Get Mystery Box with random crypto!

'ቡዳ ይሉናል፤ ጅብ ይሉናል፤ሌሊት ሌሊት ወደ ጅብነት የሚቀየሩ ይሉናል። 3,000 ዓመታት በኖርንበ | FastMereja.com

"ቡዳ ይሉናል፤ ጅብ ይሉናል፤ሌሊት ሌሊት ወደ ጅብነት የሚቀየሩ ይሉናል። 3,000 ዓመታት በኖርንበት አገር ውስጥ ፈላሻ የሚለው ስም መሬት አልባ ለማለት ነው። እዚህ አገር ላይ መሬት የላችሁም ፈልሳችሁ ነው የመጣችሁት የሚል ነው። ይህ ስም ማጠልሸት የስንቱን ትዳር ያናጋና ብዙ ማሕበራዊ ቀውስ ያመጣ ነው።"

በሰሜን ሽዋ በተለያዩ ወረዳዎች ተበትነው እምሮአዊና አካላዊ የጤና ችግር ላለባቸዉ ቤተእስራኤላውያን ጤናማ የሰፈራ መንደር ለመመስረት የተጀመረው ፕሮጀክት። ቤተ-እስራኤላውያን ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በ3 ዙሮች እንደሆኑ በጉዳዩ ላይ ሁለት መጽሐፎችን ያሳተሙት የቤተእስራኤላውያን የኦሪት እምነት ማሕበረሰብ ስራ አስኪያጅና እና የሰሜን ሽዋ የቤተእስራኤላውያን የሰፈራ መንደር ፕሮጀክት ፕረዚደንት መምህር በላይነህ ታዘብኩ ይገልጻሉ።

ጎንደር ደምቢያ ማዕከል አድርገውም ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደ ተንቀሳቀሱም አክለዋል። ቤተ እስራኤላውያኑ በአገሪቱ ታሪክ የራሳቸውን አሻራ እንዳኖሩም ያስረዳሉ።

«ወርቅ ላበደረ ጠጠር ሆነና ነገሩ» ይላሉ መምህር በላይነህ በአገሪቱ ግንባታ የራሳቸውን ሚና ለተጫወቱት እና በመጫወት ላይ የሚገኙት ሕዝቦች የተሰጣቸው ስምና መገለል ግን ሥነ አእምሮዊ እና አካላዊ የጤና ችግር እንዳስከተለባቸው የገለጹት መምህር በላይነህ ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ።

"ቡዳ ይሉናል፤ ጅብ ይሉናል፤ ሌሊት ሌሊት ወደ ጅብነት የሚቀየሩ ይሉናል። ካይላት፣ ቂሌ የተለያዩ ስሞች አሉ የተሰጡን። 3,000 ዓመታት በኖርንበት አገር ውስጥ ፈላሻ የሚለው ስም መሬት አልባ ለማለት ነው። እዚህ አገር ላይ መሬት የላችሁም ፈልሳችሁ ነው የመጣችሁት የሚል ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ የምትኮራባቸው ሦስቱ ሐይማኖቶች ኦሪት፣ ከዛ ክርስኅና ከዛ ክርስትና እነዚህ ሐይማኖቶች ከውጭ እንደመጡ ይታወቃል። የኛን ብቻ ነው ፈልሶ እንደመጣ ተደርጎ የሚወሰደው። ማምለኪያ ቦታዎች፣ የቀብር ቦታዎች እንዳይኖረው ማድረግ፤ ይህ ስም ማጠልሸት የስንቱን ትዳር ያናጋና ብዙ ማሕበራዊ ቀውስ ያመጣ ነው።"

የሚገርመው የአፍሪቃ መዲና በምትባለው አዲስ አበባ የሚኖሩ ቤተእስራኤላውያን እስከዛሬዋ ድረስ ሞተው የሚቀበሩበት ቦታ እንኳን የላቸውም። ሞተው እንደሰው የመቀበር ዕድልን ለማግኘት ከሚኖሩበት አካባቢ ሐይማኖት ጋር ተመሳስለው እና ማንነታቸውን አጥፍተው ጭምር እንደሆነ መምህር በላይነህ በምሬት አጫውተውናል።

ቤተ እስራኤላውያን በማሕበረሰቡ በሚደርስባቸው አድልኦ እና መገለል ምክንያት፤ ተከትሎ የመጣውን የሥነ አዕምሮአዊና አካላዊ ችግሮች በመቅረፍ ፈር ቀዳጅ ይሆናል የተባለለት ፕሮጀክት በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን ደብረብርሐን አካባቢ እውን ሊሆን ጫፍ የደረሰ ይመስላል። የሰሜን ሽዋ ቤተእስራኤላውያን የመንደር ምስረታ። የፕሮጀክቱ ሰብሳቢ ዶክተር አክሊሉ ተፈራ።

"የፕሮጀቱ ዓላማ ቤተ እስራኤላውያን በመንደር ተሰባስበው ጤናቸው ተጠብቆ፤ ጽዱና ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት እና ትምህርት ቤት በመገንባት የተሻለ ኑሩ እንዲኖሩ ማስል ነው። "

የቤተ እስራኤላውያን አንዱና ትልቁ ችግር ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት አለማግኘት ነው። በዚሁ ምክንያት ሕይወቷን ያጣች ወላጅ እናት፤ ሕጻን አዛውንቱ ቤት ይቁጠረው ብሎ ማለፍ ሳይሻል አይቀርም። ይህን ችግር ለመቅረፍ ግዙፍ ሆስፒታል መገንባት የፕሮጀክቱ አካል እንደሆነ ዶክተር አክሊሉ ነግረውናል።

ቤተእስራኤላውያን አዲስ አበባን ጨምሮ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የመጸዳጃና የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚያገኙት ዝቅተኛ ሊባል በሚችል ደረጃ መሆኑን የገለጹት መምህር በላይነህ በደብረብርሃን የሚሰሩ መኖሪያ ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁና የነበሩባቸውን ችግሮች የሚፈቱ እንደሚሁኑ ገልጸውልናል።

ትኩረት ተነፍጓቸው በአስከፊ ኑሮ ውስጥ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ተገቢው ትኩረትና ክብር ሊሰጣቸዉ እንደሚገባ ባለጉዳዮች ያሳስባሉ።

ዘገባው የዶይቼ ቬለ ነው።

@fastmereja