Get Mystery Box with random crypto!

በቀን እስከ 35ሺ ብር የሚቆጥቡ ሿሿ ሰሪዎች #FastMereja ፖሊስ ባደረገው ብርቱ ክትትል በ | FastMereja.com

በቀን እስከ 35ሺ ብር የሚቆጥቡ ሿሿ ሰሪዎች
#FastMereja
ፖሊስ ባደረገው ብርቱ ክትትል በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተለምዶ ሿሿ የሚባለውን ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራውን መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ወንጀል ፈፃሚዎቹ በቀን እስከ 35ሺ ብር ተቀማጭ  እንደሚያደርጉ በምርመራ ተረጋግጧል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ህዝብን ለምሬት ከዳረጉ የወንጀል ድርጊቶች መካከል በተለምዶ ሿሿ የሚባለው ወንጀል አንዱ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀሉን ለመከላከል እና ወንጀለኞቹን ህግ ፊት ለማቅረብ በጥናት ላይ ተመስርቶ ባከናወነው ተግባር በተለያዬ ክፍለ ከተሞች ወንጀሉን ሲፈፅሙ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ አያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡

ወንጀል ፈፃሚዎቹ ኃይል በመጠቀም ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓ/ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አንበሳ ጋራዥ አካባቢ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኦሮ 86853 ነጭ ሚኒባስ በመጠቀም ከአንድ ግለሰብ ላይ 10ሺ ብርና ግምቱ 14 ሺብር የሚወጣ ሞባይል ስልክ ሰርቀው ይሰወራሉ፡፡ ፖሊስ ጠንካራ  ክትትል  በማድረግ ወንጀል ፈፃሚዎቹን ከእነ ተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር በማዋልና ምርመራ በማስፋት ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የሚፈፅሙ 14 ወንጀል ፈፃሚዎችን እና  የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 ኦሮ 79184 ሚኒባስ ተሽከርካሪን ሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ /ም ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ ፋንታ አስታውቀዋል፡፡

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ግለሰቦች በቦሌ ክፍለ ከተማ 6 ቦታዎች ፣ በየካ ክፍለ ከተማ 3 ቦታዎች እንዲሁም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 3 ቦታዎች ላይ ወንጀሉን መፈፀማቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

አቶ በሪሁን ካሳው ይባላሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ስፍራው ዘሪሁን ህንፃ አከባቢ ሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ/ም ግምቱ 10ሺ ብር የሚያወጣ  ሞባይል ስልክ በወንጀል ፈፃሚዎች  የተሰረቀባቸው  ቢሆንም ፖሊስ ንብረተቻውን ማስመለሱን ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ አቶ አበበ በቀለ ወደ ስራ በመሄድ ላይ እያሉ በእነዚሁ ወንጀል ፈፃሚዎች ግምቱ 10ሺ ብር የሚያወጣ ስልክ መሰረቃቸውን እና ፖሊስ ባደረገው ክትትል በተሰረቁ ጥቂት ሰዓት ውስጥ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ተይዘው  ንብረታቸው መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

በዚህ የወንጀል ድርጊት ተሳትፎ ያላቸው 19 ወንዶችና 6 ሴቶች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ሁለት ሚኒ-ባስ መኪናዎች እንዲሁም ግለሰቦቹ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚጠቀሙባቸው 4 ልዩ ልዩ ተሸከርካሪዎች ፣ 82 ሺ 680  ጥሬ ብር ፣ 14 ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ስማርት ስልኮች እና የቀን ተቀማጭ የሚያስቀምጡበት ደብተር በኤግዚቢትነት እንደተያዘ ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ ፋንታ አስረድተዋል፡፡

ግለሰቦች ምንም አይነት ህጋዊ ገቢ የሚያገኙበት ስራ የሌላቸው ቢሆንም ከፍተኛው በቀን 35 ሺ ብር አነስተኛው 5ሺ ብር የቀን ተቀመጭ ሲያደርጉ እንደነበር  በኤግዚቢትነት ከተያዘው ሰነድ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ ስፍራዎች ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የተፈፀመባቸው ግለቦች አዲስ አበባ ፖሊስ  ጉለሌ ክፍለ በመቅረብ በኤግዚቢትነት ከተያዙ ስልኮች መካከል መምረጥ እንደሚችሉ ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ አስታውቀዋል፡፡

በተለምዶ ሿሿ የሚባለውን ወንጀል የሚፈፅሙ ወንጀለኞች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለው ወንጀሉን እንደሚፈፅሙ እና መነሻና መድረሻ የሌላቸው ሲሆኑ  ተሳፋሪውን የትነው የምትሄደው የሚል ጥያቄ እንዲሚያቀርቡ ህብተሰቡ ተገንዝቦ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደለበት ኃላፊው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ሲል አዲስ አበባ ፖሊስ ገልፇል።

@fastmereja