Get Mystery Box with random crypto!

ድንግል ሆይ ወደ አንቺ መጥቶ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ያለሽ መልአክ ዛሬም ወደ እኔ ይምጣ | ፍኖተ ጽድቅ መንፈሳዊ ማህበር አንድ መንበር አንድ ፓትርያርክ አንድ ሲኖዶስ

ድንግል ሆይ ወደ አንቺ መጥቶ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ያለሽ መልአክ ዛሬም ወደ እኔ ይምጣ፡፡
ኃጢአት ያደቀቃት በኀዘን የተዋጠች ነፍሴን ከጸጋ የተራቆትሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ይበላት፡፡

ጌታ በእኔ ልብ እንዳይፀነስ ‘ያለ ኃጢአት መኖርን ስለማላውቅ እንዴት ይሆንልኛል?’ ብልም ወደ አንቺ የመጣው መንፈስ ቅዱስ ወደ እኔ በምሕረት ይምጣ፡፡ በእስራኤል ልጆች ሠፈር መና እንደወረደ የልጅሽ ምሕረት በእኔ ላይ ይውረድ፡፡

አንቺን ድንግልናን ከማጣት እንደ ጋረደሽ እኔን ከኃጢአት ይጋርደኝ፡፡ አንቺን አምላክን ለመውለድ ያጸናሽ አብ እኔን ልጅሽን በማመን ያጽናኝ፡፡ አንቺ በማሕፀንሽ ዘጠኝ ወር የፀነስሽውን ጌታ እኔ ለደቂቃዎች እንኳን በልቤ እንድፀንሰው ፍቀጂልኝ፡፡

የፀነስሁትን የኃጢአት ሃሳብ ከልቤ አውጥተሽ በሕሊናዬ ልጅሽ እንዲያድር ለምኚልኝ፡፡ ጌታን በእጆችሽ መሃል የያዝሽው ሆይ አንቺ ጌታን ለዓመታት ታቀፈሽው ነበር፡፡ እኔ ግን ለአንድ ቀን እንኳን ሰውነቴ ከኃጢአት አርፎ እሱን ብቻ ታቅፌ እንድውል ፍቀጂልኝ፡፡

እርግጥ ነው ወደ እኔ ልጅሽን ይዘሽ ስትመጪ እንደ ቤተልሔም የእንግዶች ማደሪያ የእኔም ልብ የብዙ እንግዳ ኃጢአቶች ማደሪያ ነውና ልጅሽን ለማስተኛት ቦታ የለኝም ብዬ የልቤን በር ልዘጋብሽ እችላለሁ፡፡

በሩን ብዘጋውም ግን ልጅሽ እንደሆነ ‘በደጅ ቆሞ ማንኳኳት’ እንደማይሰለቸው አውቃለሁ፡፡ ራእ.፫፥፳
እኔ ፈቅጄ ባልከፍትለትም እንኳን የድንግልናሽን ማኅተም ሳይከፍት እንደተወለደ የእኔን የተዘጋም ልብ ሳይከፍተው መግባት አይሳነውም፡፡

ስለዚህ ዐመፄና እምቢታዬን ቸል ብለሽ ለልጅሽ ማደሪያ አድርጊኝ፡፡ አንቺ እርሱን ከወለድሽ ወዲያ በታተመ ድንግልና ጸንተሽ እንደኖርሽ ለልጅሽ ማደሪያ ሆኜ ለሌላ የኃጢአት ፅንስ ዳግም ማደሪያ እንዳልሆን ነፍሴን አትሚልኝ፡፡

የወለድሽው መድኃኒት እኔን ዙፋኑ አድርጎ ቢቀመጥ ሰዎች በእኔ እቅፍ ስላለ ብቻ በእኔ ምክንያት እንደ ሰብአ ሰገል እንደሚሰግዱለት በአንቺ ሲሆን አይቻለሁና ሰዎች በእኔ ምግባር ምክንያት ፈጣሪን መስደብ ትተው እጅ መንሻ ያቅርቡለት፡፡
ለልጅሽ በቀረቡ ሥጦታዎች ተከብቤ ከአንቺም ጋር ፦ ‘ጌታ ሆይ ለአንተ የሚሰግዱልህ ሰዎች ዙሪያዬን ከበቡኝ ፤ ለአንተ በቀረቡ ሥጦታዎችም ዙሪያዬን ታጠርኩ’
ብዬ ላመስግነው፡፡

ድንግል ሆይ አንቺን ያሳደደሽ ሔሮድስ እኔን የማያሳድደኝ ጌታ በእቅፌ ስለሌለ ነው፡፡ እኔ በልቤ ያነገሥሁት ‘የተወለደውን የአይሁድ ንጉሥ’ ስላልሆነ ሔሮድስ ከእኔ ጋር ጠብ የለውም፡፡ የሔሮድስን ሥልጣን አደጋ ላይ የሚጥል ንጉሠ ሰላም በእኔ እቅፍ የለም፡፡ አሁን ግን ፍቀጂልኝና ሔሮድስን ማስደሰት ትቼ ልጅሽን በልቤ ልቀበለው፡፡

የልቤን ክርስቶስ ሔሮድስ እንዳይገድልብኝ እኔም እንደ አንቺ ልሰደድ፡፡ እሱን አቅፌ መከራ ቢደርስብኝ እንኳን ጽናት እንደማገኝ በአንቺ አይቻለሁና የልጅሽን ፍቅር በልቤ አኑሪልኝ፡፡ ለሦስት ቀናት ከፊትሽ ዞር ቢል ፍለጋ የወጣሽዋ ድንግል ሆይ ከእኔ ሕይወት ልጅሽ ከተሠወረ ቆይቶአልና ያለ እርሱ መሰንበት የማልችል የፍቅሩ ምርኮኛ አድርጊኝ”

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የብርሃን እናት - ገፅ 305-308