒድ ክብረ በዓል ላይ ሕዝበ ሙስሊሙ፣ በክልሉ መልሶ ግንባታ ሒደት ላይ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ የትግራይ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼኽ አደም ዓብደልቃድር ጁሃር በበኩላቸው፣ "የዘንድሮ ዒድ አልፈጥር በዓል፣ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሰላም እና ተስፋ መከበሩን ገልፀዋል።

3) የዒድ ሰላት ለመስገድ ከቤታቸው ወጥተው የሰላት ሥነ ስርዓቱ ላመለጣቸው የአዲስ አበባ ከተማ እና አካባቢው ሙስሊሞች በሙሉ፤ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ይቅርታ ጠይቋል። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በዛሬው ዕለት የተሰገደው የኢድ ሰላት በሰላም፣ በደስታ በመጠናቀቁ መደሰቱን በመግለጽ፤ የዒድ ሰላት ከዚህ ቀደም ሲሰገድበት ከነበረው ሰዓት ቀድሞ በመሰገዱ የዒድ ሰላት ላመለጣቸው የከተማዋ ሙስሊም ማህበረሰቦች ይቅርታ ጠይቋል።

4) በሱዳን ለኢድ የታሰበው ተኩስ ማቆም ከሽፎ ውጊያው መቀጠሉ ተመላክቷል። በሱዳን የሁለቱ ተቀናቃኝ ጄኔራሎች ወታደሮች ዛሬ ዓርብ በካርቱም ጎዳናዎች ላይ ከፍተኛ ውጊያ ሲያደርጉ ውለዋል። ዛሬ ተከብሮ የዋለውን የኢድ በዓል ምክንያት በማድረግ የተኩስ ስምምነት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ሳይከበር ቀርቷል። በሱዳን ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና በአር.ኤስ.ኤፍ መሪ ጀነራል ሞሃመድ አምዳን ደጋሎ ወይም ሄመቲ ወታደሮች መካከል ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ፣ በተለይም በመዲናዋ ካርቱምና በሌሎችም ከተሞች በተደረገው ውጊያ፣ ከ400 በለይ ሰዎች ሲሞቱ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተጎድተዋል።

5) ዩክሬን በመጨረሻ ኔቶን እንደምትቀላቀል የኔቶ ዋና ጸኃፊ ገልፀዋል። የህብረቱ ዋና ፀሐፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ''ሁሉም የኔቶ አጋሮች ዩክሬን የህብረቱ አባል እንድትሆን መስማማታቸውን አንስተው፤ ዋናው ትኩረት ሀገሪቱ በሩሲያ ላይ የበላይነትን እንድትቀዳጅ ማብቃት መሆኑን አመላክተዋል። በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ስጋት የገባቸው ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበው፣ ፊንላንድ ወታደራዊ ጥምረቱን መቀላቀሏ ይታወሳል።