Get Mystery Box with random crypto!

1) ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ጦር ከሱዳን ጋር ተጋጭቷል መባሉ ሐሰት መሆኑን ገል | Feta Daily

1) ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ጦር ከሱዳን ጋር ተጋጭቷል መባሉ ሐሰት መሆኑን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ያሉት በሁለቱ አገራት አዋሳኝ ድንበር ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ በሱዳን ኃይሎች ላይ ጥቃት ከፍቷል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ በአረብኛ ባወጡት መግለጫ ላይ ይህን አይነት ሐሰተኛ ሪፖርቶችን የሚያሰራጩ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

2) በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን በአደገኛ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች የሚበላ የሚጠጣ ከማጣታቸዉም በላይ ምንም አይነት መረጃን እንደማያገኙ ተናግረዋል። በታጣቂ ሚሊሺያዎች ንብረታችን እየተዘረፈ ነዉ ያሉት ዜጎች ከሁሉ በላይ ግን እያስጨነቀን ያለዉ ቤታችን ቁጭ ብለን በተባራሪ ጥይት አልያም የአዉሮፕላን ጥቃት ሰለባ እንዳንሆን ነዉ ማለታቸው ተሰምቷል።

3) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያቋቋመው የሰላም ልኡክ በቀጣይ ሳምንታት ወደ ትግራይ ክልል ሊጓዝ መሆኑ ተገልጿል። የሰላም ልዑኩ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሥር በትግራይ በሚገኙ አኅጉረ ስብከት መካከል የነበረው ግንኙነት መቋረጡን አስትውሷል። በትግራይ ክልል የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል በትግራይ ከልል ለሚገኙ ብፁዓን አባቶች የግንኙነት ማስቀጠያ ደብዳቤዎች ሲጻፉ መቆየታቸውንም ገልጿል። ልኡኩ የደብዳቤው ግንኙነት እንደታሰበው የተፈለገውን ውጤት ባለማምጣቱ ምክንያት ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ከብፁዓን አባቶች፣ ከሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ከታዋቂ ሰዎችና ከምዕመናን የተወጣጣ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ መሰየሙን አመልክቷል። ልኡኩ በሚቀጥሉት ሳምንታት ወደ ክልል ትግራይ በመጓዝ በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠውን ኃላፊነት የሚወጣ መሆኑን በመግለጫው አረጋግጧል።

4) የሲዳማ የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ ክብረ በዓል፥ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ በኾነችው በሐዋሳ ከተማ በሚገኙ ሶሮሳ ጉዱማሌ ሰንጎ ተከብሯል። የሲዳማ ሕዝብ የጨረቃና ከዋክብትን አቀማመጥ በማጥናት አዲስ ዓመት የሚያከብር ሲሆን፤ በዓሉም ፊቼ ጨምበላላ ይባላል። ይህ በዓል መከበር ከጀመረ ከ1800 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን የአገር ሽማግሌዎች ገልጸዋል።

5)የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተከትሎ፣ ከ2013 ዓ.ም. ሰኔ ወር በኋላ፣ በትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየውን የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ መክፈል መጀመሩን፣ የክልሉ የፋይናንስ እና የሀብት ማስተባበሪያ ቢሮ ገልጿል፡፡ የደመወዝ ክፍያው፣ የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የላከውን በጀት መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ ለመንግሥት ሠራተኞች የሦስት ወራት ደመወዛቸውን በመክፈል መጀመሩን መረጃው አመላክቷል።