Get Mystery Box with random crypto!

«በትግራይና በኦሮምያ አካባቢዎች ያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎች ከቤተክህነት አልፈው የሕዝብም ጭምር እየሆ | FastMereja.com

«በትግራይና በኦሮምያ አካባቢዎች ያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎች ከቤተክህነት አልፈው የሕዝብም ጭምር እየሆኑ ስለመጡ የሕዝቡን ጥያቄ በትክክል በማዳመጥ ሃይማኖቱንና ቀኖናውን በጠበቀ መልኩ በጥበብና በፍቅር ጥያቄአቸውን አክብረን መቀበል ያሻል፤ ጉዳታቸውንም መካፈል ይገባናል፡፡በአጠቃላይ አባትና እናት ለልጆቻቸው ሊያደርጉት የሚገባውን በማድረግ ልናቀርባቸውና ልናቅፋቸው ይገባል፡፡

እኛ ያጐደልነው፣ የተሳሳትነውና ያስቀየምነው ካለም ይቅርታ ለመጠየቅም ሆነ ንስሐ ለመግባት ድፍረቱ ሊኖረን ይገባል፡፡ ታረቁ፣ ይቅር በሉ፣ንስሐ ግቡ ብለን የምናስተምር እኛ ይቅርታ ለመጠየቅና ንስሐ ለመግባት ዓቀበቱ ሊከብደን አይገባም፡፡ የተከሠተው ችግር በዚህ ክርስቶሳዊ ጥበብ ሊቃለል እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡
በሌላ በኩል በሀገራችን ያለው የሰላም ሁኔታ በአንድ ወገን የተረጋጋ ሲመስል በሌላ በኩል ደግሞ የመንገጫገጭ ሁኔታ እየተከሠተ እንደሆነ እያየን ነው፡፡ይህም ሂዶ ሂዶ ቤተክርስቲያንንና ሕዝብን፣ ሀገርን ልማትን መጕዳቱ የማይቀር ነው፡፡
በመሆኑም ቤተክርስቲያን ያለ ሀገርና ያለ ሕዝብ ህልውና የላትምና ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት፣ የሕዝቦቿን አንድነትና ልማት ለማረጋገጥ፣ በሃይማኖታዊ መርሕና መንፈስ፣በገለልተኛ አቋምና በሁሉም ዓቃፊነት ስልት ለሰላም ጠንክረን መስራት ይኖርብናል፡፡»

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

@fastmereja