2022-07-08 19:58:08
በነገራችን ላይ ለዐማራ ህዝብ ጭፍጨፋ ትልቁ ምክንያት ነሐሴ 15 ቀን 1987 ተደንግጎ የወጣው የህወሓት እና የኦነግ "የተሰነይ ማኒፌስቶ" በመባል የሚታወቀው ሕገመንግሥት ተብዬው ነው።
ልብ ብላችሁ ተከታተሉኝማ፣
ሕወሓት እና ኦነግ ተጨቆኑ የሚሏቸውን ብሔሮች "ነጻ የሚያወጣ" ሰፋ ያለ መብት የሚሰጥ ሕገመንግሥት ሲያወጡ፣ ጨቋኝ ነበር የተባለውን የዐማራ ሕዝብ በስብሰባው ላይ ተወካይ እንኳን እንዳይኖረው አድርገዋል። በሰኔው 83'ቱ የሽግግር ወቅት ጉባኤም ሆነ በኋላም በ1987 ሕገ መንግሥት በማርቀቁ ሂደት ዐማራው በብሔር ደረጃ አልተወከለም።
በጣም የሚያስገርመው በወቅቱ ከ80 ሺህ ሕዝብ የማይበልጥ ሕዝብ ያለው "የም" ሲወከል፤ በ1999 ዓ.ም. ሕዝብና ቤት ቆጠራ እንኳን የሕዝብ ቁጥሩ ከ180 ሺህ የማይበልጠው ሐረሬ ወይም አደሬ በንቅናቄ ፓርቲ ሲወከል፤ ከሀገሪቱ 1/3ኛ በላይ የሚሸፍነው ዐማራ የሚባል ነገድ ሳይወከል ቀረ።
ለዐማራ ህዝብ ሞት፣ መፈናቀልና ስደት ምክንያት የሆነው የወያኔና የኦነግ ሕገመንግሥት ተመርኩዞ የተነደፈው የክልሎች ሕገመንግሥትም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዐማሮችም እውቅና አይሰጥም።
በአንጻሩ፤ የዐማራ ህዝብ 81.5 በመቶ አካባቢ በሚሸፍነው ክልል ውስጥ የዋግኸምራ፣ የአዊ፣ የአርጎባ፣ የኦሮሞና የቅማንት ብሔረሰቦች ማንነታዊ አስተዳደር ተሰጥቷል።
ለምሳሌ፤ በኦሮሚያ ክልል የሚኖረው የዐማራ ነገድ ከ20 ሚሊዮን በላይ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ይህም በክልሉ ከሚኖሩት ነገዶች መካከል ከኦሮሞው ቀጥሎ በሕዝብ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ እንደሆነ የህዝብ ቤት ቆጠራ ያሳያል። በኦሮሚያ ክልል የዐማራ ህዝብ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ ቢሆንም የዐማራ ብሔረሰብ ልዩ ዞን የለም።
የኦሮሚያ ሕገመንግሥት ምዕራፍ 2. አንቀጽ 8. እንዲህ ይላል፣ "የኦሮሞ ህዝብ የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባለቤት ሲሆን፣ የህዝቡ የበላይነትም የሚገለጸው በሚመርጣቸው ተወካዮችና ራሱ በቀጥታ በሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው"
በአንጻሩ በአማራ ክልል ውስጥ የኦሮሞ ብሔረሰብ ድርሻ ከክልሉ ሕዝብ 2 ከመቶ ብቻ ቢሆንም፤ "የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን" የሚል አጥር ግን ተፈጥሯል።
በኦሮምያና በሌሎችም ክልሎች የሚኖረው በሚሊዮን የሚቆጠረው ዐማራ ግን ማንነቱ ተክዶ፣ እንደሌለ ተቆጥሮ ምንም የፖለቲካ መብት እንዳይኖረው ተደርጎ በሁለተኛ ደረጃ የክልል ነዋሪነት የጨለመ ሕይወቱን በመግፋት ላይ ይገኛል። የብሄር ማንነትን መሠረት ያደረገ ፌደራላዊ አወቃቀር በምትከተል ሀገር የኦሮሚያ፣ የደቡብ፣ የቤንሻንጉልና ሌሎችም ክልሎች የፌደራሉ ሕገ መንግስት ካስቀመጠው መርሆ በተቃራኒ በእነዚህና በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ዐማሮች በቂ ሕጋዊ፣ አስታደራዊና ፖለቲካዊ መብት አለመሰጠቱ የሚያስገርም ነው።
በ1999 ዓ.ም. የሕዝብና የቤት ቆጠራ መሠረት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባጠቃላይ የነዋሪው ብዛት 748,345 ነው። ከዚህ ቁጥር ውስጥ በርታ 199,303 ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ዐማራው 170 ሺህ ነው። ነገርግን የክልሉ ሕገመንግሥት ባለቤት የሚላቸው በርታን፣ ከዐማራ ያነሰ ቁጥር ያላቸውን ቁጥራቸው 160 ሺህ የሆኑትን ጉሙዝን፣ ቁጥራቸው 60 ሺህ የሆኑትን ሽናሻንና 15 ሺህ የሚሆኑትን ማኦን ብቻ ነው። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገመንግሥት አንቀጽ 2. እንዲህ ይላል፣ "በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች የሚታወቁ ቢሆንም የክልሉ ባለቤት ብሄር፣ ብሄረሰቦች በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦና ኮም ናቸው" ይላል። በክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዐማራ እንኳን መሥራች ሊባል ቀርቶ ማንነቱ እንኳን ተሰርዟል።
በ1999 የሕዝብና የቤት ቆጠራ መሠረት በጋምቤላ ክልል የሚኖረው የዐማራ ህዝብ 25,862 ነው። ማኦ 64 ብቻ ናቸው። ማኦ የተሰኘው ብሔረሰብ ከዐማራው ቁጥር እጅግ አነስተኛ ቢሆንም በጋምቤላ "መሥራች ብሔረሰብ" ተብለዋል።
ባጠቃላይ በስምንቱም ክልሎች በብዙ ሚሊዮን የሚቈጠር የዐማራ ህዝብ መኖሩ እየታወቀ በያለበት ራስ ገዝ እንዲሆን፣ መንግሥታዊ ውክልና እንዲኖረው፣ በቋንቋውና በባህሉ እንዲጠቀም አልተፈቀደለትም። አሁን አለ የሚባለው ፌደራሊዝም በሚደነግገው መሠረት በኦሮምያ ሆነ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ዐማሮች ባሉበት አካባቢ የራሳቸውን ዕድል በራሱ እንዳይወስኑ፣ ማንነታቸው ተጠብቆ፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዳያሳድጉ፣ በቋንቋቸው እንዳይዳኙ ተጨፍልቀው ይገኛሉ። እንዲህ ዜግነታዊ መብቱን ገፈው፤ የመምረጥና የመመረጥ መብት ነፍገው ሲያበቃ የተከተሉት ዘዴ ዐማራ "መጤ" ነው የሚል ወካይ ስም በመስጠት መግደል ነበር።
ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ተብዬው ተቀዶ ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ መጣል አለበት የምለው። ይህ ሕገአራዊት እንዲቀየር ከፍተኛ ትግል ከሁላችንም የሚጠበቅ ይሆናል። ለዐማራ ህዝብ ስቃይ ምንጩ ይህ የተሰነይ ማኒፌስቶ ነው።
https://t.me/ETHIOZENA24
1.4K views🅝🅔🅖🅡🅞 🅜🅐🅝, edited 16:58