Get Mystery Box with random crypto!

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከፅንሰታቸው ጀምሮ በሐዋርያዊ ተግባራቸውና ተጋድሏቸው ውስጥ ፈቃደ እግዚአብሔ | የደ/ም/ሰ/ም/ቅ/ማርያምና ቅ/ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል እውቀት ብርሃን ሰ/ት/ቤት

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከፅንሰታቸው ጀምሮ በሐዋርያዊ ተግባራቸውና ተጋድሏቸው ውስጥ ፈቃደ እግዚአብሔርን  ሲፈጽሙ ነውና የኖሩት፤ ስለ ዕረፍታቸው ጌታቸውን እንዲህ ሲሉ ጠይቀዋል ‹‹ጌታዬ ወደ ሰማዕትነት አደባባይ ሄጄ በስምህ እንድሞት እዘዘኝ››፡፡ ጌታችንም ‹‹መጋደልንስ ፈጸምህ፣ ከሞት በቀር ምንም ምን አልቀረህም፤ እነሆ በክፉ ሞት በሕማመ ብድብድ በሆድ ሕመም በጽኑ ደዌ በንዳድ ትሞታለህ፤ እሷንም እንደ ስቅላቴና ካንተ በፊት እንደነበሩ ሰማዕታት ደም እቆጥረዋለሁ፤ ነገር ግን ለብቻህ አይደለም፤ በዚህች ገዳም በዚህ ዓይነት ደዌ የሚሞቱትን ቁጥራቸውን ከሰማዕታት ጋር አደርገዋለሁ፤ በመንግሥተ ሰማይም ለአንተ እሰጣቸዋለሁ›› አላቸው፡፡ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር መከራ ለቅዱሳን ክብራቸውን የሚያበዛላቸው ከተሰቀለው ክርስቶስ ጋር በግብር የሚያመሳስላቸው መሆኑን ነው፤ 1ኛ ጴጥ 4፥13፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበላቸው ሕማማተ መስቀል ለቤዛ ዓለም ሲሆን የቅዱሳን ግን ስለ ክርስቶስ ክብር እስከ ደም ጠብታ ደርሶ መመስከርን የሚያጠይቅ ነው።
  ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት አስቀድሞ እንደ ነገራቸው ሦስት ደቀ መዛሙርቶቻቸው በሕማመ ብድብድ በሽታ ከሞቱ በኋላ ጻድቁ አባታችንም ለ10 ቀናት በሕመም ቆይተው ዕረፍታቸው ሲደርስ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾላቸዋል፡፡ ‹‹ወዳጄ ተክለ ሃይማኖት ሆይ! ከብዙ ድካም ወደ ዕረፍት፣ ከመከራ ወደ ደስታ ላሳርፍህ መጥቻለሁ፤ ጾምና ጸሎትህን ተቀብዬልሃለሁ፤ ስምህን በቅን ሕሊና የሚጠራውን ሁሉ ከመከራው አድነዋለሁ፤ በስምህ ዝክር የሚዘክሩና መታሰቢያህን የሚያደርጉትን አንተ ከገባህበት ውሳጤ መንጦላዕት አስገባቸዋለሁ›› የሚል ቃል ኪዳንም ሰጥቷቸዋል፡፡ ‹‹ከአንተ በኋላ በመንበርህ ላይ ኤልሳዕ ይሾማል፤ ግን ብዙ ጊዜ አይቆይም ያርፋል›› አላቸው፡፡ የጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ቅድስት ነፍስ ከክብርት ሥጋቸው ነሐሴ 24 ቀን በይባቤ መላእክት፣ በመዓዛ ገነት፣ በመዝሙረ ዳዊት ተለየች፡፡ አርድዕቱ ቅዱስ ሥጋቸውን እንደ ሥርዓቱ ገንዘው በስብሐተ እግዚአብሔር በማኅሌት ከቁመት ብዛት እግራቸው በተሰበረበት በትሩፋት ሥራ በስግደት ብዛት ወዛቸው በተንጠፈጠፈበት በደብረ አስቦ ዋሻ አሳረፉት፡፡
   አቡነ ተክለ ሃይማኖት ባረፉ በ56ኛው ዓመት ሦስተኛው ዕጨጌ አቡነ ሕዝቅያስ አበምኔት በሆኑ ጊዜ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በራእይ ለአቡነ ሕዝቅያስ ተገልጠው ዐፅማቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲያስገቡ ነገሯቸው፤ እርሳቸውም በየቦታው የነበሩትን ደቀ መዝሙሮቻቸውን ጠርተው ግንቦት 12 ቀን ዋሻውን ከፍተው ዐፅማቸውን በክብር አወጡት፤ ወደ ደብረ ሊባኖስ ቤተ ክርስቲያንም አስገቡት፡፡
   የጻድቁ መላ ዕድሜያቸው 99 ዓመት ከዐሥር ወር ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ የጻድቁን ፅንሰታቸውን መጋቢት 24 ቀን፣ልደታቸውን ታኅሣስ 24 ቀን፣ ስባረ ዐፅማቸውን ጥር 24 ቀን፣ ዕረፍታቸውን ነሐሴ 24 ቀን፣ ፍልሠተ ዐፅማቸውን ግንቦት 12 ቀን እግዚአብሔርን በማመስገን ጻድቁን በማክበር በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብራለች፡፡ የጻድቁ በረከት ከሁላችን ጋር ትሁን አሜን!
               ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
       ምንጭ፦ ገድለ ተክለ ሃይማኖት ፣ ስንክሳር ዘነሐሴ 24
- ሕይወቱ ወገድሉ ለብፁዓዊ ቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት (አውሎግሶን)

            

ሊንኩን በመጫን ከዚ በፊት የተለቀቁትን ጽሑፎች እንድታነቡ እንጋብዛለን
  የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ልደታቸው /ታኅሣሥ 24/
https://t.me/EwketBirhan/3926

  ፍልሰተ ሥጋሁ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት /ግንቦት 12/
https://t.me/EwketBirhan/4586

  አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዕረፍታቸው /ነሐሴ 24/
https://t.me/EwketBirhan/5099