Get Mystery Box with random crypto!

ብሔራዊ ባንክ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለሚጠቁሙ ወሮታ ሊከፍል ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ | FastMereja.com

ብሔራዊ ባንክ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለሚጠቁሙ ወሮታ ሊከፍል ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገሪቱ የሚካሄዱ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር በጥቆማ ለሚተባበሩ ግለሰቦች የተለያየ መጠን ያለው ወሮታ እንደሚከፍል አስታወቀ።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ መንግሥት ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቱ እየተባባሰ ያለውን የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በሕገወጥ መንገድ የሚካሄዱ የተለያዩ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር ያስችላሉ ያላቸውን እርምጃዎችን አሳውቋል።

በዚህም ምክንያት በባንክ ከተፈቀደው በላይ የገንዘብ መጠን ይዘው የሚገኙ ግለሰቦችን ለጠቆሙ ከተያዘው ገንዘብ 15 በመቶ፣ የውጭ አገር ገንዘብ ዝውውር ለሚጠቁሙ 15 በመቶ፣ ሕገወጥ ሐዋላን ለሚጠቁሙ 25 ሺህ ብር ወሮታ ብሔራዊ ባንክ እንደሚከፍል ገዢው አሳውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የወርቅ ኮንትሮባንድ ለሚጠቁሙ 15 በመቶ የወርቁን ዋጋ፣ የሐሰተኛ የገንዘብ ኖት ህትመትን ለሚጠቁሙ ከ20 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር የሚደርስ ወሮታ እንደሚከፈልም ተገልጿል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ እየጨመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የምንዛሪ ዋጋ ከዚህ በፊት ከነበሩት ሁሉ ከፍተኛው መሆኑን ነጋዴዎች ይናገራሉ።

በዚህም በይፋዊው የባንኮች ግብይት የዶላር የምንዛሪ ዋጋ የአንድ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ 52 ብር አካባቢ ሲሆን፣ በጥቁር ገበያ በእጥፍ እንደሚመነዘር ነጋዴዎች ገልጸዋል።

ዶክተር ይናገር ደሴ እንዳሉት ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር መንግሥት እስካሁን በወሰዳቸው እርምጃዎች 391 ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ እና የሐዋላ ሥራ ሲያከናውኑ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ ተይዟል።

ቢቢሲ አማርኛ