Get Mystery Box with random crypto!

በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ የአባ ሰንጋ በሽታ በመከሰቱ ህብረተሰቡ ስጋ ከመመገብ እንዲቆጠብ ተገለፀ። | FastMereja.com

በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ የአባ ሰንጋ በሽታ በመከሰቱ ህብረተሰቡ ስጋ ከመመገብ እንዲቆጠብ ተገለፀ።

ጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም በካፋ ዞን የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከተማ ግብርና ጽ/ቤት የእንስሳት ጤና ባለሙያ የሆኑት አቶ ወንድሙ አበበ እንደገለፁት ፣ ለቅዳሜ እርድ ከተዘጋጁ የእርድ በሬዎች ውስጥ አንድ በሬ በድንገት በአባ ሰንጋ በሽታ ምክንያት ሞቶ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በሬው ከመሞቱ በፊት ከሌሎች በሬዎች ጋር የተቀላቀለ በመሆኑ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሌሎች በሬዎች ላይ የበሽታው ምልክት ታይቷል ብለዋል፡፡

በአፍ ፣ በአፍንጫና በቂጥ እንዲሁም ላም ከሆነች በሽንት መሽኛ ቀዳዳ የደምና መሰል ፈሳሽ በሚታይበት ጊዜ የአባ ሰንጋ በሽታ መሆኑ ይጠረጠራል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

አባ ሰንጋ ከሰው ወደ እንስሳ ፣ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ ገዳይ በሽታ ነው ያሉት አቶ ወንድሙ ፣ ከዞንና ከከተማ መዋቅር የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን እርድ እንዳይካሄድ ውይይት በማድረግ ተወስኗል ብለዋል፡፡

በሽታው እጅግ አጣዳፊ በመሆኑ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በአከባቢው የሚገኙ ከብቶችን በማከም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ጥረት እናደርጋለን ሲሉ አክለዋል፡፡

አቶ ወንድሙ አያይዘውም እርድ ከማገድ ባለፈ ለእርድ የተዘጋጁ በሬዎች በባለሙያዎች መታየት እንዳለባቸው ገልጸው ፣ የሞተውን በሬ አከባቢውን በማይበክል ሁኔታ ለመቅበር ከማዘጋጃ ቤት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ግብዓት የማዘጋጀት ሥራ በመሠራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የአከባቢው ነዋሪዎች የእንስሳት ኮቴ ተቆጥሮ የበሽታው ስርጭት ያለመስፋፋቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ማንኛውንም እርድ ማካሄድ እንደማይገባቸው ተናግረው ፣ ህብረተሰቡ ላልተወሰነ ጊዜ ስጋ እንዳይመገብ አሳስበዋል፡፡

ለእርድም ሆነ ለሌሎች አገልግሎቶች የቁም እንስስሳት በተለይም የበሬ ሰንጋዎች ከተለያዩ ወረዳዎች ወደ ተለያዩ አከባቢዎች የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታዎች ስላሉ ፣ ላልተወሰነ ጊዜ የቁም የእንስሳት ከቦታ ቦታ ከማዘዋወር ህብረተሰቡ እንዲታቀብም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘገባው :- የቦንጋ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው፡፡