Get Mystery Box with random crypto!

በኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ አዋሳኝ ቦታዎች በእገታ እና ዝርፊያ ሕዝቡ እየተሰቃየ ነው በኦሮ | 𝗙𝗔𝗡𝗔 𝗧𝗩 (ፋና)️ ️️

በኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ አዋሳኝ ቦታዎች በእገታ እና ዝርፊያ ሕዝቡ እየተሰቃየ ነው
በኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ከኑሮ ውድነቱ በተጨማሪ፤ አፈና እና ዝርፊያ በከፍተኛ መጠን ሕዝቡን እየጎዳ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡
በዋናነት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞንና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን መካከል የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በአካባቢው የሚያደርጉት ውጊያ እና ዘረፋ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡
በዚህም በኹለቱ አዋሳኝ ዞኖች የመንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት ከተቋረጠ ከሦስት ወራት በላይ ማስቆጠሩን የገለጹት ነዋሪዎች፤ “በተደጋጋሚ ብንጠይቅም መፍትሔ የሚሰጥ አካል አላገኘንም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በተለይም ከካማሺ ወደ ኦሮሚያ ክልል ነጆ እና ጊምቢ ዞኖች የሚወስደው ዋናው መንገድ ሙሉ ለሙሉ መዘጋቱን እና ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለመኖሩን ነው የተናገሩት፡፡
መሠረታዊ ፍጆታዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች የሚገቡት በዚሁ መንገድ ቢሆንም፤ በመንገዱ መዘጋት የተነሳ ከየካቲት ወር ወዲህ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች እየገቡ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ክፉኛ መጎዳታቸው ነው የተጠቀሰው፡፡
እንዲሁም የአካባቢው የአየር ጠባይ ቆላማ መሆን ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት እንዲኖር አድርጓል የተባለ ሲሆን፤ በትራንስፖርት መቋረጥ የተነሳ የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ የሰው ሕይወት እየጠፋ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
ነዋሪዎቹ አክለውም “የአገር መከላከያ ሠራዊት በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ላይ ተደጋጋሚ እርምጃ እየወሰደ ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ ግን መንገዱን ማስከፈት አልተቻለም” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ “ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ብናመለክትም መፍትሔ ልናገኝ አልቻልንም” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በአሶሳ በኩል የተወሰኑ እቃዎችን ወደ ምዕራብ ወለጋ ለማስገባት ጥረት የተደረገ መሆኑን በመጥቀስ፣ ዝናብ በመዝነቡ እና መንገዱ በመበላሸቱ እሱም ሳይሳካ ቀርቷል ነው የተባለው፡፡
የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተለይ በወለጋ አካባቢዎች በሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች በርካታ ንፁሐን ዜጎች ሕይወታቸውን እንዳጡና ብዙዎችም እንደተፈናቀሉ ይጠቀሳል፡፡