Get Mystery Box with random crypto!

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ ጉዳትና ኪሳራ ማድረሱን መንግሥት ይፋ አደረገ | FastMereja.com

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ ጉዳትና ኪሳራ ማድረሱን መንግሥት ይፋ አደረገ
#FastMereja
በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም ማዕከሉን በትግራይ ክልል አድርጎ ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት፣ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳትና ኪሳራ በአገር ላይ መድረሱን ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ አደረገ።

ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. የገንዘብ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ተቋማቸው በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተካሄደው ጦርነት የደረሰውን ጉዳትና የመልሶ ግንባታ ፍላጎት የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት (Damage and Needs Assessment) በማከናወን፣ የጥናት ውጤቱን ለመንግሥት እንዳቀረበ ተናግረዋል።

በጥናት ግኝቱ መሠረትም ያጋጠመው አጠቃላይ ጉዳትና የኢኮኖሚ ኪሳራ በአጠቃላይ 28 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ሪፖርታቸው አመላክቷል። ይህም በወቅቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ ነው።
ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት ሪፖርት ላይ ከተቀመጠው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ ‹‹22 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 20.4 በመቶ የሚገመት ጉዳት›› ደርሷል።

በዚሁ ምክንያት የደረሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ ደግሞ፣ ‹‹ስድስት ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 5.5 በመቶ የሚገመት የኢኮኖሚ ኪሳራ (Economic Loss)›› መድረሱን ሪፖርቱ ያመለክታል።
ግጭትና ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ጠቅላላ ነዋሪዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በጦርነቱ በቀጥታ የተጎዱ መሆናቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑት የአገሪቱ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት የከፋ ድህነት ውስጥ መግባታቸውንም አስረድተዋል።

ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት የተቀመጠው የጉዳት መጠን፣ ኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት ከውጭ አበዳሪዎች ለኢኮኖሚ ልማት ተበድራ ካልመለሰችው አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ጋር እኩል መሆኑን መረዳት ይቻላል። የገንዘብ ሚኒስቴር በየሩብ ዓመቱ ይፋ በሚያደርገው የዕዳ ሁኔታ መግለጫ መሠረት፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለባት አጠቃላይ የውጭ ዕዳ መጠን 28 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ዘገባው የሪፖርተር ነው

@fastmereja