Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን። #ኖላዊ_ኄር ኖላዊ ኄር ማለት መልካ | ፍኖተ ~ ጽድቅ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።

#ኖላዊ_ኄር

ኖላዊ ኄር ማለት መልካም እረኛ ማለት ነው። እረኛ እራሱ አይነት አለው መልካምም መጥፎም እረኛ አለ። ነገር ግን ለመልካሙ እረኛ ያለን መረዳት ከህይወት ወስትናችን ጋር የሚገናኝ ነው። ምስንያቱም ስለእረኛችን ማወቅ እና እረኛችንን ማወቅ እጅግ በጣም የተለያዩ ነገሮች ስለሆኑ። ስለእረኛችን ስናውቅ ስለእርሱ የሆነ መረጃ ይኖረናል ማለት ነው እረኛችንን ማወቅ እርሱን መረዳት እና እርሱን መከተል ማለት ነው።

እረኞች አደልበው ለመሸጥ ይጠብቃሉ እርሱ ግን ተሽጦ ሊገዛን ይጠብቀናል፣ እረኞች ሲርባቸው ሊበሉ ይጠብቃሉ እርሱ ግን ምግብ ሆኖ ሊያጠግበን ይጠብቀናል፣ እረኞች እየገረፉ ይጠብቃሉ እርሱ እየተገረፈልን ይጠብቀናል፣ እረኞች በገንዘብ ገዝተው ይጠብቃሉ እርሱ ግን በደሙ ገዝቶን ይጠብቀናል፣ እረኞች በድካማቸው እያረፉ ይጠብቃሉ እርሱ ግን ያለእንቅልፍ በትጋት ይጠብቀናል፣ እረኞች ዋጋ እየተከፈላቸው ይጠብቃሉ እርሱ ዋጋ እየከፈለ ይጠብቀናል፣ እረኞች ወደ ልባቸው መሻት ያሰማራሉ እርሱ ግን ወደ ለምለሙ ስፍራ ያሰማራመፈናል ጌታችን እርሱ በእውነት ኖላዊ ኄር ነው።

የምናውቃቸው እረኞች ሁሉ ከኋላ እየተከተሉ የሚመሩ ናቸው እውነተኛው እረኛችን ግን ከኋላ እያስከተለን ነው የሚመራን። የሚመጣብንን ጦር ከፊት ሆኖ ይመክታል፣ የሚወረወረውን ቀስት እርሱ ችሎት እኛን ያሻግረናል፣ ለእኛ የመጣውን ግርፋት እኔ አለው ብሎ ይገረፋል፣ ችግሩን ሳናይ ማለፍ እንድንችህ እርሱ ከፊት ሆኖ ሁሉን ይቀበላል። ከቶም ብቻችንን ሊተወን የማይችል እውነተኛ እረኛ እርሱ እግዚአብሔር ነው።

እረኛ ከሆነ ክፉ ነገር መናጋውን የሚጠብቅ ነው ክፉ ነገር በሌለበት ወይም ምንም አይነት ክልክላ ባለተሰጠበት ስፍራ የእርኛ መኖር ትርጉም ያጣል። ይህ ዓለም በሞላው በክፉ እንደ ተያዘ እናውቃለን(1ኛ ዮሐንስ 5፥19) ክፉ በሞላባት በዚች ምድር ከክፉ ማምለጫው እረኛችን ነው። ይህም እንደሌሎቹ ለጥቅሙ የሚጠብቀን እረኛ ሳይሆን ለጥቅማችን የሚጠብቀኝ እሩሩ እረኛ። እረኛ ሺ መልካም ቢሆን በጉን ላያርደው ይችላል እንጂ ለበጉ አይታረድም፣ እረኛ ሺ ደግ ቢሆን በጉን አይሸጠው ይሆናል እንጂ ለበጉ አይሸጥም። እውነተኛ እረኛ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ግን ተሽጦ የገዛን ታርዶ ያተረፈን ነው።

መቅበዝበዛችንን የገታ፣ መጥፋታችንን ያገኘ፣ መታረዳችንን የታረደ እርሱ ኖላዊ ሄር ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው።
“እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።” 1ኛ ጴጥሮስ 2፥25 ።
“መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።” ዮሐንስ 10፥11

#ወስብሃት_ለእግዚአብሔር

ዲያቆን ተስፋ መሠረት
ነሐሴ 26/2014 ዓ.ም

ይቀላቀሉ ➟ @fenote_tsedek
በቅንነት ያጋሩ ➟ @fenote_tsedek