Get Mystery Box with random crypto!

ከአርሰናል ደጋፊዎች ጋር ተወራርዶ 15 እንቁላል የዋጠው ኬንያዊ የዩናይትድ ደጋፊ ሆስፒታል ገባ | FastMereja.com

ከአርሰናል ደጋፊዎች ጋር ተወራርዶ 15 እንቁላል የዋጠው ኬንያዊ የዩናይትድ ደጋፊ ሆስፒታል ገባ

ኤልዶሬት በተባለችው የኬንያ ግዛት 15 የተቀቀለ እንቁላል የዋጠው የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ መጨረሻ ሆስፒታል ሆኗል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ያሸንፋል ብሎ የአርሰናል ደጋፊ ከሆኑ ጓደኞቹ ጋር ውርርድ የገባው ቶማስ ኪፑታኒ ኬምቦይ ዩናይትድ ከተሸነፈ 30 የተቀቀለ እንቁላል ለመብላት መወራረዱን የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ፅፈዋል።

ባለፈው እሑድ አርሰናል በኤሜሬትስ ስታድየም ማንቸስተር ዩናይትድ ሲያስተናግድ ነው ይህ የሆነው።

ዩናይትድ በጨዋታው 3-1 መረታቱን ተከትሎ አንድ ሙሉ ትሪ እንቁላል ለመዋጥ ቃል የገባው ኬምቦይ ከጨዋታው በኋላ ቃሉን መፈፀም ይጀምራል።

ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጩ ምስሎች ግለሰቡ ጓደኞቹ እያበረታቱት በየመሐሉ ውሃ እየጠጣ የተቀቀለ እንቁላል ሲውጥ ያሳያሉ።

ሲቲዝን የተሰኘው ሚድያ እንደዘገበው ኬምቦይ 15ኛው እንቁላል ላይ ሲደርስ ራሱን ስቶ ሲወድቅ ጓደኞቹ እየቀለደ መስሏቸው ሲሳሳቁ ነበር።

ግለሰቡ ራሱን ስቶ መውደቁን የተረዱት ጓደኞቹ ከወደቀበት አፋፍሰው ወደ ሆስፒታል ይዘውት ይሄዳሉ።

የሲቲዝን ዘገባ እንደሚያሳየው ካፕኬኖ በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ተመርምሮ የሆድ ድርቀት እንዳለበት ታውቋል።

ከሕመሙ እስኪያገግም ድረስ ሆስፒታል ቆይቶ ጤናው መለስ ሲል እንደወጣ የኬንያ መገናኛ ብዙኃን አስነብበዋል።

“መጀመሪያ በጣም ደስ ብሎኝ እንቁላሉን ስበላ ትዝ ይለኛል። ከዚያ ስነቃ ሆስፒታል ውስጥ ራሴን አገኘሁት። አሁን ጤናዬ ስለተመለሰ ደስተኛ ነኝ” ሲል ካፕኬንኮ ስታንዳርድ ለተሰኘው ጋዜጣ ተናግሯል።

እሑድ ዕለት በብዙዎች ዘንድ ሲጠበቅ የነበረው የአርሰናል እና የማንቸስተር ዩናይትድ ፍልሚያ በመድፈኞቹ የበላይነት ተጠናቋል።

ማንቸስተር ዩናይትድ በራሽፈርድ ጎል ጨዋታውን መምራት ቢችልም አርሰናል በፈጣን ምላሽ በኦዴጋርድ ጎል አቻ መሆን ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው አሌሃንድሮ ጋርናቾ ቀያይ ሰይጣኖቹን መሪ የምታደርግ ኳስ ከመረብ ቢያገናኝም ቪኤአር ጎሉ ከጨዋታ ውጭ ነው ሲል ሽሮታል።

ከዚህ ክስተት በኋላ አርሰናል በዴክለን ራይስና በሄሱስ ጋብርኤል ጎሎች ዩናይትድን 3-1 መርታት ችሏል።

በሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች መካከል ያለው ፉክክር በተለይ በአህጉረ አፍሪካ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው።

ዘገባው የቢቢሲ አማርኛ ነው!

@fastmereja